የህዳሴ ግድቡን ለማጠናቀቅ ቀጣዩ የሕዝብ ተሳትፎ

0
1279

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመጠናቀቅ ጥቂት ምዕራፍ የቀረው ቢመስልም፣ ለፍፃሜ ለማብቃት ግን ቀላል የማይባል ወጪ እና ጊዜ ሊፈልግ እንደሚችል ይገመታል።

ግድቡ ከተጀመረ ከዐስር ዓመት በፊት ጀምሮ ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ ያልተለየው፣ በርካታ የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ የሚቸረው ቀዳሚው የሕዝብ ፕሮጀክት ሊባል ይችላል።

ማክሰኞ ነሐሴ 17/2014 ሕዝባዊ ተሳትፎውን የበለጠ በማነሳሳት ሀብት ለማሰባሰብ በሚል የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በዚህ ወቅት የሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንዲሁም የኹለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨትን ተከትሎ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ተፈጥሯል ነው የተባለው።

በዚህም ግድቡ ከተጀመረ እስካሁን ተሳክቶ የማያውቅ ነው የተባለ፣ ባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ ከ273 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደተሰበሰበ ተገልጿል።

ድጋፉ በግለሰብ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ጭምር እንደሆነና በዚህም በርካታ ተቋማት ለግድቡ ሰፊ ድጋፍ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እንደገለጹት፣ ግድቡ በተቋማትና ሕዝብ ተሳትፎ እዚህ የደረሰ ሲሆን፣ ባንኩ እስካሁን ለግድቡ ኃይል ማስተላለፊያ ዝርጋታ የሚውል 150 ቢሊዮን ብር ገደማ ብድር ሰጥቷል። እንዲሁም ከ425 ቢሊዮን ብር የሚልቅ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማበደሩን ነው ያስታወቁት።

አክለውም፣ የውጭ አበዳሪ በሌለበት ሁኔታ ባንኩ ብቸኛ የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ማገልገሉን ጠቅሰው፣ ለግድቡ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማሰባሰቡንም አንስተዋል።

ባንኩ ለፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጮች የባንክ ዋስትና ከመስጠት እና ሀብት ለማሰባሰብ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋዩን ያፈሰሰበት ነው ያሉት ፕሬዘዳንቱ፣ እስካሁንም የባንኩ ሠራተኞችና ባንኩ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ቆጣቢዎችና የውጭ ምንዛሬ አመንጪዎች ከባንኩ ጋር በመተባበር ግድቡን ከፍጻሜ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ትብብር እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ (ኢ/ር) በበኩላቸው፣ በአንድ ወቅት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብቶ የነበረውን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በተደረገ ሥራ በኹለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀምረናል። ሦስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት አጠናቀንም 22 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ ችለናል ነው ያሉት።

<<ፕሮጀክቶች ብዙ መሰናክል ይገጥማቸዋል፣ ይሁን እንጂ በእርግጠኝነት በቀጣይ ኹለትና ሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል>> ሲሉም ተደምጠዋል።

ግድቡ ሦስት የግንባታ ሥራዎች እንዳሉት የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ የሲቪል፣ ኤሌክትሮ ሜካኒካልና የብረታ ብረት ገጠማ (hydraulic construction) ሥራዎችን አካትቶ አጠቃላይ አፈጻጸሙ 87 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ባለፈው ሐምሌ ወር ማብቂያ 175 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል። ቀሪ 12 ነጥብ 7 በመቶ የግድቡን ሥራ ለማከናወንም ከ55 እስከ 60 ቢሊዮን ብር ይጠይቃል።

ግድቡን ገንብቶ ለማጠናቀቅም 230 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አንስተው፣ የየትኛውም አገር አምስት ሳንቲም እዳ የሌለበት፣ በፋይናንስም ግዙፍ የሆነ የኢትዮጵያውያን ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም፣ በርካታ የገጠር እናቶች ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ስላልሆኑ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩት ቁርስ ሳይሰጡ ነው። ይሁን እንጂ፣ የቁርሳቸውን ተመን ለግድቡ ያበረከቱ አዳጊዎች አሉ። ከተሰበሰበው ድጋፍ ውስጥ የገጠር እናቶችና አዳጊዎች ድርሻ ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ግድቡ የእኔ ነው የሚል ጥልቅ ስሜት አላቸው ነው ያሉት።

ፋይናንስ ከመከልከል ጀምሮ፣ ሲሚንቶ ወደ ግድቡ እንዳይገባ መከልከል፣ የሥራ ተቋራጮችን እስከማስፈራራት የሚደርሱ ጫናዎች እንደነበሩ በመግለጽም፣ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያ ሃቅ አላት እያሉ ሲጮኹ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንና ትወልደ ኢትዮጵያውያንን አመስግነዋል። አሁንም ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ያብስራ ከበደ በተመሳሳይ፣ ባንኩ በቦንድ ህትመት፣ ስርጭትና ሽያጭ ለግድቡ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ27 ሚሊዮን የሚልቁ የቦንድ ኩፖኖች ታትመው፣ ከ24 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት መሰራጨታቸውን ነው ያስገነዘቡት።

አሁንም በመላው አገሪቱ በሚገኙት 2 ሺሕ በሚጠጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎችና በተመረጡ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በቂ የቦንድ ኩፖኖች በመኖራቸው ኅብረተሰቡ ድጋፉን እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በመጨረሻም፣ በተለይ ዓለም ዐቀፍ ጫናዎችን መቋቋም እንድንችል፣ ምሁራን በየጊዜው ለሰጡት ምክንያታዊ ምላሽ፣ ግደቡ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ እንዲያገኝ ለሠሩ የማኅበራዊ አንቂዎችና ለመገናኛ ብዙኀን ምስጋና ችረዋል።

ሌላኛው በመድረኩ ተገኝተው ሐሳብ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምስክር ነጋሽ፣ ከከተማው ሕዝብ ለግድቡ እስካሁን ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በ2014 ብቻ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መድረጉን በማውሳትም፣ የግድቡ መጠናቀቅ በተለይ ለመዲናዋ ልዩ ትርጉም አለው ነው ያሉት።

ከከተማው ማኅበረሰብ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ባለፈም፣ የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ የሚቻለው አንድም ግድቡ ኃይል ማመንጨት ሲችል መሆኑን አስምረውበታል።

ቀሪ የግድቡን ግንባታ ሥራዎች ለማጠናቀቅም ከእስካሁን ያላነሰ ድጋፍ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በከተማዋ የቦንድ ሽያጭ ንቅናቄ ተጀምሯል ሲሉ ተደምጠዋል። በአገር ዐቀፍ ደረጃም ከአዲስ ዓመት ዋዜማ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ንቅናቄው የሚጀመር በመሆኑ ሕዝቡ የቻለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በዓባይ ወንዝ ላይ ቀርቶ በሌሎች ወንዞቻችን ላይም የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ግብጽን የመሳሰሉ አገራት ሳንካ ሆነው መቆየታቸውን አውስተዋል። ከዚህ ጋር አያይዘውም እውን እየሆነ ያለው ታላቁ ህዳሴ ግድብ የቅኝ ገዥዎችን የተሳሳተ ውል የሻረ፣ እንደሌሎች የወንዙ ተፋሰስ አገራት የአትዮጵያን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ፣ በተለይ በ8100 አጭር የፅሑፍ መልዕክት በቀላሉ ለግድቡ ገንዘብ እንዲዋጣ ከማድረግ ጀምሮ፣ በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉበትን አስቻይ ሁኔታ ማመቻቸት ላይ ሠርቻለሁ። ብሎም የግድቡ ሠራተኞች የማይቆራረጥ የኔትወርክ አገልግሎት እንዲያገኙ ከሳምንት እስከ ሳምንት በ24 ሰዓት ጥበቃ እየሀራሁ ነው ብሏል።

ከዚህ በኋላም ግድቡ ሙሉ ለሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተቋሙ ማኅበራዊና አገራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አመላክቷል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም፣ በአፍሪካ አስዋንን የገነባችውን ግብጽን ጨምሮ በራሱ አቅም ግድብ የገነባ አገር የለም ሲሉ ጠቅሰዋል። አክለውም ከሕዝባችን በተጨማሪ አሻራቸውን ያኖሩ ወዳጆቻችን በሙሉ የግድቡ ባለቤት ናቸው ብለዋል።

ግብጽና ሱዳንም ምንም አስተዋፅኦ ሳያደርጉ ከግድቡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ዓለም የሚደግፈውን የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ በሚደግፍና መፍትሄ በሚሆን መልኩ እየተገነባ ላለው ግድባችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ ማድረግ ይገባው ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው በዓለም መከሰሳችን ተገቢ አይደለም ነው ያሉት።

በመሆኑም በ11 ዓመታት ውስጥ በቦንድ ሽያጭና በሌሎች ልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ መንገዶች ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ከማኅበረሰቡ መሰብሰቡን አንስተው፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችም ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በጉልበታቸው ሠርተዋል በማለት አብራርተዋል።

ግድቡ የዚህ ትውልድ ገድል፣ የመጪው ደግሞ ታሪክና ቅርስ በመሆኑም ግድቡን ለማጠናቀቅ ከዚህ በኋላ ከሕዝቡ የሚደረገው ድጋፍ ከእስካሁኑ የበለጠ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ዓባይ

መነሻውን ከኢትዮጵያ ደጋማው ክፍል ያደረገው ዓባይ በዓለም ካሉ ወንዞች ረዥሙ ሲሆን፣ ከ6 ሺሕ 600 ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማል።

ወንዙ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የኢኮኖሚ እና ሥነምኅዳር ፋይዳ ጉልህ በመሆኑም፣ ባለፉት 50 ዓመታት በስድስት የተፋሰሱ አገራት ብቻ 25 የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ተሠርተውበታል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አስራ አንድ የዓባይ ተፋሰስ አገራት ያሉ ሲሆን፣ እነሱም ኤርትራ፣ ኬንያ ፣ኡጋንዳ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ብሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ግብፅ ናቸው።

በፈረንጆች 1929 ግብጽና ሱዳን በኢንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ሆነው የዓባይን ውሃ ለመጠቀም ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ የበላይ እንድትሆን ሥልጣን በመስጠት በዓባይ ጉዳይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብትም አጎናጽፏታል።

በ1959 (እ.ኤ.አ) ግብጽና ሱዳን ቀደም ብሎ የተደረሰውን ስምምነት የሚያጠነክር ሌላ ስምምነት በማድረግ 66 በመቶ የወንዙን ውሃ ግብጽ ስትወስድ፣ 22 በመቶውን ሱዳን እንድታገኝ አድርጓል። ቀሪ 12 በመቶው ተኖ የሚያልቅ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት ድርሻ አልነበራትም።

ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ የምትሳተፍበት ትብብር የተመሠረተው በፈረንጆች 1999 ሲሆን፣ በዚህ ጉባኤ ከኤርትራ በስተቀር ዐስሩም የተፋሰሱ አገራት ተካተውበታል።

በቅኝ ገዥዎች ጣልቃ ገብነት ግብጽ ባገኘችው አቅም በተፋሰሱ አገራት የሚገኙ ግድቦችን እስከመቆጣጠር ትደርሳለች። በዚህም ግብጽ በወንዙን ላይ 66 በመቶ የቁጥጥር አቅም ሲኖራት፣ ሱዳን 22 በመቶ አቅም አላት። ኢትዮጵያ ወንዙን የመቆጣጠር ምንም አቅም ሳይኖራት ቆይታለች።

የዓባይ ተፋሰስ ከአፍሪካ ቆዳ ስፋት 10 በመቶ እንደሚይዝ ይነገራል። በዚህ ተፋሰስ 300 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብም ይኖራል። ከዚህ ውስጥ ግብጽ ካላት ጠቅላላ ሕዝብ 95 በመቶ ያህሉ፣ እንዲሁም ሱዳን ከጠቅላላ ሕዝቧ 85 በመቶ የሚሆነው በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ የሚኖር ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ካላት ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ያህል ብቻ በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ የሰፈረ እንደሆነ ይገመታል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

ኢትዮጵያ 85 በመቶ የሚጠጋ የዓባይ ውሃ ድርሻ ቢኖራትም እስካሁን በወንዙ ላይ ግድብ እንደሌላት ይታወቃል። አሁን እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ በተለይ እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም ከወንዙ ላላገኙት ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ተስፋ ይዟል።

በግድቡ 145 ሜትር ከፍታ እና 1 ነጥብ 8 ኪሎሜትር ርዝመትም 74 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ፣ ከኃይል ማመንጫነቱ ባሻገር ለቱሪዝም ትልቅ ፋይዳ ያላቸው 70 የሚደርሱ ሰው ሠራሽ ደሴቶች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸውም፤ ከአምስት ሺሕ በላይ ሜጋ ዋት በማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ ይሆናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here