ተዘርፎ የወጣ አንድ ሲኖትራክ የሞላ መዳብ እስከ 100 ሚሊዮን ብር እየተሸጠ ነው
ተቋርጦ የቆየው የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ዋና ተባባሪነት ከፍተኛ ዝርፊያ እየተፈጸመበት መሆኑን የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ዝርፊያውን በዋናነት የሚፈጽሙት ፕሮጀክቱን ለመጠበቅ የተመደቡት ‘የአፋር ክልል ልዩ ኃይሎች’ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ የሕወሓት ኃይሎች ከአካባቢው ከወጡበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ቆሞ አያውቅም ነው ያሉት።
ነዋሪዎች አክለውም፣ በተለይ የሸዋሮቢት መጋዘን በጣም ትልቅ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች የተከማቹበት ቢሆንም፣ አብዛኛው ቁሳቁስ ተዘርፎ አልቋል የቀረውንም ሰሞኑን በከፍተኛ ሁኔታ እያወጡ እየሸጡት ነው ብለዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፣ ‹‹ሰሞኑን ተቀይሮ የመጣው የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ደግሞ ጭራሽ ሲኖትራክ መኪና የሚገዛኝ እያለ ነው አሉ። ያለእነሱ ፈቃድ ማንም ሰው አይገባም፣ እነሱ ናቸው የሚሸጡት። ከእነሱ ጋር በመነጋገር የምትፈልገውን ዕቃ ከፍለህ ታወጣለህ።
አሁን ኹሉንም ጨርሰው ወደ ነዳጅ ዞረዋል።፣ ማሽንና መኪኖችን ከመጋዘን ወደ በረሃ በመውሰድ ዝርፊያም ጀምረዋል።
በዚህ ዝርፊያ ብዙ ሰው ሚሊየነር ሆኗል። ከዚህ ሄዶ አዲስ አበባ የሚሸጥ አንድ ሲኖትራክ የሞላ መዳብ እስከ 100 ሚሊዮን ብር ነው የሚሸጠው። ይህ ሲሆን ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይ ያሉ አካላት አያውቁም አይባልም ብለዋል።
<<የመኪና ጎማ እየተነቀለ ነው እየተወሰደ ያለው። ፕሮጀክቱ ከዚህ በኋላ ቢጀመር እንደ አዲስ ነው የሚጀመረው። የቀረው ሀዲዱና አሸዋው ብቻ ነው። መጋዘን ውስጥ ተጠቅልሎ የተቀመጠው ብቻ ሳይሆን የተዘረጋው ሽቦም ተወስዷል።
ሕዝቡ ሊያልቅ የደረሰ ፕሮጀክት ለምን እንደዚህ ይሆናል፣ ሕግ የለም ወይ እያለ እያማረረ ነው ያለው። መንግሥት ለምን ዝም እንዳለ ግራ ያጋባል።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከሰሞኑ ጀኔረተሮችም እየወጡ እየተሸጡ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ለሚመለከተው አካል ለማመልከት ብንፈልግም፣ ተሳስረው ስለሚዘርፉት የሚሰማን አካል አይኖርም፣ ባለቤት ያጣ ሀብት ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ ባቡር ፕሮጀክት (AKH Railway Project)፣ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መነሻ በጀት ተይዞለት ያፒ መርከዚ ((Yapi Merkezi)) በተሰኘ የሥራ ተቋራጭ ሲገነባ የቆየ ቢሆንም፣ ሥራ ተቋራጩ በጦርነቱ በደረሰበት ውድመት የሥራ ውሉን አቋርጦ ወደ አገሩ መመለሱና ተመልሶ ወደ ሥራ እንዲገባ ድርድር እየተደረገ ነው መባሉን አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መዘገቧ የሚታወስ ነው።
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 94 በመቶ ደርሶ እንደነበር መገለጹም ይታወቃል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ለፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አብዱልከሪም መሐመድ (ኢ/ር) ደጋግማ ብትደውልም ስልካቸው ባለመሥራቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014



