በ2011 በሐዋሳ ከተማ በተደረገው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ እንደ አዲስ በተነሳው የውህደት ጉዳይ ላይ በተለይ ሕወሃት ተቃውሞውን መግለፁን ተከትሎ የግንባሩ ጽሕፈት ቤት አርብ ጥቅምት 2012 በሰጠው መግለጫ ሕወሃት መሰረታዊ የሆነ ስህተት ያለበት መረጃ ሆነ ብሎ በማሰራጨት ላይ ነው ሲል ወነጀለ።
ሕወሃት እንደ ድርጅትም ሆነ በድርጅቱ አመራሮች የሚሰጣቸው መግለጨዎች አህዳዊ መንግሥት ለመመስረት የታቀደ አስመልሰው ማቅረቡ ስህተት ነው ያለው የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ‹‹የአንድ ሃገር መንግሥት አወቃቀር የሚነሳው በሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ እንጂ በአንድ ፓርቲ ፍላጎት ሊሆን አይችልም›› ሲል ገልጿል።
አዲሱ ውህድ ፓርቲ ‹‹ሀቀኛ ፌዴራሊዝምን›› እውን በማድረግ እኩልነትን ያረጋግጥ ይሆን እንጂ የሕዝቦችን መብት የሚሸራርፍበት ምክንያት የለም ሲል ሃሳቡን ገልጿል። ሕወሃት አሁን ያለውን የውህደት ሃሳብ አሁን ያለው አመራር ይዞት የመጣው ማስመሰሉ አግባብ አይደለም ሲል የኮነነው መግለጫው፣ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የውህደቱ አቀንቃኝ እና መሪም ነበር ሲል ገልጿል።
በተመሳሳይም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ኦዴፓም በተገባደደው ሳምንት ባካሔደው ስብሰባ የግንባሩ ውህደት ላይ የመከረ ሲሆን ‹‹ትላንት እውነትና የፌዴራሊዝም ስርአት ተግባራዊ አንዳይሆን ይዘውት በነበረው ሥልጣን ስርአቱን ሲያፋልሱ የነበሩ ሕዝቡን የማይወክሉ ጥቂት ቡድኖች ዛሬ ላይ ራሳቸውን ለሕገ መንግሥቱ የቆሙ እና የፌዴራሊዝም ዋስ ለማስመሰል የሚያሰራጩት መሰረተ ቢስ መረጃ ተቀባይነት የለውም›› በማለት ትችቱን ሰንዝሯል።
ግንባሩ ባስጠናው ጥናት ዴሞክራሲዊ እና አቃፊ እንዳልሆነ የቀረበ እና በፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴም ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ ላይ መደረሱንም ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት የፓርቲውን አደረጃጀት በማዘመን በዘመናዊ አሰራር የሚመራ ፓርቲ ለመመስረት አብዮታዊ ዴሞክራሲን በመደመር እሳቤ ለመለወጥ ውይይት ተጅምሯልም ሲል ኦዲፒ በመግለጫው አስታውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012



