የየካቲት 12 ሆስፒታል የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሕክምና አሰጣጥ በታካሚዎች ላይ ከፍተኛ እንግልት እያደረሰ ነው ተባለ

0
1646

አዲስ አበባ የሚገኘው የካቲት 12 ሆስፒታል በሚሰጠው በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የሕክምና አገልግሎት የተነሳ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰብን ነው ሲሉ ታካሚዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

የዚህ ሕክምና ስርዓት ተገልጋይ የሆኑት ተመላላሽ ታካሚዎች መሆናቸውን በመግለጽ፣ ሆስፒታሉ ሥራ አቀለልኩኝ ብሎ የጀመረው ዲጂታል ስርዓት የእኛን ሕይወት አክብዶብናል ነው ያሉት።

በዚህም አንድ ተመላላሽ ታካሚ ወረፋ ጠብቆ ከሐኪሙ ጋር ከተገናኘ በኋላ፣ እንደገና መረጃህ ሲስተም ውስጥ ስላልገባ የዲጅታል መታወቂያ ቁጥርህን ንቁ (active) አስደርግ ይባላል። ይህን ተከትሎም ከበፊቱ የባሰ ወረፋ ቆሞ ይጠብቃል ብለዋል።

ስለሆነም፣ ሆስፒታሉ አሠራሩን ባለመፈተሹ እና እንዲሻሻል ባለመሥራቱ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ታካሚ እንደተናገሩት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልም ተመሳሳይ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ይጠቀማል። ነገር ግን እዚያ ታካሚዎች መታወቂያ ቁጥራቸውን ንቁ ማስደረግ አይጠበቅባቸውም። የኢንተርኔት አገልግሎት የለም ተብለውም አይመለሱም ሲሉ ገልጸው፣ የካቲት 12 ሆስፒታል ግን ከጥቁር አንበሳ ቀድሞ የጀመረ ቢሆንም ቴክኖሎጂው አሰራሩ ኹሌ ያው በመሆኑ ለእንግልት ዳርጎናል ነው ያሉት።

‹‹በዚህ ወቀትም ከወትሮ በተለየ መጨናነቅ በዝቷል። አንዳንዱ ጥሎ ሲሄድ ይቅርታ ይጠይቃሉ። ግን ይቅርታ ምን ዋጋ አለው ኹሌም የምንገላታ ከሆነ!›› ሲሉ ተናግረዋል።

ከሠራተኞች መካከልም ከሚሠሩት ይልቅ የሚቆሙት ይበዛሉ ሲሉ ገልጸው፣ ታካሚ ቆሟል እየተንገላታ ነው ብለውም አያስቡም በማለት ነው ቅሬታቸውን ያቀረቡት።

‹‹ካርድ፣ ምርመራ እና ውጤት እንዲሁም መድኃኒት ከዲጅታል ስርዓቱ ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ለኹሉም ሰልፍ እንቆማለን። ይህም ቀኑን ሙሉ እዚያው እንድንውልና አንዳንዴም አገልግሎት ሳናገኝ እንድንመለስ አድርጓል።›› ሲሉም ተደምጠዋል።

በዚህ የተነሳ ጠዋት ወጥቶ ቀኑን ሙሉ ሆስፒታል መዋል ከባድ መሆኑን ያነሱት ታካሚዎቹ፣ ወረፋ ስንጠብቅ ውለንም የኢንተርኔት አገልግሎት የለም ተብለን መጉላላት የተለመደ ነው በማለት አክለዋል።

ሆስፒታሉ የዲጅታል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ኹለት ዓመት ገደማ ሆኖታል የተባለ ሲሆን፣ ከዚህ ይልቅ ግን ቀደም ብሎ በወረቀት ካርድ አገልግሎት ይሰጥ በነበረበት ወቅት የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ እንደነበር ተነስቷል።

በተለይ የተመላላሽ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከኢንተርኔት ጋር የተገናኘ በመሆኑ ለታካሚዎች አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ጭራሽ ብሶበታል ነው የተባለው።

የኢንተርኔት አገልግሎት ቢኖርም፣ መረጃ አልተላከም በማለት ታካሚዎች የሚንገላቱ በመሆኑ ኢንተርኔት ቢኖርም ባይኖርም ችግሩ የተለመደ መሆኑ ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ የቀረቡ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ከየካቲት 12 ሆስፒታል ማብራሪያ ፍለጋ ስልክ በተደጋጋሚ ብትደውልም ሳይሳካ ቀርቷል።

በሕክምና ተቋማት ውስጥ ወደ ወረቀት አልባ ቴክኖሎጂዎች የሚደረጉ ሽግግሮች፣ የመረጃ ተደራሽነትን ለማፋጠን እና ለማቅለል እንዲሁም የአገልጋዮችን እና የተገልጋዮችን ጉልበት፣ ጊዜና ወጪ ለመቀነስ ዓይነተኛ ሚና አላቸው ተብሎ ይታመናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here