በ2015 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት በልዩ ሁኔታ በባንኮች በኩል የውጭ ምንዛሬ ብድር እንደሚቀርብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
የወጪ ንግድ ምርቱ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ከፍተኛ እድገት ያሳየ ሲሆን፣ ለእድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ቡና ዋናው ነው ተብሏል።
ብሔራዊ ባንክ በወጪ ንግድ ዘርፉ ለተገኘው ውጤት አርሶ አደሮች፣ ላኪዎችና የፋይናንስ ተቋማት የክልልና የፌዴራል አመራሮች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብሏል።
ቡናን ጨምሮ በአጠቃላይ ከወጪ ንግድ በ2014 በጀት ዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ባንኩ አውስቷል። በዚህ በጀት ዓመትም አፈጻጸሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቡናን ጨምሮ በወጪ ንግድ ዘርፉ ለተሰማሩ ተቋማት በባንኮች በኩል የተለየ ብድር ይቀርባል የተባለ ሲሆን፣ ይህም የተደረገው የወጪ ንግድ ዘርፉ ለአገሪቱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በመሆኑ ነው ተብሏል።
በስምንቱ ዓመታት ከቡና ምርት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱና ከ56 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸው ተነግሯል።
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላከ 300 ሺሕ ቶን በላይ ቡና 1 ነጥብ 42 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ይታወቃል።
ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014



