ደሴና ሀራ ከተማ አንድ ዳቦ 30 ብር እየተሸጠ መሆኑ ተሰማ

0
1768

ባለሥልጣናቱ ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እያስገደዱ ነው ተብሏል

በአማራ ክልል ደሴ እና ሀራ ከተማ አንድ ዳቦ 30 ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ ተጠቃሚዎቹን በማነጋገር አረጋግጣለች።

ሰሞኑን ለተስተዋለው የዋጋ ንረት መከሰት ዋነኛ ምክንያት ሕወሓት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለሦስተኛ ጊዜ በቀሰቀሰው ጦርነት ቀጠና ያሉ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ከተሞች በመፈናቀላቸው ነው።

ተፈናቃዮቹ፤ ‹‹በሀራ እና በደሴ ከተማ አንድ ዳቦ 30 ብር እየገዛን ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ከወርቄ፤ ከቆቦ፤ ከጎብዬ፤ ከሮቢት እንዲሁም ከወልዲያ ወደ አጎራባች ከተሞች ያቀኑት ተፈናቃዮቹ፤ ሀራ እና ደሴ ከተማ ከዚህ በፊት 5 ብር ሲሸጥ የነበረው ዳቦ ሰሞኑን እስከ 30 ብር እየተሸጠ መሆኑን መስክረዋል።

‹‹በመፈናቀል ላይ ዳቦ በልቶ ማደር የቅንጦት ሆኖብናል›› የሚሉት ስሞታ አቅራቢዎቹ፤ ዋጋው 30 ብር የሆነውን ዳቦ በሰላሙ ወቅት ሲሸጥ የነበረው ከ4 እስከ 5 ብር ድረስ እንደነበር ባደረጉት ማጣራት ማወቃቸውን ገልጸዋል።

እንደ ገለጻው ከሆነ፤ የዋጋ ጭማሬው ከወትሮው በተለየ መልኩ የተከሰተው ዳቦ ላይ ብቻ ሳይሆን በፍራፍሬ፤ በመጠጥ እና በትራንስፖርት ታሪፍ ጭምርም ነው።

ተፈናቃዮቹ፤ በተለይም በሀራ ከተማ በጉዞ ላይ በነበሩበት ወቅት ዳቦ በመጥፋቱ በዚህ ዋጋም መግዛት የቻሉት ጥቂቶች እንደሆኑ አስታውስው፤ ሦስት ፍሬ ሙዝ 30 ብር ገዝተን ተመግበናል ያሉም አሉ።

በተጨማሪም በሀራ፤ በወልደያ፤ በመርሳ እንዲሁም በደሴ ከተማ እስከዛሬ 12 ብር ሲሸጥ የነበረውን አንድ የታሸገ ውሃ ከ40 እስከ 50 ብር እንዲሁም 20 ብር ሲሸጥ የነበረውን ፈሳሽ ማንጎ 50 ብር እንደገዙም አስታውሰዋል።

በተያያዘም፤ 3 ብር ሲሸጥ የነበረ ሻይ ወደ 10 ብር ከፍ ማለቱን ተፈናቃዮቹ ሳያነሱ አላለፉም።

በሌላ በኩል፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት አስገድደው ወደ ጠርነቱ ቀጠና እየመለሷቸው መሆኑን አዲስ ማለዳ በኮምቦልቻ ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ሰምታለች።

ከወርቄ ሃራ፤ ከቆቦ እና ከወልደያ መርሳ እንዲሁም ከወልዲያና ከመርሳ ወደ ኮምቦልቻ እና ደሴ ለቀናት በእግራችን ተጉዘን ነው የመጣነው ብለው፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹ውጡ ወደየቤታችሁ ሂዱ›› በማለት እየወተወቱን ነው ሲሉ አማረዋል።

ባሳለፍነው ጳጉሜ 2/2014 የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከሌላ ቦታ የመጡ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አውጇል የተባለ ሲሆን፤ የሰሜን ወሎ መታወቂያ ይዘው የተገኙ ሰዎች እንዲመለሱ እየተገደዱ መሆኑ ተመላክቷል።

የትራንስፖርት ዋጋ ከወልደያ ደሴ ከ2 ሺሕ 500 እስከ 3 ሺሕ ብር መናሩም ተጠቅሷል። ተሳፋሪዎቹ፤ በሰላሙ ወቅት ታሪፉ 200 ብር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን በአንድ ጊዜ እስከ 2 ሺሕ 800 ብር ጭማሪ ተደርጓበታል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ውቤ አጽናፉ በበኩላቸው፣ በታሪፍ በኩል የተነሳው ቅሬታ ስምሪትን እንደሚመለከት አቅጣጫ ሰጥተዋል። በጥቆማው መሠረት ይመለከታቸዋል የተባሉት አካል ስብስባ በመሆናቸው ቀጠሮ ቢሰጡም በድጋሚ ሲደወል ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እያሱ መስፍን እንዲሁ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምላሽ መስጠት አልቻሉም።

የመርሳ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ፣ ከጳጉሜ 1/2014 ጀምሮ ከተለመደው በተለየ መልኩ አላግባብ የሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ ማስተካከያ ካላደረጉ ደግሞ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን አሳውቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here