ከወለጋ መከላከያ ለቆ በመውጣቱ በአንፊሌ ወረዳ የ29 ቀበሌ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነገረ

0
1223

ሕወሓት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ዳግም የቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የመከላከያ ኃይል ቦታውን ለቆ በመውጣቱ በቄለም ወለጋ ዞን አንፊሌ ወረዳ የ29 ቀበሌ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ ሰምታለች።

ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ ምንጭ፤ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን እና በጋምቤላ ክልል አዋሳኝ በሆነው አንፊሌ ወረዳ ስር በሚገኙ 29 ቀበሌዎች የነበሩ ነዋሪዎች እስከዛሬ ኦነግ ሸኔ ጥቃት እንዳያደርስባቸው በመከላከያ ከለላ ሲኖሩ ነበር ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሕወሓት ሰሞኑን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ መከላከያ ከለላውን ትቶ ወደ ጦርነት ግንባር በመትመሙ፣ ነዋሪዎቹ ኦነግ ሸኔ ጥቃት ያደርስብናል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ለመፈናቀል ተገደዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ አሁን የሚገኙት ከጋምቤላ ክልል 68 ገደማ ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አንፊሌ ወረዳ ሙጊ ከተማ ነው ብለዋል።

ተፈቃዮቹ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በተወሰነ መልኩ ከስጋት ነጻ ሆነን ስንኖር የነበረው መከላከያ በወረዳው በመኖሩ ነበር ብለዋል። አሁን ግን በወረዳው የነበረ የአማራ ተወላጅ ሁሉ ባደረበት ስጋት ወደ ሙጊ ከተማ መፈናቀሉን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

አክለውም፣ ‹‹መከላከያ ቦታውን ለቆ ወደ ግንባር ከሄደ በኋላ ኦነግ ሸኔ ያደረሰው ጥቃት የለም። ብቻ ግን በወረዳው የሚገኙት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ብቻ ስለሆኑ ሕዝቡ ስጋት ስላደረበት ሸሽቷል›› ነው ያሉት።

ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ በርካታ ተፈናቃዮች ከፊሎቹ በሙጊ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ዘመድ ያለው ተጠግቶ፤ የሌለው ደግሞ ውሎና አዳሩ በየጥጋጥጉ ሆኗል ሲሉ አብራርተዋል።

ተፈናቃዮቹ እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ ያደረገልን የመንግሥት አካል የለም ያሉ ሲሆን፣ የእርዳታ ድርጅቶች እንዲሁም መንግሥት ያሉበትን ኹኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ተማጽነዋል።

አንዳንዶቹ ተፈናቃዮች ጋምቤላ ክልል ወደሚገኙ ወዳጅ ዘመድ ለመሄድ ቢያስቡም ከአንፊሌ ወረዳ ወደ ጋምቤላ ክልል የሚወስደው ድልድይ በመሰበሩ መሻገሪያ ማጣታቸው ሌላኛው ችግር መሆኑን አንስተዋል።

ከተፈናቃዮች መካከል ሕጻናት፤ የሚያጠቡ እናቶች፤ ነፍሰጡሮች እንዲሁም አቅመ ደካሞች ይገኙበታል የተባለ ሲሆን፤ ምንም እንኳ የክረምቱ ወራት በመገባደድ ላይ ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚዘንበውን ዝናብ እና የክረምቱን ቁር መቋቋም እንደከበዳቸው በማማረር ገልጸዋል።

በሰሜኑ በኩል ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት ግምት ውስጥ እናስገባለን ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ከኦነግ ጥቃት ከለላ ሆኗቸው የኖረው የመከላከያ ኃይል ወደ ግንባር መሄዱን ባይጠሉትም፤ ስጋት ባለባቸው የአንፊሌ ወረዳ ያለው ትንሽ ብቻ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በመሆኑ ቢያንስ የፌዴራል ፖሊስ እንዲጨመርላቸው ጠይቀዋል።

ከአንፊሌ ወረዳ ወደ ጋምቤላ ክልል ለመጓጓዝ የሚያገለግለው ዋና መንገድም በሚመለከተው አካል ጥገና ቢደረግለት፣ የተጋረጠባቸውን ችግር በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሊያቀልላቸው እንደሚችል ገልጸዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን የጸጥታ አስተዳደር ተሰማ ዋሪዮ ስለተፈጠረው ችግር እንዲያብራሩ ከአዲስ ማለዳ ጥያቄ ቢቀርባላቸውም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወቅቶች በንጹሐን ላይ ጭፍጨፋ ሲያደረግ ቢቆይም፤ በተለይም ከነሐሴ ወር ጀምሮ የአገር መከላከያ ሠራዊት በቄለም ወለጋ ሲያደርግ በቆየው ዘመቻ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ እንደነበር ሲገለጽ መቆየቱ የሚታወስ ነው። አሁን ግን ነዋሪው ወደ ቀደመ ስጋቱ ተመልሷል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here