መነሻ ገጽአምዶችዓውደ-ሐሳብኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በጉራጌ ሕዝብ ኪሳራ ማዳን አይቻልም!!

ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በጉራጌ ሕዝብ ኪሳራ ማዳን አይቻልም!!

ውጥንቅጥ በበዛበት አስቸጋሪ ጊዜ ጠቅላላ የአገሪቱ ሕልውናና የእያንዳንዱ ሕዝብ ሕልውና ነጻነትና ዴሞክራሰዊ መብትን የመጎናጸፍ ዕድል እውን ሊሆን የሚችለው ትንንሽ ነገሮችን በማጋነንና በመጯጯህ አይደለም ይላሉ፤ ግዛቸው አበበ። ይልቁንም መሠረታዊ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ማመንና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ትኩረትን አሳርፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ይመክራሉ። የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን መነሻ አድርገውም በክፍል አንድ ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ እንደ አገርና እንደ ሕዝብ የገጠሙ ኪሳራዎችን ጠቅለል አድርገው አንስተዋል።

ክፍል አንድ

የጉራጌ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ማንሳትን ተከትሎ የብልጽግና ደጋፊዎችና አክቲቪስቶች ብቻ ሳይሆኑ ብልጽግናን በመቃወም ከሚታወቁ አክቲቪስቶች (አንቂዎች)፣ ፖለቲከኞችና ዩትዩበሮች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ይህን የጉራጌ ሕዝብ ጥያቄ አገርን የማፍረስና የሕዝብ አንድነትን የማናጋት አንድ እርምጃ አድርገው ሲያወግዙትና ሲተቹት ተደምጠዋል። ከእነዚህ አብጠልጣዮች አንዳንዶቹ የሲዳማ ሕዝብ ያቀረበውን የክልልነት ጥያቄ በተመሳሳይ መንገድ ኢትዮጵያን የማፍረስ እርምጃ እንደሆነና ከብዙ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሰዎች አሳምረው የገነቧትን ሐዋሳ ከተማን የመስረቅ ግርግር አድርገው ሲገልጹት የምናውቃቸው ናቸው።

እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎችን ቀርበው ማነጋገር፣ የሕዝብን ሐሳብ መረዳትና የሕዝቡን ፍላጎት ማክበር ሲገባቸው እነሱ ብቻ ለአገር የሚቆረቆሩ ይመስል በየግል ሐሳባቸው እየተነዱ ለትዝብት የሚዳርጋቸውን ሥራ እየሠሩ ነው።

አንድ ወይም አንዲት አክቲቪስት ወይም ምሁር ነኝ ባይ ግለሰብ የክልልነት ጥያቄ ከሚያቀርቡ በመቶ ሺዎች ወይም በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የአንድ ብሔረሰብ ሕዝቦች መካካል የእነሱን ያህል አዋቂና ለአገር የሚቆረቆር የሌለ የሚያስመስል ወሬ በየቀኑ ለአንድና ለኹለት ሰዓታት ራሳቸው በከፈቱት ወይም በጓደኞቻቸው ዩትዩብ ላይ ሲያስተጋቡ መዋላቸው የትዕቢተኛነታቸው፣ የትምክህተኛነታቸውና ለሕዝብ አክብሮት የጎደላቸው የመሆናቸው ማሳያ ከመሆን አልፎ እንደ ቁም ነገረኛ ሊቆጠሩ አይገባም።

ከሳምንታት በፊት በአዲሰ አበባና በሌሎች የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተደረጉና ‹‹… ለእኛ የማትበጅ ኢትዮጵያ ፍርስርሷ ይውጣ…›› የመሳሰሉ ፉከራዎችን እያሰሙ ሲጨፍሩ የነበሩ ተማሪዎችን ንቁ ታጋዮች አድርገው ሲያንቆለጳጵሱ ከርመወል። አሁን ኢትዮጵያዊነቱን በማክበር እንከን የማይገኝለትን የጉራጌን ሕዝብ የክልልነት መብቴ ይፈቀድልኝ ስላለ ብቻ በጸረ-ኢትዮጵያዊነት ፈርጀው እንዳሻቸው እየወረፉትና ሊያስተምሩት እየከጀሉ ነው።

‹የኢትዮጵያን መፍረስና የሕዝቦቿን መበታተን ሊያስከትሉ የሚችሉ መሠረታዊ ችግሮች ምንድን ናቸው?› “እነሱን ለማስወገድስ እንዴት መታገል ይገባል?’ ብሎ በመጠየቅ ለስር ነቀል ለውጦችና ለወሳኝ ሥራዎች ከመነሳሳትና ሌሎችን ከማነሳሳት ይልቅ በትንንሽ ጉዳዮች ላይ የመንጨርጨር ትግልን የሙጥኝ በማለት ሌላውም መንጨርጨርንና እያማረሩ መቀመጥን ባህል አድርጎ ጊዜውን እንዲያባክን አሳፋሪ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።

ጸረ-ብልጽግና አክቲቪስቶች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ኢትዮጵያዊ ተንታኞች ነን ከሚሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቂት የማይባሉት በትንንሽ ጉዳዮች ላይ ትኩረታቸውን አሳርፈው በዩትዩብ፣ በፌስቡክና ሊያስተናግዷቸው በፈቀዱ የስርጭት ሚዲያዎች (የኤፍ.ኤም. ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች) ላይ የመንጨርጨር፣ ያንንም ይህንንም የማውገዝ ሥራ ላይ በተጠመዱበት በዚህ ጊዜ የብልጽግና ቡድን ዝርክርክነት ቅጥ ያጣ ሆኖ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ኪሳራ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖችን ያጎበጠው ድህነትና የኑሮ ውድነት በቃ ሳይባል አገሪቱ በየቦታው ከሚከሰቱት ከትንንሽ ሰላም ነፋጊ ግጭቶች ጀምሮ በወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአፋርና በሶማሊያ ክልሎች ያለ ማቋረጥ እስከሚካሄዱ ከባድ መሣሪያዎችን የቀላቀሉ ትንንሽ ጦርነቶችን እያስተናገደች ነው። ጎሳንና ሐይማኖትን መሰረት አድርገው ወገኔ አይደለም ያሉትን በግለሰብ ተነሳሽነት ወይም በቡድን ተደራጅቶ ጥቃት መፈጸም እንደ መብት ተቆጥሮ ያለ ጠያቂ ይካሄዳል።

ነገሩን ማስቆም የሚገባው መንግሥትም ነገሩ ቀለል ተደርጎ እንዲታይ ሊመክር ይሞክራል። ጥቃቶች አንድን ግለሰብን መግደልን ወይም ቤተሰብንና የአንድን መንደር ነዋሪ እንዳለ መጨፍጨፍን የሚመለከቱ ናቸው። ከክልሌ ውጣ ብሎ ማሳደድ፣ ንብረቱን በመዝረፍና በማውደም እንዲሁም ሰብል የሚዘራበትንና ምርት የሚሰበሰብበትን ጊዜ ጠብቆ አካባቢውን ሰላም በመንሳት በረቀቀ ዘዴ ሕዝቦች ተስፋ እንዲቆርጡና በምሬት እንዲሰደዱ ማድረግ ወዘተ… የተለመዱ የዘረኝነት ጥላቻን የማሳያ ድርጊቶች ሆነዋል።  እነዚህን መሰል ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉና እየከፉ በመቀጠል ላይ ናቸው።

የብልጽግና ቡድንን የዝርክርክነት ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን የሚያጋልጠው በትግራይ ክልል የተፈጸመውና መዘዙ ለአማራና ለአፋር ክልሎች የተረፈው ቸልተኝነት ነው። በመጀመሪያ በዛላንበሳና በአካባቢው ቀጥሎም በባድመና በአካባቢው የሰፈረው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ከድንበር አካባቢ እንዲርቅና ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለማንቀሳቀስ የተደረገው ሙከራ በአመጸኛ ወጣቶች ተመካኝቶ ሲከሽፍ ታይቷል። በኋላ መሄድ ከፈለጋችሁ መሣሪያውን ለትግራይ ትታችሁ ውጡ ሲባል፣ ከ2011 ጀምሮ ሕወሐት ሚሊሻና ልዩ ኃይል ከማሠልጠን አልፎ ኮማንዶና የከባድ መሣሪያዎች ምድብተኛ ኃይል (መድፈኛ፣ ታንከኛ ወዘተ…) ሲያሠለጥን፣ በየጊዜው ወታደራዊ ትርኢትና ሰልፍ በመቀሌና በሌሎች የትግራይ ከተሞች በተደጋጋሚ ሲያሳይ ተስተውሏል።

ይህን ጨምሮ፣ ሕወሐት ለጦርነት ዝግጁ መሆኑ በይፋ ሲናገርና ግልጽ ሕወሐታዊ መልዕክት ሲያስተጋባ በትግራይ የሰፈረው ጦር አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን በመገንዘብና በዚያ ያለው ከባድ ቀላል የጦር መሣሪያ አፈሙዝ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ሊደገን እንደሚችል ግምት ተወስዶ ነገሩን ለማክሸፍ ዘዴ ሊቀየስና ሰላማዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባ ነበር። ተነግሮ ያላለቀ ሰቆቃ በሰሜን ዕዝ ወታደሮች ላይ ተፈጽሟል። ይህን ተከትሎም ኤርትራን ያሳተፈ ጦርነት ተካሂዷል። በዚያ የነበረው የጦር መሣሪያም በብዛት ኢትዮጵያን አውድሞ ወድሟል ተብሎ ይገመታል። የተወሰነው ደግሞ ለሌላ የማውደም ዘመቻ ዝግጁ ሆኖ ተቀምጧል።

በሰሜን የተካሄደው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈና የሰነከለ ትልቅ ጦርነት ነው። ጦርነቱ ፍጹም ጠላት በሆኑ ኹለት አገራት መካከል ለምሳሌ በፍልስጥኤምና በእስራኤል መካከል ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቅበት ደረጃ ነው የተካሄደው። ጦርነቱ ሰላማዊ ሰዎችን ሆነ ብሎ መግደልና መሰንከል፣ ሕጻናትንና በዕድሜ የገፉ ሴቶችን መድፈር፣ የምስኪን ገበሬዎችን እንስሳት ያለ ምንም ይሉኝታ አርዶ መብላትና ምግብ ከመሆን ያመለጡት በጥይት ረሽኖ ባለቤቶቻቸውን ማራቆት፣ በጎተራና በክምር ኩንታል የተቀመጠ እህልን መዝረፍና በማቃጠል ወይም በውኃ በማጥመቅ ማበላሸት፣ የግልና የመንግሥት ተቋማትን ንብረትን መዝረፍና ለዘረፋ የማይመቸውን ወይም ቢዘረፍ ብዙም አይጠቅምም ተብሎ የተፈረጀውን ማውደም ወዘተ… በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በሰፊው የተፈጸሙ የለየለት የጠላትነት ድርጊቶች ናቸው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ወይም በትግራይ ተጀምሮ እስከ ደብረ-ሲና ተቀጣጥሎ በቀጠለው ጦርነት የመቀሌ እንደ በሻሻ መሆን በኩራት ተነግሯል። ትግራይ ክልልን በ40 እና በ50 ዓመት፤ አማራ ክልልን በ20 እና በ30 ዓመት ወደ ኋላ የመመለስ ሥራ መሠራቱን ከየክልሎቹ በሚመጡ እሮሮዎች ተረድተናል። የሰሜኑ ጦርነት ትልቅ ኪሳራ ትግራይን እንደ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ሊሆን ይችላል። ይኼ ደግሞ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ አገሪቱን ከመጠን በላይ አዳክሟልና ሌላው ኢትዮጵያዊው ኤርትራዊ ወገኖቹን በሸኘበት ሁኔታ ተጋሩዎችን ከመሰናበት የተለየ ሚና ላይኖረው ይችላል።

ሕወሐት ጎሰኝነትን ሆነ ብሎ ያሰፈነውና አንዱ ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ ዐይኑ እንዲያየው የሚያደርግ መንፈስ ያሰፈነው ለኢትዮጵያ ብሎ እንዳልሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። ሕወሐት የዘር ፓርቲዎችን አዋቅሮ፣ ለዘበኝነት የማይመጥኑ የሚላቸውን በፖለቲከኝነት ሥም አደራጅቶ በክልልና በፌዴራል የሥልጣን ቦታዎች እየሰገሰገ የኖረው እንዲህ ዓይነቱ የመከራ ጊዜ ሲመጣም ሊጠቀምባቸው አስቦ ይሆን?

- ይከተሉን -Social Media

ይህን መሰል ውጥንቅጥ በበዛበት አስቸጋሪ ጊዜ ጠቅላላ የአገሪቱ ሕልውናና የእያንዳንዱ ሕዝብ ሕልውና ነጻነትና ዴሞክራሰዊ መብትን የመጎናጸፍ ዕድል ዕውን ሊሆን የሚችለው ትንንሽ ነገሮችን በማጋነን በድጋፍ በመቧረቅ ወይም በትንንሽ ችግሮች ላይ ትኩረትን በማድረግ በተቃውሞና በእሮሮ በመጯጯህ አይደለም። ይልቁንም በሌሎች ሦስት መሠረታዊ ለውጦች ብቻ መሆኑን ማመንና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ትኩረትን አሳርፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

ሕዝቦች የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ ወይም ከተማ አስተዳደር አከላለልን የሚመለከት ጥያቄዎችን ባነሱ ቁጥር የዚያ ሕዝብ አካል ያልሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አገር ሊፈርስ ነው እያሉ ማላዘናቸው ግን ጊዜን ከማባከንና ራስን ግምት ውስጥ ከመጣል ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች የሚፈቱት፣ የኢትዮጵያ ዘላለማዊ የግዛት ሉዓላዊነት የሚከበረውና ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተባብረውና ተከባብረው የሚኖሩት (1ኛ) እውነተኛና ጠንካራ የተቃውሞ አደረጃጀትን ፈጥሮ ችግሮቹ የሚጠይቁት ትግል በማካሄድ (2ኛ) ሕገ-መንግሥቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን አንድነት በሚያስከብር መልኩ እንዲሻሻል በማድረግ (3ኛ) ዘርንና ጎሳን መሠረት ያደረገ የፖለቲካና የክልል አደረጃጀት እንዲሁም በብልጽግና ዘመን ብልጭ ድርግም እያለ መታየት የጀመረውን ግዛትን፣ ፓርቲንና የንግድ ኤምፓየርን ሐይማኖትን መሠረት አድርጎ ማደራጀትን በማስቀረት፤

(4ኛ) ቀደም ብሎ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ጭፍን አገልላጋይ የሆኑና አሁን በዚያው ጭፍን የአገልጋይነት ወይም የተላላኪነት ባህሪቸው (ባህላቸው) የብልጽግና/ኢሕአዴግ አገልጋይ የሆኑ ዋና ዋና ሰዎችን እድሜ ልካቸውን ከፖለቲዊ ተሳትፎ እንዲገለሉ ማድረግ ነው። በተጨማሪም እነዚህ ግለሰቦች ለ5 ወይም ለ10 ዓመታት ከማንኛውም መንግሥታዊ የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታዎች ገለል ብለው እንዲቆዩ ማድረግ የሚያስችል መራርና ወሳኝ ትግል በማካሄድ ነው።

እስከ 2010 መገባደጃ የተካሄደው ትግል እውነተኛ ለውጥ ያላመጣውና፣ ለውጡን ከሕወሀት/ኢሕአዴጋዊ አገዛዝ ሕወሐት ወደሌለበት ኢሕአዴጋዊ አገዛዝ ብቻ የቀየረው፤ አፈናውን ከአንድ ፓርቲ (ቡድን) አፈና ወደ ግለሰባዊ አፈና ያሻገረው በአብዛኛው በወጣቶች ትግል የመጣውን ለውጥ ተረክቦ አገርን መምራት የሚችል ሁነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ስላልነበረ መሆኑ ይታወቃል። አሁንም ጠንካራ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መድኅን ሊሆን የሚችል ፓርቲ የመወለድ ዕድሉ ብዙም የሚሳካ ሆኖ አይታይም።

እውነተኛና ጠንካራ የተቃውሞ አደረጃጀትን ፈጥሮ አገሪቱን እንደነቀርሳ ሆነው ውስጥ ውስጧን የሚቦረቡሯትን ችግሮች ለመቀረፍ የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ ለመፍጠር ከሚደረገው ትግል ይልቅ ብልጽግናዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደሚያመልኩት ሁሉ ተቃዋሚ የሚባሉት ቡድኖችም የየራሳቸውን ግለሰብ የማምለክ አካሄድ እየተከተሉና ግለሰብ በሚቀደው ቦይ እየፈሰሱ ነው።

ትልቅ ፓርቲ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው፣ የ1997ቱን ቅንጅት ተክቶ ሕዝቦችን በዘርና በሐይማኖት ሳይከፋፈሉ እንዲደራጁ በማድረግ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ሕልውና ያስከብራል፣ የእውነተኛ ዴሞክራሲዊ ስርዓትን መወለድ እውን ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ኢዜማ ዜጎችን ወደሚያደናግርና የራሱን ተለጣፊነት ራሱ በይፋ የሚናገር ጀሌ ወደ መሆን እየወረደ ነው።

የዘመኑ መኢሶን ሊባል የሚገባው፣ ሰርጌንም ሞቴን ከገዥው ቡድን ጋር ያድርገው ባዩ ኢዜማና አለቆቹ በተለይም ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ብልጽግና አገሪቱን እያሻገረ ነው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ የተሻለ አሻጋሪ የለም ብለው በድፍረት በመናገር ተወዳዳሪ የሌላቸው ሆነው እየታዩ ነው። ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በቅርቡ ከአንድ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የብዙዎች ሕይወት እንደዋዛ እየተቀሰፈ ባለበት፣ ሰላም በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በታጣበትና ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ መሆኑ እየተባባሰ መምጣቱ እየታየ ባለበት ጊዜ እሳቸውና ፓርቲያቸው ብልጽግናና የአገር ሉዓላዊነት በጠቅላይ ሚ/ሩ አመራር እውን እየሆነ ነው የሚሉት እንዴት እንደሆነ ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበረ።

- ይከተሉን -Social Media

ፕ/ሩ የሰጡት መልስ በጣም አሳዛኝ፣ ለሰው ሕይወትም ሆነ ለአገሪቱ ሕልውና ብዙም የማይጨነቁ መሆኑን የሚያጋልጥ ነው ማለት ይቻላል። ፕሮፌሰሩ የደርግ ዘመንን የመጀመሪያ አራት ዓመታት አውስተው በደርግ የመጀመሪያ ዓመታት ሰው በቀይ ሽብር ሲረግፍ ስለነበረ አሁንም በየቦታው ሰዎች እንደ ቅጠል መርገፋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ የብልጽግና ቡድንን ለወቀሳ መዳረጉ ተገቢ አይደለም። በለውጥ ጊዜ የሚከሰት ነው ብለው ለመሞገት ሞክረዋል።

ፕሮፌሰሩ ቀጠል አድርገውም ደርግ በሥልጣን ዘመኑ ባሳለፋቸው የመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ከፍተኛ ደም መፋሰስን ያስተናገደ ቢሆንም፣ ከአራቱ ዓመታት በኋላ ወደ እርጋታ ገብቷል በማለት መሠረተ ቢስ የሆነና ደም መፋሰሱ መቀጠሉን ችላ ያለ ታሪክ በመንዛት ተለጣፊነታቸውን ተገቢና ተቀባይነት ያለው መሆኑን ለማስረዳት  ሞክረዋል።

ከደርግ ዘመን የመጀመሪያ አራት ዓመታት በኋላ ከከተሞች የተባረረው ኢሕአፓ በትግራይ፣ በጎንደርና በጎጃም አንዳንድ ቦታዎች ጦርነት ለማካሄድ መሞከሩ፣ እየተንጠባጠበ ቢሆንም ኢሕአፓ እስከ 1983 መጨረሻ ጠመንጃ ይዘው የሚወራጩ አባላት እንደነበሩት የሚካድ አይደለም። በጎንደርና በትግራይ ምድር በኢዲዩ አማካኝነት የሚካሄደው ጦርነትም ከሙሉ ግብግብ አልፎ አልፎ ወደሚካሄዱ ጥቃቶች፣ ፈንጅ በመቅበርና ግለሰቦችን በመግደል እያሰለሰ መቀጠሉ ግልጽ ሃቅ ነው።

ኢዲዩ በደርግና በሕወሐት ከባድ ዱላ ስብርብሩ ወጥቶ ጥቂት አመራሮቹ ወደ ሱዳን ሸሽተው አርፈው የተቀመጡ ቢመስልም፣ በቅጥረኛነት ኢትዮጵያን የማጥቃት ሐሳባቸውን ሰንቀው መቀመጣቸው የሚረሳ አይደለም። በትግራይ ምድር በሕወሐት ተሳትፎ የቀጠለውን፣ በኤርትራ ምድርም በመጀመሪያ በጀበሃና በሻእቢያ በኋላም በሻእቢያ አማካኝነት ተጧጡፎ የቀጠለውን በመጨረሻም አገሪቱን በማፍረስ የተጠናቀቀውን ጦርነት ፕሮፌሰሩ የእፎይታ ጊዜዎች ነበሩ ባሏቸው ዓመታትም ጭምር የተካሄዱ ናቸው።

በትግራይ ምድር ሕወሕት ተዳክሞ የነበረባቸው፣ በኤርትራ ምድርም ጀበሃ ወድሞ ሕዝባዊ ግንባርም (ሻእቢያም) ተዳክሞ የነበረባቸው ጊዜያት የነበሩ ቢሆንም ጦርነት አልነበረም። የወንድማማቾች መገዳደል ተገትቶ ነበረ ማለት ተገቢ አይደለም። ሃቁን ወደ ጎን በመተው፣ ዐይኔን ግንባር ያድርገው በሚል ዓይነት ክህደት በመዘፈቅ የብልጽግና አካሄድም ወደ እርጋታና ሰላም እየወሰደን ነው ብሎ ድርቅ ያለ አቋም መያዝ የጤነኛ ፖለቲካዊ ሰው አስተሳሰብ አይደለም።

የኢዜማው ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በትክክል የጠቅላይ ሚ/ሩ ደጋፊ የሆኑበትን ግላዊ ምክንያት በቀጥታ ማስቀመጥ ሲገባቸው፣ በፈጠራ ታሪክ ምክንያታዊ ሰው መስለው ለመታየት ሞክረዋል። በእርግጥ ጥቂት የማይባሉ የኢዜማ አንቱ የተባሉ ሰዎች የብርሃኑ ነጋን (ፕ/ር) አካሄድ ‹አድርባይነት› መሆኑን እየተናገሩ፣ ፕሮፌሰሩ ኢዜማን የብልጽግና ተለጣፊ አድርገውታል ብለው እየከሰሷቸው ነውና ‘የአሻግሬና የተሻገር’ ጨዋታው ብዙም የሚዘልቅ አይመስልም።

በሌላ በኩል ደግሞ ገና ከምሥረታው ጀምሮ ግራ አጋቢ አካሄድ ውስጥ የተዘፈቀው፣ ማኅበር ነው ወይስ የፖለቲከ ፓርቲ ተብሎ ሲያጠያይቅ የከረመው ባልደራስ የተባለው ፓርቲ እንኩቶ የመሆን ዕጣ የገጠመው ይመስላል። ታላቁ እስክንድር የሚሉትን ግለሰብ ‘እሱ ራሱ ነው ባልደራስ’ በሚሉ ወገኖችና እስክንድር ከፓርቲው ሰዎች መካከል እንዱ ነው በሚሉ ጓዶቻቸው መካከል በተፈጠረ ቁርቁስ፣ እንዲሁም የፓርቲው አካሄድ ግልጽና ወቅቱን የሚዋጅ አይደለም የሚል ውዝግብ ባልደራስ ችግር ውስጥ መዘፈቁ ግልጽ ሆኗል።

ይህ ውዝግብ ደግሞ ባልደራስ በስደቱ ዓለም ባሉ ግለሰቦች የመዘወር ሌላ ችግር እንዳለበት የሚያጋልጥ አጋጣሚ ፈጥሯል። የባልደራስ መሪ የነበሩት እስክንድር ነገሩን የሕጻናት ጨዋታ መፈራረስን የመሰለ ግራ መጋባትን ያስከተለ ራስን የመሰወር ድራማ መሥራታቸው፣ አገር ቤት ያሉት የባልደራስ አመራሮች በእስክንድር መሰወር ግራ ተጋብተው በስደት ካሉት ግለሰቦች መረጃ ፍለጋ መራወጣቸው ባልደራስ የተባለው ቡድን ያለበትን የአደረጃትና የአወቃቀር ችግር የሚያጋልጥ ሆኗል።

- ይከተሉን -Social Media

እስከ 120 ሺሕ አባላትን አቅፎ፣ በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ጥቂት ትልልቅ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የነበረው ኦፌኮም በገባበት ያልተቀደሰ ጋብቻ ተስፋ ሰጪ መሆኑን እያጣ ነው። ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነው፣ ኦሮሞ ቅርንጫፍ አይደለምና ተገንጥሎ ስለ መውደቅ አያስብም በሚል መፈክሩ የሚታወቀው ኦፌኮ፣ ኢትዮጵያን ሲፈልጉ እንደ ኪራይ ቤት ሲያሰኛቸው ደግሞ አንደ አገራቸው ከሚያዩት የኦሮሞ ፈርስት አቀንቃኞች ከሆኑት ከእነ ጃዋር መሐመድ ጋር የፈጠሩት ቅልቅል ለኢትዮጵያ ሕልውናና ሉዓላዊነት ጠበቃ መሆን እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።

የኦፌኮ አመራሮች ሕወሐትን የእውነተኛ ፌዴራሊዝም አባት አድርገው ማየታቸውና ፌዴራሊዝምን ከመቀሌ ለማምጣት መቀሌ ድረስ ለስብሰባ መሄዳቸው፣ የሕወሐት እስር ቤቶችን የሸራተንን የመሰለ ምቾት ያላቸው የመቀማጠል ቦታዎች አስመስለው እያወሩ በእነዚያ እስር ቤቶች ሰቆቃን የተቀበሉና ሕይወታቸውን ያጡ ኦሮሞዎች ብዙዎች መሆናቸውን ችላ ማለታቸው፣ ሕወሐቶች በኦሕዴዶች መሣሪያነት ኦሮምያን በእጅ አዙር እየገዙ የኦሮሞን ሕዝብ እየገደሉና እያሳደዱ የኖሩ መሆናቸውን የረሱ መስለዋል።

ያም ብቻ አይደለም፤ በአማራ ምድር የሚፈጸሙ የሕወሐት ሴራ ውጤት የሆኑ ግብግቦችን በሕወሐት ዐይን እያዩ ፈራጅ ለመሆን መዳዳታቸው፣ ሕወሐት የቅማንት ኮሚቴና የአገው ነጻ አውጭ ለሚባሉ ቡድኖች መቀሌ ውስጥ ጽሕፈት ቤት ከመክፈት አልፎ ተዋጊና አደጋ ጣይ ቡድኖችን እያደራጀ በአማራ ምድር በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶችን ማካሄዱን ያላዩና ያልሰሙ መስለው የአማራ ሕዝብ በቅማንትና በአገው ሕዝብ ላይ በጠላትነት የዘመተ የሚያስመስል ፕሮፓግንዳ መንዛታቸው ወዘተ… ኦፌኮ ከኢትዮጵያዊነት እየራቀ ቁጥር ኹለት ሕወሐት እየሆነ ወይም ‘ራብዐይ ወያነ’ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ሃቆች ናቸው።

ኦፌኮ ትግራይ ውስጥ በሕወሐት፣ በተቃዋሚዎቹና በምሁራን አማካኝነት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ካለው ትግራይን የመገንጠል አካሄድ አንዳች ጥቅም ለማግኘት የሚያደባ ቡድን እየሆነ ነው። በትግራይ የሚታየው እንቅስቃሴ ትግራይ የተባለች አገር መመሽረትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ በይፋ እየተነገረ፣ ኦፌኮ ብልጽግናን አገርን በማፍረሰ በሚተችበት ሁኔታ ኽወሐትን ሲኮንን አይሰማም። የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ክልሎችን ሲያዋቅር ሆነ ብሎ የአማራ ክፍለ ሀገር ከሚባሉት ከጎንደር፣ ከጎጃም፣ በወሎና ከሸዋ ሰፋፊና ለም ምድሮችን ገምድሎ ወደሌሎች ክልሎች ያካተተ መሆኑን ይታወቃል። እነዚህ የአማራ ክፍለ ሀገሮች መሬታቸውን የሚመለከት ጥያቄ ባነሱ ቁጥር ሕወሐት ‘የአማራ ተስፋፊነት ጥያቄ ነው’ ሲል ኦፌኮዎችም አብረው ይህንኑ ማጣጣያ ያስተጋባሉ።

በ2010 መጨረሻ ወራት ላይ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ተሰነጣጥቆ ለውጥ መጣ ሲባል ኢሕአዴግ አስተሳሰቡንና አሰላለፉን ሳይቀይር ሥሙን ብቻ ቀይሮ ብልጽግና ነኝ ብሎ ገዥ ለመሆን የበቃው እዚህ ግባ የሚባል ተቃዋሚ ባለመኖሩ ነው። ብሎም ተቃዋሚ ነን የሚሉ ቡድኖች በትንሽ ይሁን በትልቅ ልዩነት እርስ በእርሳቸው የሚጠላለፉ በመሆናቸው መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው። ትልቅ ይሆናሉ ተብለው ሲገመቱ አድሮ ጥጃና የብልጽግና ወይም ሕወሐት ተለጣፊ ወደ መሆን ያዘቀጡ ፓርቲዎችን አካሄድ በማየት ከዚህ በኋላ የ2010ሩን የመሰለ ለውጥ ቢመጣ እንኳ የብልጽግና ቡድን በሌላ ሥም መልሶ እንደሚነግሥ የሚያጠራጥር አይደለም።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት ያሳስበናል የሚሉ ፖለቲከኞች፣ አንቂዎችና ምሁራን ሕዝብ በየሰበቡ መተቸታቸውን ትተው በዚህ ረገድ ምክርና ትምህርት ሊሰጡ ቢሞከሩ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል።

የጠንካራ ፓርቲዎች መፈጠርና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩ ማድረግ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ ሕገ-መንግሥቱን ለአገሪቱ ሕልውናና ለሕዝቦች ተከባብሮ መኖር አስተዋጽኦ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ እንዲሻሻል ትግል ለማድረግ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩ ነው። የጠንካራ ፓርቲዎች መኖር ምርጫዎችንና ሌሎች የሕዝብን ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮችን የካድሬዎች መጫወቻ ከማድረግ ያስጥላሉ። ኢትዮጵያን ሉዐላዊነት አሳጥቶ ክልሎች ከኢትዮጵያ እየተቆረሱ እንዲሄዱ የሚፈቅደው የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ሳይቀየር ስለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ማውራት በአገሪቱ ከመቀለድ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

ግንጠላን መብት አድርጎ የሚያስቀምጠውን አንቀጽ ያካተተውን ሕገ-መንግሥት ተሸክሞ መኖር፣ ሌላ ሕወሐት ወይም የሕወሐት ጉዳይ አስፈጻሚ ከመሆን ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ከብልጽግና ቡድን ትልልቅ ስህተቶች አንዱና ዋነኛው ይህን የሕገ-ምንግሥት አንቀጽ ታቅፎ ስለ ኢትዮጵያ ዘላለማዊ የግዛት አንድነት መወሽከቱ ነው። የብልጽግና መሪዎች ተደጋጋሚ ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚል ቀረርቶ ተራ የገደል ማሚቶ ብቻ ነው።

 ‘አገርን እንዴት ማፈራረስ ይቻላል’ የሚል ኮርስ ማዘጋጀት ቢያስፈልግ በዚያች አገር ውስጥ ዘርንና (ጎሳንና) የሐይማኖት መሠረት ያደረጉ ፓርቲዎችን በማዋቀር ሕዝቦችን ማናቆር ተገቢ መሆኑን የሚያስረዳ አንድ ሰፊ ምዕራፍ ማካተቱ የግድ ነው። በዚህ ምዕራፍ ስር በዘር አንድ የሆኑትን በሐይማኖት ልዩነት፣ በሐይማኖት አንድ የሆኑትን በዘር ልዩነት አቧድኖ እንዴት ማጋጨትና ማለያየት እንደሚቻል የሚገልጹ ንዑስ ምዕራፎች ሲካተቱበት አገር ለማፍረስ የተዘጋጀው ቡክሌት ምሉዕ ይሆናል።

ከዚያም የኮርሱን ውጤታማነት ለማጉላት የራስ ወዳድና የስግብግብ ግለሰቦች ተላላኪነትና በተላላኪነት ተደራጅተው በዘርና በሐይማኖታዊ የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ እንደ አሸን በማፍላት በሚሊዮኖች ማራባት የዚችን አገር ተስፋ ቢስና ውስጡ በምስጥ እንደተቦረቦረ ትልቅ ዛፍ ከመውደቅ የተለየ ዕጣ የሌላት እንደሚያደርጋት የሚያስረዳ ክፍል የቡክሌቱ አካል በማድረግ፣ ከ1983 ጀምሮ የዘር ፖለቲካ ጨዋታ ሕጋዊ በተደረገባት ኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ሃቅ የሚያሳይ የመጨረሻ ምዕራፍ በማካተት ኮርሱን የተዋጣለት ማድረግ ይቻላል።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕልውና ያሳስበናል የሚሉ ወገኖች ጎሳን ወይም ብሔርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የግዛት (የክልል) እና የንግድ ኤምፓየር ወዘተ አደረጃጀት እንዲገታ ማታገል በተጨማሪም ከ2010 በኋላ በማቆጥቆጥ ላይ ያለ የሚመስለውን ሐይማኖትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀትና ከሐይማኖታዊ ሥራዎች ውጭ ለሆኑ ተግባራት ሐይማኖታዊ ጎጦች በመቧደን መንቀሳቀስን ለማስቆም መሥራት ተገቢ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።

ብዙዎች እምነታቸው የፖለቲካ ዓላማዎች ማራመጃና ተገቢ ያልሆኑ ንግድ መሰል እንቅስቃሴዎች ማድረጊያ መሆኑን በመቃወም ላይ ናቸው። ምሁራን፣ አንቂዎችና ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያከብሩ ፖለቲከኞች ትግል ሊካሄድበት የሚገባው ሌላው አቅጣጫ ይህ መሆኑን ተገንዝበው ርብርብ ሊያደርጉበት ይገባል።

ይቀጥላል…

ግዛቸው አበበ በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች