አጭበርባሪዎች ይለዩ!

0
954

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን ውስጥ ተከሰቱ ለማለት የሚከብዱ ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች መፈፀማቸው እየተበራከተ ይገኛል። በሰው ላይ የሚፈፀም ዘግናኝ ወንጀል እንደፈፃሚውና እንደምክንያቱ የሚለያይ ቢሆንም፣ ያለምንም ማመንታት ሊወገዝና እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ነው።

በሌላ በኩል፣ በሕይወት ያለነውን ብቻ ሳይሆን መጪ ትውልድንም ሊያጠፋ የሚችሉ አሳፋሪ ወንጀሎች መፈፀማቸውንም እየተለማመድነው እንገኛለን። ከአነስተኛ የኪስ ማውለቅ ወንጀሎች ጀምሮ ከፍተኛ ውንብድናዎች መጠናቸውና ብዛታቸው እያደር እየጨመረ መምጣቱን መመልከት ይቻላል። እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች የተበራከቱት ከመንግሥት አካላት ቸልተኝነት የተነሳ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በግለሰብ ደረጃ ለራሳቸው ጥቅም ብለው ከሚዘርፉና ከሚያጭበረብሩ በላይ፣ እንደፍትሕ ሰጪ የመንግሥት አካል እየተንቀሳቀሱ ኅብረተሰቡ ፍትሕ አልባ የሆነ እንዲመስለው የሚያደርጉ የበለጠ ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል። “ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ” እንደሚባለው ፍትሕን ለማሟላት ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ራሳቸው እያጭበረበሩ ኅብረተሰቡን የሚያማርሩ ከሆነ ወደ ተስፋ መቁረጥ እንዲገባ ስለሚያደርጉ በአፋጣኝ ሊታሰብባቸው ይገባል።

በተለይ ሠነድ የሚያጭበረብሩ የትክክለኞቹን ታማኝነትም ስለሚያሳጡ በአጠቃላይ የስርዓቱን ታማኝነት አደጋ ውስጥ ስለሚከቱ፣ በዘመናዊ መንገድ አገር አስተዳድራለሁ ብሎ የሚያምንም ሆነ ልጅን አሳድጎ ለቁምነገር ለማብቃት የሚያስብ ሁሉ ሊያጤነውና ተግባሩን ለማጥፋት ሊንቀሳቀስ ይገባዋል።

ከሠሞኑ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ከ100 በላይ በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ገብተው የሚሠሩ መገኘታቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎ መረጃው ኅብረተሰቡን አለማስደነቁ ሊያሳስብ ይገባል። ከዚህ ቀደም በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ተሰግስገው ያለምንም ትምህርት ማስረጃ ጭምር ሲያጭበረብሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሹመኞች ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉ አይረሳም።

የባለፈው ምህረት እንደማስተማሪያ ባለመቆጠሩ ሳቢያ ለካድሬዎች ሲባል በይቅርታ የተተወው የሰነድ ማጭበርበር አሁን ወደ ባለሙያዎችም ማደጉ እየተሰማ ነው። የትውልድን እጣ ፋንታ የሚወስኑና ወደፊቱን የሚቀርፁ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ የተለያዩ ኃላፊዎች የተጭበረበረ ሰነድ ተጠቅመው ሥራ መያዛቸው ወይም እድገት ማግኘታቸውና በአንድ ትንሽ የማጣራት ሥራ መገኘቱ እንደአገር ሊያሳፍር በተገባ ነበር።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሕክምና ሙያ፤ በዳኝነትና ጥብቅና፤ በመምህርነት፤ በግንባታ እንዲሁም በማናቸውም የሰው ልጆችን ሕይወት በቀጥታ አደጋ ላይ ሊጥሉ በሚችሉ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ተቋማት የሠራተኞቻቸውን ማስረጃ ሊፈትሹ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በትምህርት ማስረጃ በኩል የሚሠሩ ማናቸውም ማጭበርበሮች ደግሞ በኹሉም ዘርፍ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉና የጉዳት መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ መዘዞችን ሊያስከትሉ ስለሚችሉ በከፍተኛ ትኩረት ሊታዩ ይገባል።

ያጭበረበሩትን ለይቶ በይቅርታ ማለፍ ውጤታማ እንደማያደርግ ከዚህ ቀደም በነበረ ተሞክሮ ስለታየ፣ ከዚህ በኋላ የማያዳግም አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። አሁንም ተገኙ በተባሉ አጭበርባሪዎች ላይ ተወሰደ የተባለው እርምጃ እንደ ጉዳቱ አስከፊነት ተመጣጣኝ ነው ሊባል ባይችልም፤ እንደጅምር ጥሩ ነው። ነገር ግን ገና ተጎልጉሎ ያልወጣው ብዙ እንደሆነ አመላካች ነው።

ቅጣቱም ሆነ አስተማሪነቱ በተጭበረበረ ሠነድ የሚጠቀሙት ላይ ብቻ እንዲሆን ማድረግ ሳይሆን፣ እንዲያጭበረብሩ ሰነዱን በክፍያ ያዘጋጁላቸው ታድነው ካልተያዙና ሌላውን የሚያስፈራራ እርምጃ ካልተወሰደባቸው፣ ቀጣይ ትውልድን የባሰ አበላሽተው መመለስ የማይቻልበት አዘቅት ውስጥ ኹላችንንም መክተታቸው እንደማይቀር አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

ለሥልጣን ሲባል የሌላቸውን የትምህርት ማስረጃ እንዳላቸው ተደርጎ በሿሚዎቻቸው ታዘውም ይሁን ሐሳብ ቀርቦላቸው የሚቀበሉና በዛው ማስረጃ እንደፈለጉ እጃቸውን የሚጠመዝዟቸው ሹመኞችም ለራሳቸው ሲሉ ያጭበረበሩትን ገሐድ አውጥተው ራሳቸውን ከባርነት ሕይወት ሊታደጉት ይገባል።

በተጭበረበረ ሰነድ ብቻ ሳይሆን፣ በውሸትና በዘመድ ተመርኩዘው የማይገባቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት የያዙም ማስተማሪያ ሊሆኑ ይገባል። ትምህርቱን አጠናቆ ሥራ ለመፈለግ ዓመታትን የሚባዝነው ወጣት ያለዘመድ መቀጠር እንደማይችል ካመነ ቆይቷል። ይህን አስተሳሰብ መቀየርና በአፋጣኝ ትክክለኛውን መስመር ማስያዝ ካልተቻለ ታዳጊዎች ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትና በመማር የሚያምኑበትን ሞራል ማሳጣት ስለሚሆን በአስቸኳይ ርብርብ ሊደረግበት ግድ ይላል።

በሕጋዊና በልፋቴ ሠርቼ ያልፍልኛል የሚል ትውልድ ለማፍራትም ሆነ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሹመኛም ሆነ ባለሀብት ከጠፋ፤ መጨረሻችን ምን እንደሚሆን ግልፅ ነው። አትዋሽ እያሉ ወላጆች ልጃቸውን ለማስተማር የሚወስኑበት ጊዜ እያበቃ እስኪመስል እውነተኛነት ጅልነት እየተደረገ መጥቷል።

ይህ ዓይነት ማኅበረሰባዊ እሴትን መሸርሸር ብቻ ሳይሆን እንደጎርፍ ወስዶ ባዶ የሚያስቀር አጉል አስተሳሰብ፣ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድም መሰናክል እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

የተጭበረበረ ሰነድ በትምህርት ማስረጃ ላይ ብቻ ሳይሆን መታወቂያን በመሳሰሉ የማንነት ገላጭ ሰነዶች ላይም ተዘውትሮ የሚታይ ነው። ይህ ዓይነት ማጭበርበር ለብዙ ኢ-ፍትሐዊ አሠራሮች ብቻ ሳይሆን ለከባባድ ወንጀሎችም በር የሚከፍት መሆኑ እሙን ነው።

ለአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ምቹ ስለሚያደርግ በሚል በቅርቡ እንኳን በአማራና ኦሮሚያ ክልል መካከል ውዝግብ የፈጠረውና መንገደኞች እንዳያልፉ የተደረገበት ቅሬታ ያስነሳው ክስተት መማሪያ ሊሆን ይገባል። ይህ ዓይነት ማጭበርበር በአንድ ወቅት ላይ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ በሕዝብ ቆጠራ ወቅትና በበጀት አደላደል ጊዜ ተደጋግሞ እንዲዛባ ያደርጋል። በምርጫ ወቅትም የተሳሳተ መረጃና ውጤት እንዲኖር ስለሚያደርግ ማኅበረሰብን ለማያባራ መቃቃርም ስለሚዳርግ ይበልጥ ሊታሰብበት ይገባል።

በዘመናዊ መልክ አሻራና የዐይን ብሌን የሚወሰድበት የአመዘጋገብ ሂደት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ በመታወቂያ ብቻ ሳይሆን በሀብት ምዝገባና በሌሎችም አስፈላጊ መስኮች ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ይታመናል። በተለይ እንዲህ ዓይነት ዘመናዊ ተብለው የሚመጡ ሰነዶችም ሆኑ መንገዶች እንደ ኮንደሚኒየም አወጣጡ በቴክኖሎጂ ተደግፈው እንዳይጭበረበሩ ሊታሰብበት ግድ ይላል።

በየትኛውም መስክ አጭበርባሪዎችን ሊቆጣጠሩና ሊፈትሹ የሚችሉ ጎበዝ ባለሙያዎችን ለመቅጠርም መንግሥት ልስላሴ ሊያሳይ አይገባም። ሰነፉ ጎበዙንና ብልሁን መቆጣጠር ስለማይቻለው፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ብሩህ አእምሮ ያላቸውን መንግሥት ከሕዝብ ጎን እንዲሰለፉ ሊሠራ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here