አሊያንስ የከተማ አውቶብስ ከእጥፍ በላይ እያስከፈላቸው መሆኑን ተሳፋሪዎች ገለጹ

0
1540

አሊያንስ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ሥራ ከጀመረ ከወራት ወዲህ ከእጥፍ በላይ ስለሚያስከፍል ላልተፈለገ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን ተሳፋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በ2 ሺሕ 500 ባለ አክሲዮኖች አማካኝነት የተቋቋመው የብዙኅን ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢው አሊያንስ አውቶብስ፤ በ2009 ከንግድ ባንክ በተገኘ ብድር 100 አውቶብሶችን ገዝቶ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር። ሆኖም ግን እዳውን መክፈል ባለመቻሉ ባንኩ ንብረቶቹን ለጨረታ ስላቀረበ አገልግሎቱ ከተቋረጠ ከኹለት ዓመታት በላይ አስቆጥሮ ቆይቶ፤ በ2014 ሥራ ጀምሯል።

ነገር ግን ተሳፋሪዎች አሊያምስ አውቶብሶች፣ ሌሎች የብዙኅን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶች ከሚያስከፍሉት ዋጋ ከእጥፍ በላይ በመጠየቁ ለወጪ እየተዳረጉ በመሆኑ ቅሬታ አድሮባቸዋል።

ዓለማየሁ ግርማ ሁሌም ከአባዶ ወደ መገናኛ ተመላላሽ የቀን ጥበቃ ሠራተኛ ናቸው። ‹‹አሊያንስ የከተማ አውቶብስ ሥራ ከጀመረ ወዲህ ለከፍተኛ ወጭ እየተዳረኩ ነው›› ብለዋል። በተያያዘም፤ አንበሳና ሸገር የብዙኅን ትራንስፖት አገልግሎት በሚሰጡበት ሰዓትና ቦታ አሊያንስ አውቶብስ ቀድሞ በመቆምና ተራ በመያዝ ከእጥፍ በላይ ያስከፍላል በማለት አማረዋል።

በሸገር የብዙኀን ማመላለሻ ትራንስፖርት በወር 240 ብር ያወጡ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን በወር 600 ብር ለማውጣት ግድ እንደሚላቸው ነው የገለጹት። በሸገር አውቶብስ ለአንድ ጉዞ 4 ብር፤ ለደርሶ መለስ በቀን 8 ብር ያወጡ የነበረ ሲሆን፤ በአሊያንስ አውቶብስ ሲጓዙ ግን ለአንድ ጉዞ 10 ብር፤ ለደርሶ መልስ በቀን 20 ብር ያወጣሉ።

‹‹በእርግጥ በአሊያንስ አውቶብስ መጓዝ አለባችሁ ተብለን አልተገደድንም›› ያሉት ዓለማየሁ፤ ሌሎች የብዙኅን ትራንስፖርት ሰጪ አውቶብሶች ቀድመው መገኘት ስለማይችሉ ሰልፍ የያዘ ሰው በአሊያንስ ለመጓዝ ይገደዳል ብለዋል።

ሌላኛዋ ከመገናኛ ካራ ተመላላሽ ነኝ ያሉት መሠረት በለጠ ችግሩ የተከሰተው ‹‹ሆን ተብሎ ሌሎች አውቶብሶች መጫን ባለባቸው ሰዓት ወደኋላ እንዲዘገዩ ተደርጎ አሊያንስ ቀድሞ ስለሚመጣ ነው›› ሲሉ የዓለማየሁን ሐሳብ ይጋራሉ።

‹‹ለምሳሌ ሸገር አውቶብስ ኹለት ሰዓት ከመገናኛ ወደ አባዶ የሚጭን ከሆነ፤ ቀድሞ አሊያንስ አውቶብስ ለመጫን እንዲመጣ ይደረግና ሸገር ወደ ኋላ ይዘገያል። ሸገር ደግሞ ከኹለት ሰዓት በኋላ አይጭንም። ስለዚህ አምሽተን ለታክሲ ይበልጥ ላለማውጣት ሳንወድ በግድ በአሊያንስ ለመሳፈር እንገደዳለን›› ሲሉ አብራርተዋል።

‹‹ቅሬታ ስናቀርብ አሊያንስ አውቶብስ ሥራ አቁሞ ስለቆየ መሥራት አለበት ይሉናል›› ያሉት መሠረት፤ አውቶብሱ ቆሞ የኖረበትን ጊዜ የሚያካክሰው በኑሮ ውድነት ከተመናመነው የሕዝብ ኪስ መሆን የለበትም የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።

አክለውም፣ ‹‹ሹፌሮቹ ሰውን ከልክ በላይ በመጫን ሆን ብለው ፍሬን ያዝ ለቀቅ በማድረግ ሰውን እየጨፈለቁ ያሸጋሽጋሉ። ዕቃ እንጂ ሰው የጫኑ አይመስላቸውም።›› ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ አሊያንስ እንደሌሎቹ አውቶብሶች ትኬት አለመቆረጡ ሹፌሮቹ ዋጋውን እንዳሻቸው እንዲያሾሩት አድርጓል ያሉ ሲሆን፤ አዲስ ማለዳም ትኬት እንደማይቆረጥ በቦታው ተገኝታ አረጋግጣለች።

በሰሜኑ ጦርነት አውቶብሶች ለግዳጅ መውጣታቸውን እንደምክንያት በማንሳት የታክሲ ሹፌሮችም ከተለመደው የተለየ ዋጋ የሚጠይቁ መሆኑም ቅሬታ አሳድሯል።

ከ02 ወደ ካራ ለመጓዝ እስከዛሬ ሲከፈል የነበረው 10 ብር እንደነበርና ሰሞኑን ግን 20 ብር እየተጠየቀ መሆኑን ተሳፋሪዎቹ ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ በቦታው ባደረገችው ቅኝት የታክሲ ሾፌሮቹ የ10 ብር ታሪፍ 20 ብር እንደሚያስከፍሉ አረጋግጣለች።

ክፍያውን የተቃወሙ ተሳፋሪዎችን መንገድ ላይ እንዲወርዱ የተደረጉ ሲሆን፤ ሹፌሮቹም ለምን ተብለው ሲጠየቁ ‹‹አሁን እኮ አውቶብሱ ሁሉ ለግዳጅ ወጥቷል፤ አንከፍልም ካሉ በእግራቸው ይሄዳሉ›› ነው ያሉት።

ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ከአሊያንስ አውቶብስ ኃላፊዎች ለማግኘት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here