የወይን አስፈላጊነት

0
2243

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አዳምና ሔዋን አትብሉ ከተባሉት የበለስ ፍሬ ቀጥሎ፣ በቀደምት ልጆቻቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ ከነበሩ ፍራፍሬዎች ውስጥ ወይን ከቀዳሚዎቹ መካከል እንደሆነ ይነገራል። የተለያዩ መዛግብትም የወይን ፍሬ ጥንት መኖርን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሥልጣኔዎች ውስጥ ማለፉንም ይጠቅሳሉ።

በተለምዶ ወይን ሲባል የሚጠጣውን አስካሪ የወይን ጠጁን እንደሆነ የምንረዳ ብዙዎች ልንሆን እንችላለን። መጠጡም ቢሆን ከምግብ በኋላ ለምግብ መፈጨት ይጠቅማል ሲባል እንሰማለን። ነገር ግን፣ እንደብርቱካንና ማንጎ ጭማቂ ሆኖ ሳይብላላና አልኮል ሳይሆን ተጨምቆ ስለመጠጣቱ ብዙ የሚሰማ ነገር የለም።

ወይንን ብዙ አገራት የማብቀላቸውን ያህል ፍሬው ከሚበላው ይልቅ ለመጠጡ መጥመቂያነት እንደሚውል ማስረጃዎች ያሳያሉ። ለምግብነትና አልኮል ለመጥመቂያ የሚውለው ዓይነቱ የተለያየ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገራት ለመጥመቂያም ለመብልነትም የተለመደው አንድ ዓይነቱ ነው ማለት ይቻላል።

በመጠኑ ከፍ ብሎ ፕሪም የሚያክለው በውጪ ዓለም የተለመደው ለመጠጥ መጥመቂያነት የማገልገል እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። በመጠናቸው ትንንሽ እንደሆኑት ወፍራም ቆዳና በቂ የስኳር ይዘት ስለሌለውና ደካማ አልኮል ስለሚያስገኝ፣ እንዲሁም ጣዕሙም ተወዳጅ ስላልሆነ የጠረጴዛ ወይን ተብሎም ይገለፃል።

በብዛት ረገድ ለምግብነት የሚውለው የወይን መጠን ከአጠቃላይ ምርቱ አንፃር ይሄን ያህል ነው ብሎ መናገር ባይቻልም፣ መጠጡን ለመጭመቅ ከሚውለው መጠን አንፃር በፍሬነቱ የሚበላው አነስተኛ እንደሚሆን ይገመታል። አንድ ሊትር ወይን ለማምረት አንድ ተኩል ኪሎግራም ገደማ የሚመዝን የወይን ፍሬ ያስፈልጋል።

አንድ የወይን ፍሬ በውስጡ ከ80 እስከ 90 በመቶ ውሃ በመያዙ ለመጠጥ መጥመቂያነት ተፈላጊ ያደርገዋል። ከሌሎች ፍራፍሬዎችም ‘ዋይን’ የሚባለው ወይን ጠጅ እንደሚጠመቅ ቢነገርም፣ በተፈላጊነት ረገድ የተለመደው የወይን ዘለላን የሚያክል እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለምግብነት ተብሎ ብቻ የሚመረተው የወይን ፍሬ መጠን በእርግጠኝነት ይህን ያህል ነው ባይባልም፣ በትኩስነቱ እንደበሰለና ደርቆም ለምግብነት እንደሚውል ይታወቃል። የወይን ዘቢብ በመባል የሚታወቀው ለምግብ ፍጆታነት ብቻ ሳይሆን፣ ለሃይማኖታዊ ግልጋሎትም ይውላል። የሚወሰድበት መንገድና መጠንም ይሁን የሚጠቀምበት ማኅበረሰብ ዓይነት ቢለያይም፣ ጥቅም እንዳለው ግን ይታመናል፤ ሲነገርም ይሰማል።

የወይን ፍሬ በብዙ አገራት ውድ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው በተፈለገበት ቦታ ሁሉ አለመብቀሉ እንዲሁም እንክብካቤው ከፍተኛ ወጪና ክትትል የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ ብዙዎች እንዳያገኙት ዋጋውም እንዳይቀመስ በማድረጉ ሌሎች ፍራፍሬዎች የሚገኙትን ያህል በየቦታው ሊገኝ አይችልም። ለማጓጓዝም ሆነ ለረጅም ጊዜ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ስለሆነም፣ በብዙ ነጋዴዎችም ሆነ ተገልጋዮች ዘንድ ተመራጭ አይደለም።

ከዓለም አገራት ብዙ ወይን የምታመርት ቻይና ስትሆን፣ ጣሊያን ደግሞ ቀጣይ ሆና ከቻይና አንፃር በግማሽ ገደማ ያነሰ ወይንን ታመርታለች። አሜሪካም በሦስተኛ ደረጃ የተመዘገበች ሲሆን፣ ሦስቱ አገራት ወደ ሠላሳ ሚሊዮን ቶን ወይን ለማምረት ወደ ኹለት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን እንደሚጠቀሙ አትላስ ቢግ የተሰኘው ድረገፅ ያስነብባል።

ወይን ለምግብነትና ለአልኮል መጠጥነት ከማገልገሉ በላይ ለጤናም ጠቃሚ ነው ተብሎ ከዚህ ቀደም ይነገር ነበር። ይህ አስተሳሰብ ዝም ተብሎ በመላምት የመጣ ሳይሆን በተለያዩ ጥናቶች የታወቀ ነው። የፍሬውን ይዘት ተመርኩዘው በተለያዩ ጊዜያት ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፤ ተክሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው።

ሠሞኑን በጀሩሳሌም ፖስት ላይ ይፋ የሆነ የጥናት ውጤት እንደጠቆመውም፣ የወይን ፍሬን አዘውትሮ መመገብ ለጤና እንደሚጠቅም ብቻ ሳይሆን፣ ቢያንስ እድሜን በአምስት ዓመት ያህል መጨመር እንደሚያስችል ነው።

የዌስተርን ኒው ኢንግላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉት በተባለው ጥናት መሠረት፣ ለመልቀምም ሆነ ለመብላት ምቹ እንደሆነ የሚነገርለትን ይህን ፍሬ ለምግብ መፍጨት ሂደት ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የሰውነታችን ጤና እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ነው። በተለይ ስብን በመመገብ የሚመጣ በሽታን ከመከላከል አኳያ ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው ብለዋል።

እንደተመራማሪዎቹ ከሆነ፣ በጥናት የተገኘው ውጤት እጅግ የሚደንቅ ነው። ወይንን መብላት ገዳይ የሆኑ በሽታዎች እንዳይከሰቱብን በማድረግ ፍሬውን ከማይበሉት በተሻለ አምስት ዓመታት ያህል በሕይወት መቆየት ያስችላል ብለዋል።

ወይን በውስጡ ያለው የኬሚካል ንጥረ ነገር በሆድ እቃችን ውስጥ ያሉ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች እንዲበዙ ስለሚያደርግ፣ እንዲሁም የሰውነታችንን የኮሌስትሮል መጠን የሚቀንሱ ውሕዶች ስላሉት ጠቃሚነቱ የጎላ ነው ይላሉ። የሰውነት መቆጣትን የሚገድቡ አንቲ-ኦክሲዳንቶችንም በውስጡ ከመያዙ ባሻገር፣ የልብ ድካም በሽታ እንዳያጋጥመንም ሆነ በካንሰር የመጠቃት እድላችን እንዲቀንስ የወይን ዘለላ ይጠቅማል ሲሉ የግኝታቸውን ውጤት አስረድተዋል።

ከሁሉም ጠቀሜታቸው በላቀ ሁኔታ በዘመናችን እጅግ የተለመዱ የፋብሪካ የሆኑ የታሸጉ ምግቦች እንዳይጎዱን ማድረጋቸው ነው። የስብ መጠናቸው የበዛና ውፍረትንም የሚያስከትሉ ኮሌስትሮልን የመሳሰሉ የሰውነት ጤናን የሚጎዱት በሰውነታችን አካሎች ውስጥ እንዳይፈጠሩ ወይን ውስጥ ያለ ውሕድ ይጠቅማል ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል።

ከጤናና ከአመጋገብ ጋር የተገናኙ ከ600 በላይ ሳይንሳዊ የምርምር ጥናቶችን እንዳሳተሙ የሚነገርላቸው የዚህ ምርምር ባለቤት የሆኑት ጆን ፔዞቶ(ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ሰው የሚበላውን ምግብ ይመስላል የሚለውን አባባል በጥናት ማረጋገጥ እንደሚቻል ነው። ጎጂ ንጥረ ነገር ያላቸውን የሚመገብ በሰውነቱ ላይ ጉዳቱ እንደሚታየው ሁላ፣ ጠቃሚዎቹን አዘውትረው የሚመገቡም ሕይወታቸው ላይ በጉልሕ ይታያል ይላሉ። ከፅንሰታችን ጀምሮ እስከሞታችን አሳድጎ ለውጣችንን የሚያሳየን ምግባችንና አመጋገባችን ነው ሲሉም ስለምርጫችን አስፈላጊነት ይናገራሉ።

አሁን ምርምር ያደረጉበት ወይንን በተመለከተም፣ ወይን የራሳችንን ሰውነትና ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን ለውጥ የሚያመጣው በዘርም (ጄኔቲካሊ) ወደ ትውልድ የምናስተላልፈው ላይ ዘላቂ ለውጥ እንደሚያስከትል ነው።

ተመራማሪውና ቡድናቸው ስለወይን ያገኙትን የጥናት ውጤት ይፋ ያደረጉት ከብዙ ሙከራና ፍተሻ በኋላ እንደሆነ ይናገራሉ። አይጦችን በቤተሙከራ ውስጥ በመለየት በኹለት ቡድን ከፍለው ሲያስተውላቸው ቆይተው ለውጣቸውን መመዝገባቸውንም ጠቅሰዋል። ኹለቱንም ቡድን ስብነት ያላቸውን ቶሎ የሚያወፍሩና ለጤና ጎጂ እንደሆኑ የሚታወቁ ምግቦችን እስኪበቃቸው እንዲበሉ ካደረጉ በኋላ ለይተው ለአንደኛው ወይንን መግበዋል። በመደበኛነት በአንዱ ጎራ ብቻ ላሉት የደረቀ የወይን ዱቄትን በመደበኛነት በመመገብ ልዩነቱን በጊዜ ሂደት መከታተል ችለዋል።

ከምገባው በኋላ ከኹለቱም ወገን ያሉትን ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸውን አይጦችን ለያይተው መርምረዋል። ወይንን በመደበኛነት ይመገቡ የነበሩት የበለጠ ጤናማ ሆነው የተገኙ ሲሆን፣ በምዕራባዊያኑ ዓለም የተለመደን የስብ መጠኑ ከፍ ያለን የተግበሰበሰ ምግብን ያለ ወይን የሚመገቡት ላይ ግን ልዩነት አግኝተዋል። ጉበታቸው ላይ ጨምሮ በተለያዩ በሽታዎች ሊያስጠቃቸው በሚችል መልኩ የሰውነት አካሎቻቸው ላይ አላስፈላጊ ስቦች ተከማችተው ማየት ችለዋል።

በዚህም አማካኝነት ወይን የተመገቡት ካልተመገቡት በአንፃራዊነት ረዘም ላለ ጊዜ በሕይወት መቆየት መቻላቸውን ማረጋገጥ እንደቻሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል። በአይጦቹ እድሜ ልዩነት ላይ የታየው ለውጥ ወደ ሰዎች ሲቀየር ከአራት እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ የሚችል ለውጥ እንደሆነም ዋናው ተመራማሪ ተናግረዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት የወይን ጥቅሞች ባሻገር ለመርሳት በሽታ እጅግ ጠቃሚ መሆኑም ተነግሯል። አልዛይመር በመባል ለሚታወቀው በሽታ መከላከያ ይሆናል የተባለው ወይን የአእምሮ መረጃ አስተላላፊ ሕዋሶችን በማነቃቃት ፈጣንና የማንረሳ እንድንሆን ውስጡ  ያሉ ንጥረነገሮች ይረዱናል ይላሉ። ከአስተሳሰብ ብቃት ጋር በተገናኘ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ግንኙነታችንም የዳበረ እንዲሆን ያደርጋል፣ እንዲሁም የልብ ድካም እንዳይከሰትብን ይከላከልልናል ሲሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታውን በግኝታቸው ይፋ ማድረጊያ ወቅት አብራርተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here