ኮርፖሬሽኑ በዘንድሮው ዓመት ከ380 ሺሕ በላይ ኩንታል የስንዴ ዘር ለማባዛት እቅድ ይዟል

0
1018

በዘንድሮው ዓመት ከአስራ አራት ሺሕ በላይ በሆነ ሄክታር መሬት ላይ ከ380 ሺሕ በላይ ኩንታል ምርጥ የስንዴ ዘር ለማባዛት እቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመንግሥት ትልቅ እቅድ የተያዘበት የመስኖ ስንዴ እህል የማባዛት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው ብሏል።

በዘንድሮው ዓመት በአስራ አራት ሺሕ 140 ሄክታር መሬት ላይ 380 ሺሕ ኩንታል ምርጥ የስንዴ ዘር ለማባዛት እቅድ ተይዟል። ከተባዛ በኋላ ወደ 20 ሺሕ ሄክታር ለሚሸፍን መሬት የዘር ግብዓት እንደሚሆንም ተመላክቷል።

ከዚህ ውስጥ በአዋሽ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ወደ 400 መቶ ሄክታር መሬት ላይ ዘር እየተባዛ ነው የተባለ ሲሆን፣ 10 ሺሕ ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት እንደሚገኝም ነው የተገለጸው።

እንዲሁም በፈንታሌ አንድ፣ ኹለትና አሚባራ እየተባዙ ያሉት የስንዴ ዘሮች ለቆላማ አካባቢ የሚሆኑ አዳዲስ ዝርያዎች ናቸው ተብሏል።

ዝርያዎች እ.ኤ.አ በ2017 የወጡ ሲሆኑ ከፍተኛ ምርት ያስገኛሉ፤ ከምርምር ጣቢያዎች በመውሰድ 60 ሄክታር የሚደርስ መሬት ላይ ዘሩ እየተባዛ ነው። በቀጣይ አንድ ዓመት ተጨማሪ የማባዛት ሥራ በመሥራት ለአርሶ አደሮች የሚከፋፈል ይሆናልም ሲል ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

በአዲስ መልክ እየለሙ ባሉ ኦሞ አንድ፣ ተንዳሆና በለስ ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ኮንትራት በመውሰድም በልዩ ሁኔታ በስፋት ዘር ለማባዛት በቅድመ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፣ በነባሮች የዘር ማባዣ ላይ ስንዴና በቆሎን በስፋት ለመሥራት ዝግጅት እያደረኩኝ ነውም ብሏል።

ኮርፖሬሽኑ ስንዴን በማባዛት ላይ ላሉ አካላት ከመሬት ልማት ጀምሮ እስከ አጨዳ ድረስ ያሉትን ሥራዎች አግዛለሁ ያለ ሲሆን፣ በተጨማሪም ማዳበሪያና ዘር ከማቅረብ ጀምሮ የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘር እንዲደርስ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ሲል አክሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here