ብልፅግና ፓርቲ በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የሚንቀሳቀሰው የክልልና የፌዴራል የምክር ቤት አባል ውክልናን ለመንጠቅ በክስ ሂደት ላይ መሆኑን የቁጫ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
የፓርቲው ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ደቡብ ክልል ላለው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ውክልና ሰጥቶ፣ የጋሞ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ነው ክስ መስርቷል የተባለው።
ይህም የሆነው በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በአካባቢው ምርጫው እንዲደገም በፍርድ ቤት ካስወሰነ በኋላ፣ በእጩዎቼ ላይ በደል እየደረሰብኝ ነው በማለት ራሱን ማግለሉን ተከትሎ፣ ምርጫ ቦርድ በድጋሚ ምርጫ ለማካሄድ እንደማይችል በመግለጽ ምርጫው ሳይደረግ በመቅረቱ መሆኑ ተመላክቷል።
በዚህም ድጋሚ ምርጫ ሊካሄድ ነው ሲባል የክልልና የዞን ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በአካባቢው ችግር ሲፈጥሩ ነበር የተባለ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ምርጫው አልተደረገም በሚል ምርጫ ቦርድን ከሰዋል ነው የተባለው።
የክሱ ዓላማም የክልልና የፌዴራል ምክር ቤት ወንበር ያገኙ አራት የቁጫ ማኅበረሰብ ተወካዮችን ለማንሳት ነው ሲሉ፣ ‹‹ይህን በመናገሬ የሚደርስብኝን አላውቅም›› በማለት ለደኅንነታቸው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቁጫ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር ተናግረዋል።
ሆኖም ክሱን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎት፣ ብልፅግና ፓርቲ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የቁጫ ማኅበረሰብ በአካባቢው አስተዳደር በተለይም የጠራ አመለካከት በሌላቸው የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ነው ያሉት አመራሩ፣ ለአብነትም ፓርቲውን መርጣችኋል በሚል የአካባቢው አስተዳደር እስከ አምስት ሺሕ ብር እያስከፈላቸው ነው ብለዋል።
ሞተራቸውን ተነጥቀው የተሰደዱ በርካታ ወጣቶች ከመኖራቸውም በላይ፣ ምግብና ሽንት ቤት የመሳሰሉ አገልግሎት የማግኘት መብቶችን ተነፍገው ብዙዎች እስር ቤት መታጎራቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ገነነ ገደቡ (ረ/ፕ) በመጋቢት ወር የመረጣቸውን ሕዝብ ለማወያየት ወደ አካባቢው ቢያቀኑም እገታና የመግደል ሙከራ ተፈጽሞባቸዋል ተብሏል።
ባለፈው ነሐሴ 19/2014 ላይም የክልል ምክር ቤት ተወካዮች ከሕዝቡ ጋር ለመገናኘት በሄዱበት ወቅት በጠራራ ፀሐይ መኪናቸው እንዳልነበር ተደርጎ በድንጋይ ተወግሮ ከሞት አምልጠዋል። ወጋሪዎቹም ዱርዬዎች ሳይሆኑ ሹመት ተሰጥቷቸው የመንግሥትን ሥልጣን እየመሩ ያሉ የአካባቢው አመራሮች መሆናቸውን ነው ፓርቲው የገለጸው።
በተወካዮች ላይ የደረሰው በደል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ቢሆንም፣ አፈ ጉባኤው (ታገሰ ጫፎ) ጉዳዩን አውቀዋለሁ በማለት አድበስብሰው አልፈውታል የሚል ቅሬታ ቀርቦባቸዋል።
‹‹እርሳቸውን እጅግ እናከብራቸዋለን›› ሲሉ የተናገሩት የቁጫ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር፣ አሁንም በቁጫ ማኅበረሰብ ላይ ጭቆናን የሚያደርሰው አመራር ብሔር አባል ስለሆኑ እርሳቸውም እጃቸው እንዳለበት እናምናለን ነው ያሉት።
አክለውም፣ ‹‹ሌላ አካባቢ የሕዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር መወያየት አልቻልንም በማለት በሚዲያ ሲያስተጋቡ፣ የእርሳቸው አካባቢ ሲሆን ግን አይነገርም። ታች ድረስ ወርደው ‹ይህ ግለሰብ የፖለቲካ አመለካከቱ እንዲህ ነው…ለምን ቀጠራችሁት?› የሚሉ ናቸው›› ሲሉ ተደምጠዋል።
‹‹የቁጫ ማኅበረሰብ በ2010 ለውጥ ሲመጣ፣ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ እፈታለሁ ብሎ በአደባባይ በመናገሩና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹አሸባሪው መንግሥት ነበር› ብለው ሲናገሩ፣ መሳደዳችንና መታሰራችን ቆሞ ጥያቄያችን ይፈታል የሚል እምነት ነበረን። ይሁን እንጂ፣ በዚህ ወቅት ድጋሚ ምርጫ ለመወዳደር ቀርቶ ኦክስጅን በእነሱ እጅ ቢኖር ኖሮ መተንፈስ አንችልም ነበር›› ብለዋል።
የቁጫ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ድጋሚ ምርጫ ቢደረግም አሁን ያለው ሁኔታ ፍጹም አፈና በመሆኑ መወዳደር እንደማይቻለው ገልጾ፣ ቅድሚያ ማኅበረሰቡ እንደዜጋ የመኖር መብቱን እንዲያገኝ ጠይቋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014



