መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ 20 ሚሊዮን ዜጎች 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ 20 ሚሊዮን ዜጎች 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ 20 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ (ኦቻ ኢትዮጵያ)፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 20 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ባወጣው ሳምንታዊ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ከሚያስፈልገው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 700 ሚሊዮን ዶላር በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን መሆኑን ኦቻ ኢትዮጵያ በሳምታዊ ሪፖርቱ አመላክቷል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በበርካታ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ቀውሶች የተነሳ ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ኦቻ ኢትዮጵያ በሪፖርቱ ጠቁሟል። በ2022 የሰብዓዊ ምላሽ እቅድ ላይ እንደተመላከተው እስከ ፈረንጆቹ 2022 መጨረሻ ድረስ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እና የጥበቃ አገልግሎት ይፈልጋሉ ተብሏል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለአምስት ወራት ከዘለቀው የተረጋጋ ሁኔታ በኋላ፣ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በዐስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን ማወቁን ድርጅቱ አስታውቋል። ሁኔታው ከፍ ያለ የሰብዓዊ ፍላጎቶችን በመፍጠር እና ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ ለማድረስ የሚጥሩትን የሰብዓዊ አጋሮች የምላሽ አቅም እየፈተነ ነውም ተብሏል።

በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ እና በዋግ ኽምራ ዞኖች ጦርነቱ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦች ችግር ላይ መሆናቸውንና የጸጥታ ችግር በመኖሩ ሰብአዊ አገልግሎት ሰጪዎች ለመድረስ አስቸጋሪ ሆኖባቸው መቀጠሉንም ኦቻ ኢትዮጵያ አስታውቋል። በሰሜን ወሎ ዞን በመርሳ ከተማ ከ12 ሺሕ ያላነሱ አዲስ ተፈናቃዮች በተለይም ሴቶች እና ሕጻናት በከተማዋ ተጠልለዋል ተብሏል።

የኦቻ ኢትዮጵያ ሪፖርት እንደሚያመላክተው፤ በአማራ ክልል ቢያንስ አምስት ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ዋስትና ማግኘት አልቻሉም። በተለይ በክልሉ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መኖሩ ተመላክቷል።

በተመሳሳይ፣ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና የዜጎች ንብረትና መሠረተ ልማቶች መጎዳታቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል። በሰመራ መስመር ወደ ትግራይ የሚጓጓዙ የሰብአዊ ኮንቮይ እንቅስቃሴ በመቋረጡ፣ የሰብአዊ አቅርቦቶችን ለማጓጓዝ እንቅፋት ሆኗል ተብሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ አየር አገልግሎት በሳምንት ኹለት ጊዜ ከአዲስ አበባ መቀሌ በአየር ትራንስፖርት ያደርስ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ በረራም ተቋርጧል።

በምሥራቅ እና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ መንግሥት እና ግብረሰናይ አጋሮች በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ወደ 17 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች ዘርፈ ብዙ የሕይወት አድን እርዳታዎችን ለማቅረብ ግብአቶችን ማሰባሰብ ቢቀጥሉም፣ ፍላጎቱ አሁንም እየተካሄደ ካለው የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ ጋር የተመጣጠነ አለመሆኑን ሪፖርቱ ይትታል። የምግብ ዋስትና እጦት ከመባባሱና የተመጣጠነ ምግብ እጦት እየጨመረ ከመምጣቱ በተጨማሪ፣ የትምህርት ማቋረጥ እና የደኅንነት ስጋቶች መበራከታቸውን ኦቻ ኢትዮጵያ አመላክቷል።

2.9 ሚሊዮን ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች እስከ ዓመቱ መጨረሻ ማለትም እስከ 2022 መጨረሻ ድረስ የአልሚ ምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል። በድርቅ ምክንያት መፈናቀል መበራከት፣ ትምህርት ቤቶች መዘጋት እና የተላላፊ በሽታዎች መከሰት የተነሳ 1.4 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያመላክታል። የኩፍኝ እና የተቅማጥ በሽታዎችን ጨምሮ ድርቁ በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም እየጨመረ መሆኑም ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች