በመንግሥት ምክንያት የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ኪሳራ እያጋጠመው ነው

0
987

በሚሊኒየም አዳራሽ ጥቅምት 6 ቀን 2012 በይፋ የተከፈተው የአፍሪካ እንስሳት ሀብት አውደ ርዕይን ለማዘጋጀት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር የአዳራሹን ቦታ በውል በመያዝ ከ10 አገራት የተውጣጡ አንድ መቶ ዓለም ዐቀፍ ኩባንያዎች የሚሳተፉበትን አውደ ርዕይ ማዘጋጀት የጀመረው፤ ይሁንና በመንግሥት ትእዛዝ አዳራሹን ለቆ እንዲወጣ ተደርጓል።

አውደ ርዕዩ የእንስሳት ጤና፣ መኖ፣ እንዲሁም የወተት እና የስጋ ዘርፉን በዘመናዊ መልክ በቴክኖሎጂ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበትን መንገድ ማመቻቸት ዓላማው ያደረገ እንደነበር እና ለተለያዩ የኢንቨስትመንት እድል የሚፈጥር እንደነበር የዝግጅቱ አሰናጅ የፕራና ኢቨንትስ መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነቢዩ ለማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አራት ሺሕ ከሚበልጡ የዘርፉ አጋሮች ጋር የቴክኖሎጂ ሽግግርን መሰረት ያደረገ የንግድ ልውውጥ እና የወጪ ንግድ የገበያ ትስስር እንደሚካሔድበት ታስቦ ሚሊዮኖች ቢያወጡበትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፍ ምረቃ ምክንያት አዲስ ፓርክ ገና ዝግጀቱ በተጀመረ በአንድ ቀን ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ቀጭን ትእዛዝ ያስተላልፋል።

ይህንንም ተከትሎ አብዛኛዎቹ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በሌሎች ሀገራት እንደዚህ ዓይነት ክስተት አጋጥሟቸው ስለማያውቅ አውደ ርዕዩን ለቀው ወደ መጡበት መመለሳቸውንም ነብዩ ተናግረዋል። ያሉትም ቢሆኑ አውደ ርዕዩ አስቀድሞ በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት ቅዳሜ የሚጠናቀቅ በመሆኑ እና አቅደው የመጡት እስከዛ ቀን በመሆኑ ቅዳሜ ማምሻውን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በመወሰናቸው በተለይ ኢንቨስት የማድረግ ሃሳባቸውን የሚያስቀይር፣ አገርን እና ኢኮኖሚውንም የሚጎዳና በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለ ድርጊት ነው ብለዋል።

በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት ዘጠነኛው የኢትዮ ዶሮ እርባታ (ፖሊታሪ) ኤክስፖ፣ 5ኛው የአፍሪካ የእንስሳት አውደ ርዕይ እና ጉባኤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሔዱትን አሳ እርባታን (አኳ ካልቸር) እና ንብ ማነብ (አፒ ካለቸር) በአንድ ላይ በማድረግ የየዘርፎቹን ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ለማሳተፍ የያዘው እቅድም የሃገር ውስጥ እና የውጪ ባለሃብቶችን ያንገላታ በመሆኑ ማዘናቸውን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

‹‹በአዳራሹ አስተዳደር በኩል ቀድሞ የተያዝ እና ክፍያ የተፈፀመበት በመሆኑ እንደማንለቅ ተነግሮን ዝግጅቱን ብንቀጥልም አዳራሹ ቅድሚያ ለሚሰጠው ሀገራዊ ጉዳይ ይፈለጋል እንዲሁም የመንግሥት መርሃ ግብሮች በአዳራሹ ቅድሚያ ያገኛሉ በሚሉ ምክንያቶች ተባረናል›› እንደ ነብዩ ገለጻ።

በዚህም ምክንያት የቦታ እና የጊዜ ለውጥ በማድረግ ከጥቅምት 8 እስከ 9 ጦር ኀይሎች ቀራንዮ ፕላዛ ላይ ለማድረግ እንደተገደዱም ገልጸዋል። አክለውም እቃዎችን ለማጓጓዝ፣ ለሠራተኞች ክፍያ እና ለሌላ አዳራሽ ኪራይ እንዲሁም ለማስታወቂያ ተጨማሪ ወጪ ለማወጣት ተገደናል ብለዋል።

ከዚህ በኋላ በምናደርጋቸው አውደ ርዕዮች ላይ ዓለም ዐቀፍ እና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ለመካፈል ያላቸውን ፍላጎት የሚቀንስ ነው ያሉ ሲሆን፣ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች እርስ በእርስ የሚነጋገሩበት እና መረጃ የሚለዋወጡበት መንገድ ስላላቸው ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከዚህ በኋላ በሚደረጉ አውደ ርዕዮች ለመካፈል ፍላጎት አይኖራቸውም ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም በሀገሪቱ መልካም ገፅታ ግንባታ ላይ መጥፎ ሊባል የሚችል አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እና ማንነታቸውን ለመግለፅ ያልፈለጉ ሌሎች የኤግዚቢሽን አዘጋጆች እንዳሉትም፣ በተመሳሳይ ከመንግሥት በሚመጡ ትእዛዞች ሚሊዮኖችን ለመክሰር መዳረጋቸውን ይገልፃሉ። ውሉን በተደጋጋሚ የሚያፈርሰው አዲስ ፓርክም፣ ከመንግሥት ጋር ባለን ውል መሰረት በሚል ምክንያት፣ በተደጋጋሚ ኪሳራ ከመግባታቸው ባሻገር የኢንዱስትሪውን ገፅታ የሚያጎድፍ ተግባር ነው ብለዋል። መንግሥትም ኢኮኖሚውን እና ኢንቨስትመንትን አበረታታለሁ ቢልም በተግባር ግን እንዲህ ያሉ ተግባራትን መፈፀሙ አግባብ አይደለም ብለዋል።

ጉዳዮን በማስመልከትም የአዲስ ፓርክ የሽያጭ ክፍል ኀላፊ ሀብታሙ ነጋሽ ጋር ስልክ በመደወል ምላሽ እንዲሰጡን ብንጠይቀም አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here