የሥርዓተ ትምህርት ነገር!

0
2995

‹መማር ያስከብራል፤ አገርን ያኮራል› የሚለው ብሂል፤ ትምህርት ለግል አእምሮአዊ እድገት ብቻ ሳይሆን ለአገርም ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው ያመላክታል። አገር በትምህርት ውስጥ የሚያልፉ ዜጎቿ በጨመሩ ቁጥር፣ ምክንያታዊ ትውልድን እያፈራች እድገትና ልማቷን የማፋጠን እድሏ እየጨመረ ይሄዳል። እነዚህ ዜጎቿ ችግሯን የሚሸሹ፣ ሲከፋም ችግር የሚፈጥሩባት ሳይሆን በቅርብ ሆነው መፍትሄ የሚሰጡና የችግርን መፍቻ ቁልፍ የታጠቁ ናቸው።

ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ዜጎች ለአገር ሸክም ይሆናሉ። የተሠራን የሚያጠፋና የሚያወድም ትውልድም ይፈጠራል። ለዚህ ታድያ ቁልፍ መሠረቱ የትምህርት ሥርዓት ነው። ብዙ አገራት የትምህርት ስርዓትን እንደ ዱላ ቅብብል እያሻገሩ ብሎም እያሻሻሉ ማስቀጠል ሲችሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ከፖለቲካ ለውጥ ጋር የቀደመውን እየጣሉ፣ አዲስ መሠረት ለመጣል እየሞከሩ፣ እንደ አዲስ እየጀመሩ ይሄዳሉ። የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ያላት የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓትም እንዲህ ባለ መልክ ሲጓዝ ቆይቷል።

የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ ባለሞያዎችን በማነጋገርና ጥናቶችን በማጣቀስ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ትምህርት ለሰው ልጆች ኑሮ ቅልጥፍና፣ ለአገራት ዕድገትና ልማት፣ ባህልንና እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገልግል ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል። የዓለም ተምሳሌቱ የመጀመሪያው ጥቁር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት ስለትምህርት ሲናገሩ፣ “ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ልትጠቀምበት የምትችለው በጣም ኃይለኛ መሣሪያ ነው” ብለው ነበር።

ስለ ትምህርት ሲነሳ ይህ የኔልሰን ማንዴላ ንግግር ብዙውን ጊዜ እንደ እነ ዩኔስኮ እና ተመድ በመሳሰሉ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል። ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ቁልፍ መሣሪያ ነው የሚለውን መርህ የዓለም አገራት የሚስማሙበት ቢሆንም፣ የዓለም አገራት በሙሉ ትምህርትን ለለውጥ ተጠቅመውታል ለማለት ብዙም አያስደፍርም።

ትምህርት የአንድን ማኅበረሰብ እሴቶች እና የተከማቸ እውቀት ማስተላለፊያ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል በትምህርት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ከዚህ አንጻር የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ማኅበረሰብነት (socialization) ከሚሉት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ይገልጻሉ። ማኅበራዊነት የኅብረተሰቡን ደንቦች እና ርዕዮተ ዓለሞች ወደ ውስጥ የማስገባት ሂደት ሲሆን፣ ማኅበራዊነት መማርን እና ማስተማርን እንደሚያካትት አጥኚዎች ይጠቅሳሉ።

አንድ ማኅበረሰብ ቀስ በቀስ ለትምህርት የበለጠ ቦታ ሲሰጥ፣ አጠቃላይ የትምህርት ዓላማዎችን፣ ይዘቶችን፣ አደረጃጀቶችን እና ስልቶችን ለመንደፍ እንደሚሞክርም ጥናቶች ያመላክታሉ።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ትምህርትን በአግባቡ ለለውጥ ካልተጠቀሙ አገራት መካከል አንዷ ስለመሆኗ በትምህርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ምሁራን ሲገልጹ ይደመጣሉ። ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚያነሱት የኢትዮጵያ ትምህርት ከስርዓቱ እስከ ትግበራው ከፖለቲካ ነጻ አለመሆኑን እና የትምህርት ጥራት በብዙ መመዘኛ የተዘነጋ መሆኑን በማንሳት ነው።

ትምህርት ለእውቀትና ባህል ሽግግር፣ እንዲሁም እውቀትን ለማሻሻልና ዴሞክራሲን ለማዳበር የሚጠቅም አቅም ያለው መሣሪያ መሆኑ ላይ ብዙ ልዩነት ባይታይም፣ ተግባራዊነቱ ላይ ብዙ ጥያቄ ከሚነሱባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። የኢትዮጵያ ትምህርት ከሥርዓቱ እስከ መዋቅሩ፣ ከትምህርት ቤቶች እስከ መምህራን ጥያቄ የሚነሳበት ነው።

ትምህርት እና ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ከባሕላዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር፣ በዋናነት ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተያያዘ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። እ.አ.አ በ2015 በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ  የትምህርት ኮንፈረንስ ላይ “የኢትዮጵያ የሥርዓተ ትምህርት መሠረት፣ ታሪካዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ ሳይኮሎጂካል እና ሶሺዮሎጂካል ዕይታዎች” በሚል ርዕስ በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ በነበሩት አወቀ ሺሺጉ የቀረበ ጥናት እንደሚያስረዳው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት እሳቤ የተጀመረው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ነው።

ጥናቱ ከሆነ እ.አ.አ በ1908 ዘመናዊ ትምህርት ወደ ኢትዮጰያ እስከገባበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓትን በስርዓቷ አቅፋ ይዛ እንደነበር ያትታል። ዘመናዊ ትምህርትን ያስተዋወቁት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ባጋጠማት የማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት ዘመናዊ ትምህርትን በ1908 ወደ ኢትዮጵያ ማምጣታቸውን ጥናቱ ይብራራል።

ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ እ.አ.አ 1908 በአፄ ምኒልክ ሲጀመር፣ ዓላማውም የምዕራባውያንን ሐሳቦች እና ዘመናዊነትን የመማር ፍላጎት፣ የመንግሥት ባንክ ምሥረታ፣ የድልድይ ግንባታ፣ የሆስፒታሎች፣ የሆቴሎችና የባቡር ሀዲድ ግንባታ፣ የፖስታ አገልግሎት፣ በስልክ እና ወዘተ የመሳሰሉ ፈጠራዎች አስፈላጊነት በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንደነበር ጥናቱ ያስረዳል።

የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የተመራው በግብፃዊ ፕሮፌሰር የነበረ ሲሆን፣ በትምህርት ቤቱ ወደ 150 የሚጠጉ ብቸኛ ወንድ ልጆች ይማሩበት ነበር። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የመኳንንት ልጆች ሲሆኑ፣ ከተማሪዎቹ  መካከል ልጅ ኢያሱ እና ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለሥላሴ) እንደሚገኙበት ጥናቱ ያረጋግጣል።

ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በተስፋፋበት በዚያ ወቅት ሥርዓተ ትምህርቱ እንደ ሳይንስ፣ ሂሳብ፣ ሥዕል፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የቤት አስተዳደርን ያጠቃልል ነበር።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የትምህርት ሚኒስትር የተሾመው በልጅ ኢያሱ (1906-1909) ጊዜ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በርካታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ይነገራል። በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ እድገት የተመዘገበውም በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ (1923-1966) ጊዜ ነው። እድገቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ማለትም የትምህርት መዋቅር፣ የመምህራን ሥልጠና፣ የትምህርት አስተዳደር እና ትብብር እንደነበር ጥናቱ ያመላክታል።

የትምህርት ሥርዓት

የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አብሮ የሚቀያየር ስለመሆኑ፣ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል ከሚባልለት ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት ወዲህ እንኳን ያለውን በመንግሥታቱ መቀያየር አብሮ የሚቀያየረውን የትምህርት ሥርዓትና የትምህርት መዋቅር መመልክት በቂ ማስረጃ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ።

መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየረው የትምህርት ሥርዓት ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በመራው ኢሕአዴግ ተቀይሯል። በኋላም ብልጽግና መራሹ መንግሥት የኢሕአዴግን የትምህርት ሥርዓት ለመቀየር አዲስ የትምህርት እና ጥናት ረቂቅ ፖሊሲ አዘጋጅቶ፤ ፖሊሲው ገና በረቂቅ ላይ እያለ ከቅድመ መደበኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በተያዘው 2015 ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተገቢውን እውቀትና ክህሎት ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አጣምሮ ለመስጠት የሚያስችል እና በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ በሰጠው ማብራሪያ አስታውቋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከዚህ በፊት የነበረው ስርዓተ ትምህርት የነበሩበት ክፍተቶች በጥናት ተለይተዋል፤ አዲሱ ስርዓተ ትምህርትም በጥናት ላይ መሠረት ተደርጎ የተቀረጸ ነው ብሏል። አዲሱ ስርዓተ ትምህርት አገር በቀል እውቀትን፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እንዲሁም ተግባር ተኮር ትምህርትን ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አቀናጅቶ ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ ነው፡፡ በመሆኑም በእውቀትና ከህሎት የታነጸ ትውልድ ከመገንባት አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው ተብሎለታል።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ፣ ቅደመ መደበኛ ደረጃ፣ አንደኛ ደረጃ፣ መካከለኛ ደረጃና ኹለተኛ ደረጃ ተብሎ ተከፋፍሏል። በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የአደረጃጀት ለውጥ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም ቅድመ መደበኛ  ኹለት ዓመት፣ አንደኛ ደረጃ (ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል)  ስድስት ዓመት፣ መካከለኛ ደረጃ  (7ኛ እና 8ኛ ክፍል) ኹለት ዓመት እንዲሁም ኹለተኛ ደረጃ (ከ9ኛ እስከ 12ኛ) ክፍል አራት ዓመት እንዲሆን ተደርጓል።

በ2015 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን፣ በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ደግሞ የሙከራ ትግበራ በተመረጡ 80 ትምህርት ቤቶች እንደሚካሄድ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

አዲስ ማለዳ ትምህርት ሚኒስቴር አዲሱን ስርዓተ ትምህረት ተግባራዊ ለማድረግ ለመምህራን ሥልጠና አቅጣጫ የሰጠበትን ሰነድ የተመለከተች ሲሆን፣ በሰነዱ ላይ ከዚህ በፊት ይሰጡ ከነበሩ የትምህርት ዘርፎች የተቀነሱና የተጨመሩ መኖራቸውን ተመልክታለች። በአዲሱ የትምህርት መዋቅር (ካሪክለም) መሠረት ለቅድመ መደበኛ ደረጃ የሚሰጡ ትምህርቶች የመጀመሪያ ቋንቋ፣ ግላዊና ማኅበረ-ስሜታዊ እድገት፣ ሂሳብ፣ አካባቢ ሳይንስ፣ ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ እና የጤናና የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ናቸው። በዚህ የትምህርት ደረጃ እንግሊዝኛ የተቀነሰ ሲሆን፣ ግላዊና ማኅበረ- ስሜታዊ እድገት አዲስ የተጨመረ ትምህርት ነው።

የአንደኛ ደረጃ የትምህርት (ከ1ኛ እስከ 6ኛ) ክፍል የሚሰጡ የትምህርት ዘርፎች ስምንት ሲሆኑ፣ የመጀመሪያ ቋንቋ፣ የፌዴራል ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ አካባቢ ሳይንስ፣ የግብረ ገብነት ትምህርት፣ ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ፣ የጤናና የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ናቸው። በዚህ የትምህርት ደረጃ በትምህርት ስርዓቱ እንዲካተት ብዙ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረው የግብረ ገብነት ትምህርት አዲስ የተጨመረ ትምህርት ነው።

የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት (7ኛ እና 8ኛ ክፍል) በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት 11 የትምህርት ዓይነቶችን ያካተተ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ቋንቋ፣ የፌዴራል ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ፣ ሂሳብ፣ አጠቃላይ ሳይንስ፣ የኅብረተሰብ ትምህርት፣ የዜግነት ትምህርት፣ ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ፣ የጤናና የሰውነት ማጎልመሻ፣ የሥራና ቴክኒክ ትምህርቶች ተካተዋል።

በዚህ የትምህርት ደረጃ እንደ አዲስ የተጨመሩት የትምህርት ዘርፎች የሥራና ቴክኒክ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና አጠቃላይ ሳይንስ ሲሆኑ፣ ከዚህ በፊት ለየብቻቸው ሲሰጡ የነበሩት የፊዚክስና ኬሚስትሪ ትምህርቶች በአጠቃላይ ሳይንስ ተካተዋል።

በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል 12 መደበኛ የትምህርት ዓይነቶችና ሦስት አማራጭ ትምህርቶች ቀርበዋል። የመጀመሪያ ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ፣ ሂሳብ፣ ባዮሎጂ፣ ኬምስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ጂኦግራፊ፣ ታሪክ፣ የዜግነት ትምህርት፣ ኢኮኖሚክስ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና የጤናና የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርቶች ናቸው። እንደ አማራጭ የቀረቡት ደግሞ፣ የፌዴራል ቋንቋ፣ የውጭ ቋንቋ እና ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ናቸው። በዚህ የትምህርት ደረጃ ከአማራጭ የትምህርት ዘርፎች ውጪ ኢኮኖሚክስ እንደ አዲስ የተጨመረ ትምህርት ነው።

አዲሱ ሥርዓት ትምህርት በኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት ሲሠራበት የቆየውን የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ የቀየረ ሲሆን፣ የተሻሻለው የትምህርት ሥርዓት የመማር ማስተማሩን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል እንዲሁም ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ እና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የትምህርት ማኅበረሰብ መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ትምህርት በቀድሞው የትምህርት ሥርዓት 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው አገራዊ የመልቀቂያ ፈተና እንዲቀር የተደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ ፈተና በክልል ደረጃ 6ኛ ክፍል እንዲሁም በአገር ዐቀፍ ደረጃ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ይሰጣል። ከዚህ ቀደም ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ዝቅተኛው አራት ዓመት እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ ለኹሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ከሚሰጡ ትምህርቶች ውስጥ እንደ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሺዮሎጂና ሥነ-ምግባር የመሳሰሉት ተካተዋል።

በኢትዮጵያ ቀደምት የትምህርት ሥርዓት ይሰጥ የነበረው የግብረ ገብ ትምህርት መቅረቱ፣ በትምህርት ማኅበረሰቡ ውስጥ ሥነ ምግባርና ስብዕና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፋ እንዲሄድ ጉልህ ሚና እንደተጫወተ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ትምህርት መምህር እና በትምህርት አስተዳደር ጥናት ያደረጉ ምሁር ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል። ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የትምህርት ሥርዓት የግብረ ገብ ትምህርት መካተቱ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ብዙዎች በተስፋ ይገልጻሉ።

ትምህርት እና ፖለቲካ

የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት በየዘመናቱ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር የትምህርት ሥርዓት መሆኑን እና ከፖለቲካ ነጻ ያልሆነ ዘርፍ ስለመሆኑ ብዙ መከራከሪያዎች ይነሱበታል። የትምህርት ዘርፉ ከሥርዓት እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ክፍተቶች እንዳሉበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በዘርፉ የሚታየው የሥርዓት እና የአፈጻጸም ክፍተት ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝም የሚያምኑ ወገኖች አሉ።

በዋናነት በዘርፉ የሚታየው ችግር የትምህርት ሥርዓቱን ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ፣ ሥርዓቱ በአፈጻጸም ረገድ የፖለቲካ መጠቀሚያ ወይም የፖለቲካ ጥገኛ መሆኑ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ጭምር ማረጋገጣቸውን ይገልጻሉ።

በትምህርት ሥርዓቱ በኩል የሚታየውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ የታሰበው የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል። በዚሁ መሠረት ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ከቅድመ መደበኛ ደረጃ እስከ 8ኛ ክፍል በሙሉ ትግበራ፣ እንዲሁም በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እያደረጉ ነው።

የትምህርት ዘርፉ ከዚህ ቀደም በነበረው ሥርዓት የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን ተከትሎ ስብራት እንዳጋጠመው የሚገልጹት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ዘርፉን ካለበት ችግር ለማውጣት ትምህርትን ለሙያተኞች መተው እና በእውቀት ላይ የተመሠረተ አሠራር መከተል እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ትምህርት በዓለም ላይ ለሚታዩ ለውጦች ጉልህ ሚና የሚጫወት፣ ለእድገትና ለለውጥ ቀዳሚ መሠረት ነው። ትምህርትን በአግባቡ የተጠቀሙ እና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት የተከተሉ የዓለም አገራት በተለያዩ ዘርፎች ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። የትምህርት ዓላማ እውቀትን ማስጨበጥ እና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኹለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የሚጠቅም የእውቀት ሽግግር ማድረግ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ባለሙያዎቹ ሲገልጹ ይደመጣሉ። በተደጋጋሚ ሲሉ እንደሚደመጡትም፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ችግር፣ በተለይ የደርግን መንግሥት መውደቅ ተከትሎ ወደ ሥልጣን በመጣው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የአገዛዝ ዘመን የተስፋፋ ነው። በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ካመጣው ውጤት ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ።

በኢሕአዴግ የመንግሥትነት ዘመን የትምህርት ዘርፍ የትምህርት ዓላማን ከማሳካት ይልቅ ያስከተለው ጉዳት እንደሚያመዝን የሚገልጹም አሉ። የትምህርት ዘርፉ ዓላማውን እንዲስት አድርገዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል፣ ኢሕአዴግ ትምህርትን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ መጠቀሙ መሆኑ ይጠቀሳል። ዘርፉ የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን ተከተሎ ከዋና ዓላማው በማፈንገጡ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ዋጋ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኹሉን ዐቀፍ ዕድገት ማምጣት ሳይችል ቀርቷል የሚል ትችት ይበዛበታል።

በወቅቱ የነበረው የትምህርት ሥርዓት በአግባቡ ተግባራዊ አለመደረጉን ተከትሎ፣ የትምህርት ሥርዓቱ በአፈጻጸሙ የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑ ይነገራል። በዚህም በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች የሚሰጡት ትምህርት፣ በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች የሚቀነቀነው አስተሳሰብ የብሔር ፖለቲካ በትምህርቱ ማኅበረሰብ ላይ እንዲጎለብት ማድረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

የትምህርት ዘርፉ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና መሣሪያነት ነጻ መሆን እንዳለበት እነዚሁ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይመክራሉ። ይሁን እንጂ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉ የፖለቲካ ጥገኛ ከመሆን አልዳነም። በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ መቅሰም ያለበትን ተገቢ እውቀት አግኝቶ መውጣት ሲገባው፣ በትምህርት ተቋማት ቆይታው የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ሆኖ የሚወጣበት ሁኔታ ጎልቶ መውጣቱ አሳሳቢ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ለዚህም ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከሰተው የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን መመልከት እንደ አንድ ማስረጃ ይወሰዳል። የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ እንደመሆናቸው መጠን፣ ብዝኅነትን ማስተናገድ አልቻሉም። ለዚህም ዋናው ማሳያ በትምህርት ተቋማት ሲከሰቱ የነበሩት የጸጥታ ችግሮች ብሔርን ወይም የፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን መሠረት አድርገው የተከሰቱ መሆናቸው ነው።

የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት አፈጻጸም የፖለቲካ ሥርዓት ማስፈጸሚያ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በትምህርት ጥራት ላይ የሚነሳው ጥያቄ አሁንም ምላሽ ያገኘ ጉዳይ አይደለም። በጥራት ላይ የሚነሳው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝና የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በሚጠበቅበት ሁኔታ፣ የትምህርት ስርዓቱ አሁንም ከፖለቲካ ጥገኝነት ነጻ አለመሆኑን የሚያሳዩ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

አዲስ ማለዳ ስለ አዲሱ የትምህርት ፖሊስ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጧት የጠየቀቻቸው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የፖሊሲ አማካሪ እንደሚሉት፣ ትምህርት የአንድን አገር ትውልድ የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስን እንደመሆኑ መጠን የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ ቀረጻና ትግበራ ከፖለቲካ ቅኝትና ተጽዕኖ ነጻ መሆን ይገባዋል። ይሁን እንጂ፣ በኢትዮጵያ ያለው ተሞክሮ የትምህርት ሥርዓት መንግሥታት በሚቀያየሩበት ወቅት አብሮ የሚቀያየርና ያለ ፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ለባለሙያዎች ብቻ የተተወ ጉዳይ አለመሆኑን ያነሳሉ።

የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታን ካዘጋጁት ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነልቦና እና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የፖለቲካ ጥገኛ መሆኑን ተከትሎ ስብራት ውስጥ መቆየቱን ያነሳሉ። የዘርፉ ምሑር ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ የትምህርት ዘርፍ ከፖለቲካ ነጻ መሆን ካልቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣቱ ቀርቶ የሚያስከትለው ጉዳት ያመዝናል ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ የትምህርት ዘርፉ በፖለቲካ ተጽእኖ ስር መውደቁን ተከትሎ የትምህርት ተቋማት ሲመሩ የነበሩት በካድሬ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም የተነሳ የትምህርቱ ዘርፍ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን ተከትሎ ዋና ግቡን ሳያሳካ በስብራት ውስጥ መቆየቱን ጠቁመዋል። እርሳቸው በተሳተፉበት የትምህርት እና የሥልጠና ፖሊሲ ላይ በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ያካበቱትን ልምድ ያካፈሉ ሲሆን፣ አሁንም የትምህርት ዘርፉ በሙያተኞች መመራት እንዳለበት ጠቁመዋል። ዘርፉ የመንግሥት ተጽእኖ የሚበዛበት ቢሆንም፣ በሂደት ከፖለቲካ ጥገኝነት ነጻ ማድረግ እንደሚገባም ይመክራሉ።

ከኢሕአዴግ ከሥልጣን መወገድ በኋላ የተተካው ብልጽግና መራሹ መንግሥት አሁን ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘውን የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ እንዲያረቁ ከተመረጡ የዘርፉ ምሑራን ውጪ፣ የፖለቲካ ሰዎች ተካተው እንደነበር አዲስ ማለዳ ሰምታለች። በዚህም በፖለሲ ማርቀቁ ሂደት የተካተቱ የዘርፉ ምሑራን ተቃውሞ በማሰማታቸው በወቅቱ ከሂደቱ የወጡ የፖለቲካ ሰዎች ስለመኖራቸውም ተመላክቷል።

የፖሊሲ አማካሪው እንደሚሉት፣ የትምህርት ፖሊሲን እንደ ቀላል ነገር ዐይቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የፖለቲካ ሰዎች በሂደቱ ተሰይመው አሁንም ተሳትፎ አድርገው ከሆነ  እና የትግበራ ሂደቱን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት ጣልቃ ገብነት የሚኖር ከሆነ፣ አሁንም የትምህርት ስርዓቱ ከነበረው አዙሪት ሊወጣ እንደማይችል ይገልጻሉ። የትምህርት ፖለሲ ከሌሎች ፖሊሲዎች ለየት የሚያደርገው ትውልድ የመቅረጽና እውቀት የማሸጋገር ጉዳይ መሆኑን የሚያነሱት የፖሊሲ አማካሪው፣ እንደ ሌሎች ጉዳዮች በፖለቲካ መነጽር መታየት እንደሌለበት ይገልጻሉ። የትምህርት ፖሊሲ የዘመናት የትውልድ ሽግግር ጉዳይ እንጂ፣ የአምስት ወይም ዐስር ዓመት የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም አማካሪው ይጠቁማሉ።

በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ከሙከራ ወደ ሙሉ ትግበራ የተሸጋገረው የትምህርት ሥርዓት የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ፣ ከመምህራን እስከ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች ድረስ ያሉ ሙያተኞች የአገር ፍቅር ወኔ ኖሯቸው ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚገባ ምሑሩ ጠቁመዋል። በትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ የትምህርት ሥርዓቱ ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል የተባለው የትምህርት ቋንቋ ሲሆን፣ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድ አገር በቀል ቋንቋ በፈቃደኝነት እንዲማሩ በፍኖተ ካርታው መካተቱን ይጠቅሳሉ። የቋንቋ ፖሊሲው፣ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አምስት አገር በቀል ቋንቋዎች የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ መጽደቁ የሚታወስ ሲሆን፣ ኦሮሞኛ፣ ትግሪኛ፣ ሱማሊኛ እና አፋርኛ የተመረጡ ቋንቋዎች ናቸው።

የተለያዩ አገር በቀል ቋንቋዎች ያሏቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት፤ ኹሉንም ቋንቋዎች ማካተት ባይችሉም እንኳን፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የተወሰኑ ቋንቋዎች ተማሪዎች እንዲማሩ ያደርጋሉ የሚሉት ጥሩሰው፣ በኢትዮጵያም አገራዊ መግባባት በሚፈጥር ኹኔታ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የቋንቋ ትምህርት አስፈላጊ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች እንደመኖራቸው መጠን በማንኛውም አካባቢ ቢያንስ አንድ አገር ዐቀፍ ቋንቋ፣ አንድ የማኀብረሰብ ቋንቋ እና አንድ ኢንተርናሽናል ቋንቋ በትምህርትነት ቢሰጥ፣ አገራዊ መግባባት ከማምጣቱ በላይ፣ የትምህርት ማኅበረሰቡ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመሥራት እና የመግባባት ዕድል እንዲያገኝ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ በአንድም በሌላም በኩል ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ ነው ማለት አይቻልም የሚሉት የፖሊሲ አማካሪው፣ ዘርፉ ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ በሙያተኞች እንዲመራ ካልተደረገ በየጊዜው በመንግሥታት መቀያየር አብሮ የሚሽከረከር ከሆነ የትምህርት ዓላማ መሳቱ አይቀርም ይላሉ። አንድ ፖሊሲ ሲቀረጽ እንደየዘርፉና እንደየሁኔታው የአጭርና የረዥም ጊዜ ግቦች እንደሚኖሩትም ጠቅሰው፣ የትምህርት ፖሊሲ መቀረጽ ያለበት አንድ ፓርቲ መንግሥት መሥርቶ በሥልጣን ላይ እስከቆየበት ጊዜ ብቻ የሚጠቀምበት ሳይሆን፣ በመንግሥታት መቀያየር የማይናወጥ የትምህርት ፖሊሲ መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ።

በኢትዮጵያ ትምህርትን እንደ ፖለቲካ መጠቀሚያ የማድረግ አባዜ አሁንም የሚታይ ሲሆን፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እነዚህ ተጽእኖዎች በትምህርት ዘርፉ ላይ ይታያሉ። ለዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ዋና ማሳያ የሚነሳው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገው የኦሮሚያ ክልል መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ነው። ከባለፈው ዓመት ወዲህ አከራካሪ አጀንዳ የሆነው ይሄው አሁንም በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መቀጠሉ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ የፈጠረና ትችት የበዛበት ጉዳይ ነው።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች መምህራንን አስተያየት ጠይቃለች። በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል መዝሙር መዘመርና ሰንደቅ ዓላማ መሰቀል ለችግሮች መከሰት ምክንያት ቢሆንም፣ በአዲሱ የትምህርት ዘመንም መቀጠሉን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው መምህራን ተናግረዋል። ጉዳዩ በመምህራንና በተማሪዎች ላይ ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ መሆኑን የሚገልጹት የከተማዋ መምህራን፣ ጉዳዩ ቋንቋውን በማይችሉ ተማሪዎችና መምህራን ላይ ፍራቻ የፈጠረ መሆኑንም ይገልጻሉ።

የኦሮሚያ ክልል መዝሙር በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መዘመሩና የክልሉ ሰንደቅ መሰቀሉ፣ በመምህራንና ተማሪዎች ላይ የፍራቻ ስሜት የፈጠረው ጉዳዩ ፖለቲካዊ እየሆነ በመምጣቱና ተማሪዎች ላይ የተፈጠረው ስሜት ከትምህርት ዓላማ ያፈነገጠ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል የሆኑት የፌዴራሊዝም ምሁሩ ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ላቀረበችላቸው ጥያቄ፣ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እንዲዘመርና ሰንደቅ እንዲሰቅል የተደረገው ውሳኔ ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑን ገልጸው ነበር። ውሳኔው ከጤነኛ እሳቤም የሚመጣ ነው ማለት አይቻልም የሚሉት ሲሳይ፣ ጤነኛ እሳቤ ቢሆን፣ ሕጋዊ መሠረት እንዲከተል ይደረግ ነበር ብለዋል።

ሕጉንና ስርዓቱን ተከትሎ መዘመርና መውለብለብ እንኳን ካለበት በየደረጃው ውይይት ተካሂዶበት፣ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ተደርጎ፣ ከተማ አስተዳደሩም በየደረጃው ያሉ አካላትም ተነጋግረው መወሰን እንዳለበት ይመክራሉ።

አሁን እየሆነ ያለው ግን በየትምህርት ቤቱ ያሉ የኦሮሞ መምህራና ተማሪዎች ይሄን እናደርጋለን የሚል አይነት ስሜታዊነትና የባለጊዜነት ስሜት የሚንጸባረቅበት እና ‹ተዉ!› ሲባሉም የማንአለብኝነት ሁኔታ የሚታይበት መሆኑንም ገልጸዋል። ጉዳዩ በየመድረኩ ሲነሳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚሰጡት ማብራሪያ የበለጠ ጤናማ እንዳልነበረና ግልጽ የሆነ ባለጊዜነት የተንጸባረቀበት መሆኑን ምሁሩ ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here