በሰባት ክልሎች የኅብረት ሥራ ማኅበር አባላት ለሚመረቱ ዘጠኝ የግብርና ምርቶች የምርት መለያ ሥያሜ (ብራንድ) መስጠቱን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታውቋል።
የምርት ሥያሜ (ብራንድ) የተሰጣቸው የአፋር ቴምር፣ የሀላባ በርበሬ፣ የአፍዴራ ጨው፣ የአፍዴራ ነጭ ፍየል፣ የቦንጋ በግ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለውዝ፣ የሀረሪ አምባ ንጉሥ ማንጎ፣ የመቂ ባቱ ሽንኩርት እና የሶማሌ ቀላፎ ሽንኩርት ናቸው። የምርት ሥያሜ የተሰጣቸውን ምርቶች በከተሞች ታላላቅ አደባባዮች ላይ እንዲተዋወቁ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ኮሚሽኑ እንዳለው፣ ሥያሜው ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ገበያም ተፈላጊ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም ምርቶቹ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙና ገበያ በማረጋጋት ረገድ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ያስችላል ነው ያለው። የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ሰኔ 29/2014 የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የጨንቻ አፕል እና የአዊ ድንች የምርት ሥያሜን (ብራንድ) ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014


