በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ 20 ንጹሓን በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለጸ

0
2021

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ቦሌ ቀበሌ 20 ንጹሐን ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ከሥፍራው በቅርብ ርቀት የነበሩ ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ‹‹20 ንጹሐን ዜጎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተጨፍጭፈዋል›› ሲሉ ነው እማኝነታቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

ኹነቱን በመከታተል ላይ እንደነበሩ የተናገሩት ምንጮች ባብራሩት መሠረት፤ የታጣቂ ቡድኑ አባላት የግድያ ጥቃቱን ያደረሱት በነሐሴ ወር መግቢያ 2014 ሲሆን፤ ቦታውን ዘልቆ ያየውና ሁኔታውን የዘገበው ጋዜጠኛ የለም ነው ያሉት።

እንደ ገለጻው ከሆነ፤ ግድያው የተፈጸመው በኹለት ተከታታይ ቀናት ማለትም ባሳለፍነው ነሐሴ 1 እና 2/2014 ሲሆን፤ ‹‹መንግሥት መፍትሄ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም ጋዜጠኞች እንኳ ሁኔታውን አለመዘገባቸው ከጥቃቱ በላይ ሀዘን ሆኖብናል›› የሚል ቅሬታ አንስተዋል።

የግድያ ጥቃት አድርሰዋል የተሉት ታጣቂዎቹ አመጣጣቸው ምንጃር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በሚዋሰነውና ልዩ ሥሙ አምሳአምስት በተሰኘው ሥፍራ ወደ ቦሌ ቀበሌ ማለትም በላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ በመዝለቅ  መሆኑን የዐይን እማኞቹ አብራርተዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ በፊት ምንጃር አካባቢ ባደረሰው ዘረፋ ዋጋቸው 700 ሺሕ የሚገመቱ ከብቶችን እንደወሰደ ያስታወሱት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፤ አሁንም የሟቾቹን በርካታ ንብረት ስለመዝረፉ ገልጸዋል።

ጥቃት የተሰነዘረባቸው የቦሰት ወረዳ ቦሌ የላይኛው አዋሽ ነዋሪዎች፤ ‹‹በከፋ ኹኔታ ተጨፍጭፈዋል›› ነው የተባለው። ይሁን እንጂ ታጣቂ ቡድኑ ያሻውን አድርጎ ቢሄድም መንግሥትም ሆነ ሌላ የሚመለከተው አካል ስለ ሟቾቹ ምንም ያለው ነገር አለመኖሩ እንዳስከፋቸውም ወቀሳዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ግድያ የተፈጸመበት አካባቢው የብርቱካን አትክልት የሚበዛበት እና ለበርካታ ዓመታት የአማራ ተወላጆች የሚኖሩበት መሆኑም ተብራርቷል።

መንግሥት ያስተዳድረኛል ብሎ ተስፋ የሰነቀው ሕዝብ በታጣቂዎች ይገደላል ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ምንድን ነው?›› የሚለውን ጥያቄ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሦሰት ሰዎች ደጋግመው አንስተዋል።

በተያያዘም፤ ‹‹አርሶ አደፋርሶ፤ አርሞ ኮትኮቶ በመጨረሻም አጭዶና ወቅቶ ምርት ከማቅረብ በዘለለ ሌላ ፖለቲካ የማያውቅ የዋህ ሕዝብ መንግሥት የማይደግፈው ለምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄም ያነሱ ሲሆን፤ ለመንግሥት እና ለሚመለከተው አካል ደርሶ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ተስፋ አድርገዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች በቄለም ወለጋም ሰሞኑን እንዲሁ 50 የሚደርሱ ንጽሐን ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውን የጠቆሙ ሲሆን፤ ከሳምንት በፊት በነበረው ጥቃትም  በቦሰት ወረዳም እስረኛ፤ ዳኒ እና ሌሎች ሥፍራዎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ኦነግ ሸኔ በቦሰት ወረዳ የግድያ ጥቃት ሲያደርስ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆነ ያነሱት መረጃ አቀባዮቹ፤ ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ በፊት ወደ ምንጃር የተለያዩ ቀበሌዎች ሰርገው ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ራሱን የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር ብሎ የሚጠራው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ስፍራዎች በንጹሐን ላይ በተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እንደሚያደርግ የሚነገርለት ሲሆን፤ በቦሰት ወረዳ ኅዳር 22/2014፣ 14 ንጹሐን ዜጎችን እንዲሁም በዚሁ ወረዳ አዋሳኝ ምንጃር አሞራ ቤት ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባሳለፍነው ግንቦት ወር፤ በወለጋም የተለያዩ ሥፍራዎች በተደጋጋሚ  ግድያ መፈጸሙ ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here