የሲሚንቶ ምርቶችን ግብይት እና ስርጭት ስርዓት የሚደነግገው መመሪያ ከወጣ በኋላ በብዙ ከተሞች የሲሚንቶ ምርቶች አለመኖራቸውን አዲስ ማለዳ ከተጠቃሚዎች እና ከምርት አከፋፋዮች አረጋግጣለች።
ይህ የሆነውም በመመሪያው የተላለፈው የሲሚንቶ ምርቶች ጊዜያዊ የመሸጫ ዋጋ ለነጋዴዎች አዋጭ አይደለም በሚል እንደሆነም ተገልጿል።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለሥርጭቱ የተመረጡ አንድ ወኪል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እኔ እንዳከፋፍል የተመረጥኩት ከዞን ከተማ 80 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላለው ማኅበረሰብ ነው።
ይሁን እንጂ ሲሚንቶ እንዳመጣና እንዳከፋፍል የተጠየኩት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በ40 ብር የትራንስፖርት ዋጋ ነው። ከዚህ ቀደም እንኳን ከ80 ብር በታች ስለማይጫን የትራንስፖርት ዋጋውን ስታስተካክሉ ጥሩኝ ብዬ ትቻቸው ወጣሁ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በዚህም እርሳቸው አከፋፋይ ሆነው በተመረጡበት የወረዳ ከተማ ለተጠቃሚው የሚደርስ ምንም ዓይነት የሲሚንቶ ምርት እንደሌለ ነው የተናገሩት። የሚፈልጉ አካላት ከዞን ከተማ ነው ከመመሪያው ውጪ ከሚሸጥ ሲሚንቶ ከ1 ሺሕ 500 ብር በላይ ገዝተው የሚያስመጡትም ሲሉ ተደምጠዋል።
በመዲናዋ የሚገኝ የአንድ ትልቅ ንግድ ድርጅት ተወካይ በበኩላቸው፣ ድርጅታችን ለኮንስትራክሽን ሥራ የሚያስፈልገውን ሲሚንቶ ለማግኘት ከአከፋፋይ በደብዳቤ ቢጠይቅም ሲሚንቶ የለም የሚል ምላሽ ነው ያገኘው ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የሲሚንቶ አከፋፋዮች ለግዥ የሚመጡ ተጠቃሚዎችን ሲሚንቶ የለም ሲሉ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመመሪያው የተቀመጠው መሸጫ ዋጋ አዋጭ ባለመሆኑ ሲሚንቶ አላስገባንም የሚል ነው።
ይሁን እንጂ ብዙ አከፋፋዮች መጋዘን ውስጥ በድብቅ አከማችተው ከፍ ባለ ዋጋ ለመሸጥ እየተጠባበቁ እንደሆነም ተገልጿል።
ሥሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ በግንበኝነት ሙያ የተሰማሩ ግለሰብ እንደተናገሩት፣ ለደላሎች ወይም ፋብሪካዎች ውስጥ ለሚሠራ አንድ ሰው ገንዘብ በመክፈል እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ በመጋዘን ይከማቻል። ተጠቃሚውን ሲሚንቶ የለም ይሉታል እንጂ ጊዜ ነው የሚጠብቁት ብለዋል። እርሳቸው እንዳሉትም በአዲስ አባባ አሁንም ከመመሪያ ውጪ ከ1 ሺሕ 500 እስከ 1 ሺሕ 600 ባለው ዋጋ በግልጽ ሲሚንቶ የሚሸጡ አካላት አሉ ነው ያሉት።
እስካሁን በአዲስ አበባ ከ850 ብር ባነሰ ዋጋ እንዲሁም በክፍለ አገር ከተሞች ከ1 ሺሕ 150 ብር በታች እንዲሸጡ የተወሰነ ቢሆንም በተቀመጠው ዋጋ ተጠቃሚው ሲሚንቶ እያገኘ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የሲሚንቶ ግብይትና ሥርጭት መመሪያ ከሐምሌ 05/2014 ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም፤ ከሥርጭት ትስስርና ከመሸጫ ዋጋ ጋር ተያይዞ ለተጠቃሚው እየደረሰ አለመሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም።
በተደረገ ክትትልም ሲሚንቶ ከተቀመጠው የሥርጭት መመሪያ ውጪ ከፋብሪካዎች እየወጣ በተለያዩ መጋዘኖች የሽያጭ ቦታዎች እንደሚገኝ እንዳረጋገጠ ገልጾ፣ ለዚህም በየክልሉና ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከተው የፀጥታ ተቋም ጋር በመቀናጀትና የሲሚንቶ ግብይት ቁጥጥር ቡድን በማሰማራት፣ ከመመሪያ ውጪ እየተከናወነ የሚገኘውን ሕገ-ወጥ የሲሚንቶ ግብይት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በአስቸኳይ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።
ተጠቃሚው የሲሚንቶ ምርት ማግኘት እንዲችልም፣ ለሥርጭቱ የተመረጡ አካላት በአስቸኳይ ምርቱን ከፋብሪካ በመቀበል በተላለፈው ጊዜያዊ የመሸጫ ዋጋ እንዲቀርብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀደም ብሎ ጠይቆም ነበር።
አዲስ ማለዳ ተጨማሪ ማብራሪያ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014



