በሱማሌ እና በአፋር ክልል መካከል ዳግም ባገረሸ ግጭት 700 አካባቢ የሚሆኑ የሱማሌ ክልል ተወላጆች የደረሱበት እንደማይታወቅ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ፓርቲ (ኦብነግ) ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ሰሞኑን በነበረውና ዳግም ባገረሸው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሱማሌ ክልል ነዋሪዎች በአፋር ክልል አስተዳደር ሚሊሻዎች መገዳላቸውን የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አባል አሕመድ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የፓርቲው አባል በተናገሩት መሰረት፤ በስፍራው የሚያጠና አካል ባለመኖሩ የሟቾችን ትክክለኛ ቁጠር በትክክል ማወቅ ባይቻልም 700 የሚደርሱ ሰዎች እንደሞቱ ይታመናል ብለዋል።
በተያያዘም ‹‹የሟቾችን ቁጥር የሚያጣራ አካል ስለሌለ ትክክለኛ ቁጥር 700 ነው ብለን መወሰን ባንችልም፣ ተገድለው ይሁኑ ታፍነው ይሁኑ ማወቅ በማይቻልበት ኹኔታ ላይ ነው ያለነው። እስከ 700 የሚደርሱ ሰዎች ግን የሉም›› ነው ያሉት።
ጥቃቱን የፈጸሙት የአፋር ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች መሆናቸውን የጠቆሙት አሕመድ፤ ግድያው የተፈጸመውም ሁንዲፍቱ፤ አደይቱ፤ ገርበኢሴ እንዲሁም ሥማቸውን አላስታውስም ባሏቸው በሌሎች ኹለት ሥፍራዎች ነው ብለዋል።
በመሆኑም የፓርቲው አባል <የሟቾች> ቁጥር ከ700 ሊያንስ ወይም ሊጨምር እንደሚችልም ጠቅሰዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የአፋር ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ሙሐመድ ዳውድ በበኩላቸው፣ በሱማሌ ክልል ሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት ግድያ እንዳልተፈጸመ ነው ምላሽ የሰጡት።
የአፋር ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ሕዝቡ ግድያ እንዳልፈጸመ የሚገልጹት ሊቀመንበሩ፤ ይልቁንም የሱማሌ ክልል የአፋር ክልል የሆነን መሬት በመያዝ በአፋር ዜጎች ላይ ጥቃት የመፈጸም ሙከራ እንደሚያደርግ ነው የጠቀሱት።
አዲስ ማለዳ በሱማሌ ሕዝብ ላይ ተከስቷል የተባለው ጭፍጨፋ በማስመልከት ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ከአፋር ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አሕመድ ካሎይታ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።
የኦብነግ ፓርቲ ግን <<አልገደልንም ብሎ መካድ ኹለተኛ ጥፋት ነው>> ብለው፤ <<ለመካድ ከፈለጉ ኹኔታውን ቀርጸው ለምን በማህበራዊ ሚዲያ ለቀቁት? ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የሚስተዋለው የግድያ ምስል ለመግደላቸው ምስክር ነው>> ብለዋል።
ምናልባት የሟቾቹን ቁጥር በመግለጽ ልዩነት ቢኖር እንጂ የአፋር ክልል ‹‹አልገደልኩም›› ብሎ መካድ እንደማይችልም አሕመድ ጨምረው ተናግረዋል። የፓርቲው አባል በተያያዘም፣ ‹‹በእስር እያሰቃዩት ያለውንና የቀረጹትን የሟቾች ምስል እንዴት ይክዳሉ?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
ከሞት የተረፉት ሰዎች በችግር ላይ ስለመሆናቸውና በርካታ ግመሎቻቸውን እንዲሁም ሌሎች ንብረቶቻቸውን ሜዳ ላይ ጥለው እንደሄዱም ተመላክቷል።
በኹለቱ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በዐስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደተፈናቀሉና በአስከፊ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ የሶማሌ ክልላዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ አሕመድም ከሞት የተረፉ ነዋሪዎቹ ድጋፍ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮቹ በሲቲ ዞን ኤረር ወረዳ ስለመሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ መንገዶች በመቆራረጣቸው ተሽከርካሪ ማስገባትም ስላልተቻለ የእርዳታ ድጋፍ አልተደረገላቸውም ተብሏል።
ጥቃቱ በተሰነዘረባቸው አካባቢዎች የነበሩ የሱማሌ ክልል ነዋሪዎች ግድያውን ለመመከት ያልቻሉት ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች የአልሸባብን ጥቃት በመጋፈጥ ላይ ስለሆኑ ነውም ተብሏል።
የአፋር ክልል ልዩ ኃይልም በነዋሪዎቹ ላይ ጥቃቱን አድርሷል የተባለው ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም መሆኑንም አሕመድ አንስተዋል።
በአፋርና በሱማሌ ክልል መካከል በግጦሽ መሬት ምክንያት በሚፈጠር አለመግባባት ለዓመታት በተደጋጋሚ ግጭት በመነሳቱ በነዋሪዎች ላይ ሕልፈተ ሕይወት፤ የንብረት ውድመት እና መፈናቀል ሲከሰት መቆየቱ አይዘነጋም።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014



