የሚመጣ እርዳታ በመንግሥት በኩል ብቻ እንዲሰጥ ከተወሰነ ወዲህ እየደረሰን አይደለም ሲሉ ተፈናቃዮች ተናገሩ

0
875

በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች ከለጋሾች የሚቀርበው የእርዳታ ቁሳቁስ በከተማ አስተዳደሩ መጋዘን እንዲቀመጥና ለተፈናቃዮች በመንግሥት በኩል እንዲሰጥ ከተወሰነ ወዲህ እየደረሰን አይደለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ተፈናቃዮቹ ሲገልጹ፣ ‹‹በፊት እርዳታ የሚሰጡ ተቋማትና ግለሰቦች በቀጥታ መጥተው አሰልፈው ይሰጡን ነበር። ጊዜ ከሌላቸውም ለተፈናቃዮች አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ ሰጥተው፣ ዐቢይ ኮሚቴውም ለንዑስ ኮሚቴው በማስረከብ ለእያንዳንዱ ተፈናቃይ ይደርሰው ነበር›› ብለዋል።

‹‹ነገር ግን፣ በቅርቡ ማንኛውም ለተፈናቃዮች የሚቀርብ እርዳታ መጀመሪያ ወደ ከተማ አስተዳደሩ መጋዘን ገብቶ፣ ከዚያም በመንግሥት አካላት በኩል እንዲሰጠን ከተወሰነ ወዲህ ምንም ዓይነት እርዳታ አግኝተን አናውቅም።›› ነው ያሉት።

የሚቀርበው እርዳታ ወደ መጋዘን እንዲገባ የተደረገበትን ምክንያት በደንብ ባናውቅም፣ ከከተማ አስተዳደሩ የሰማነው ግን፣ ለተፈናቃዩ የሚቀርበው እርዳታ ከበቂ በላይ ስለሆነና በከተማው ብዙ የሚራብ ማኅበረሰብ በመኖሩ ለማገዝ የሚል ነው ሲሉም አክለዋል።

ይሁን እንጂ፣ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ አሰቃቂ ረሃብ መኖሩን በማንሳት፣ በተለይ አሁንም ድረስ እየመጡ ላሉ ወገኖች የሚሰጣቸው ነገር ባለመኖሩ ከባድ ችግር እያስተናገዱ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ቻይና ካምፕ ተብሎ በሚጠራውና በአሁኑ ጊዜ 16 ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች አሉበት በተባለው መጠለያ ጣቢያ ያሉ የተፈናቃዮች አስተባባሪ እንደተናገሩት፣ በዚህ ወቅት የሚቀርበው የእርዳታ መጠን ከተፈናቃዩ ቁጥር ጋር የማይገናኝ ነው።

የእርዳታ ቁሳቁሱ ወደ ከተማው መጋዘን ይግባ ከተባለ ወዲህ ብዙ ነገር ገብቷል ሲባል እንሰማለን ያሉት አስተባባሪው፣ ለእኛ ግን ይህ ነው የሚባል የደረሰን ነገር የለም ብለዋል።

ለአዲስ ዓመት ማክበሪያ ተብሎ የገባ ድጋፍም ሆነ ዝግጅት እንደሌለም ነው ያመላከቱት።

‹‹ቀደም ብለው የገቡት ዱቄት አላቸው። አሁን እየገቡ ያሉት ግን ምንም ስለማይሰጣቸው ችግሩ ከባድ ነው።›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹እርስ በእርስ በመረዳዳት፣ አሁን ለሚመጡት እንጀራ በመለመን እንዲሁም የከተማው ማኅበረሰብ በሚያቀርብልን የእለት ጉርስ ድጋፍ ነው እየኖርን ያለነው።›› ሲሉ ተደምጠዋል።

በየቀኑ ቤተሰቦቻቸውን የያዙ አባወራዎች እንደሚመጡ በመጥቀስም፣ በመጠለያ ቦታ ጥበት አዲስ የሚመጡ ተፈናቃዮች ዝናብ ላይ የሚያድሩ እንዲሁም በፍራሽ እጥረት መሬት ላይ የሚተኙ መኖራቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ብሎ የቤት ኪራይ እየተከፈላቸው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አሁን ላይ የሚከፍልላቸው አጥተው ወደ መጠለያ ጣቢያዎች እየተመለሱ እንደሚገኙ ብሎም፣ በተለይ ከምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ አካባቢዎች ተፈናቃለው የመጡ ዜጎች ወደ ቀያቸው የመመለስ ተስፋ እንደሌላቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ወይንሸት ተብሎ በሚጠራው መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሌላኛው አስተባባሪ፣ ከዚህ በፊት ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ያሉትን ችግሮች በተመለከት መረጃ ሰጥተን ከከተማው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጫናዎች ደርሰውብናል በማለት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። መታወቅ ያለባቸው በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የሥነ ሕዝብ ባለሙያ፣ እንዲሁም የተፈናቃዮች አስተባባሪ አንተነህ ገብረእግዚአብሔር፣ የሚቀርቡ የእርዳታ ቁሳቁሶች በመጠለያ ጣቢዎች እንደሚራገፍ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በመሆኑም፣ መጋዘን እንኳን የለንም በማለት ተፈናቃዮች ያቀረቡትን ቅሬታ ትክክል አለመሆኑን ገልጸው፣ ድርጅቶች መጋዘን አስገብተው የገቢ ደረሰኝ ሲጠይቁንም እንኳን መጋዘን ስለሌለንና ብንፈልግም ሕጋዊ አሠራር ባለመኖሩ አንሰጠም ነው ያሉት። ይህን የሚፈልጉ አካላትም በከተማ አስተዳደሩ ሳይሆን በዞኑ ነው የሚስተናገዱት ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ በዚህ ወቅት የምግብ እርዳታ እየተመናመነ ሄዶ ባዶ ሆኗል ካሉ በኋላ፣ ‹‹ለክልልና ለፌዴራል መንግሥት ብንገልጽም ሊፈታ አልቻለም። ተፈናቃዮችም ራበን እያሉ ቢሮ ድረስ ይመጣሉ። በዓልን እንዴት እንደምናውላቸውም ተቸግረናል። የምግብ አቅርቦት ጉዳዩ አሳሳቢና ከአቅማችን በላይ ነው›› ብለዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋና ምሥራቅ ወለጋ ዞኖች ብቻ ተፈናቅለው የመጡት ተቆጥረው፣ በስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ 23 ሺሕ ገደማ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here