መንግሥት አለሁ ይበል!

0
1289

‘በሕግ አምላክ’ ሲባል እንኳን ሰው ወራጅ ውሃ ይቆማል› የሚል ብሂል አለ። ይህም ሕግ በማኅበረሰብ ውስጥ ምን ያህል ቦታ እንዳለው የሚያሳይ ነው። በሰዎች ዘንድም በሕግ ላይ የጸና እምነት አለ። ይህ የጸና እምነት ነው ሰዎች በማኅበራዊ ሕይወታቸው በጋራ ለሚያኖራቸው ስርዓት ተገዢ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው። ይህ ካልሆነ ግን ስርዓት የሌላቸው፣ ከእንስሳት ያልተሻሉ ሰዎች ይፈጠራሉ።

አንድ ማኅበረሰብ በጋራ ለመኖር የሠራውን ሕግ በፈቃደኝነት ሊያከብር የሚችለው፣ የራሱን ጥቅም ሲያስከብርለት ብሎም ከክፉ ሲከላከለው ነው። (በዚህ ውስጥ ግዴታና መብት የሚባሉ ነገሮች እንዳሉ እንዳልተዘነጋ ልብ ይሏል!) ሕግ ትርጉም የሚሰጠውም በዛ መልክ አንድን ማኅበረሰብ ወይም ሕዝብ ማገልገል ሲችል ነው። እንዲያ ሳይሆን ሲቀር፣ ሕጉን የሚጥስ ሲመጣ የሕግ አምላክ ወዴት አለህ ብሎ ማኅበረሰብና ሕዝብ ይጣራል።

አዲስ ማለዳ በምድር ላይ የሕግ አምላኩ መንግሥት እንደሆነ ታምናለች። ሕግ አንድም ሕዝብ ተስማምቶበት፣ ይበጀኛል ብሎ የሚያወጣውና አብሮ ሊያኖረው የሚችል መመሪያ ነው። መንግሥት አንድም ገዢ አንድም ሕዝብን የሚወክል ነውና ይህን ሥልጣን አግኝቷል።

አሁን አሁን ታድያ የሕግ አምላክ ወዴት አለህ! መንግሥት አለሁ በል! የሚያሰኝ ብዙ አሳዛኝ ክስተት በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ይታያል።

ሰው በገዛ አገሩ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው መንቀሳቀስ አልቻለም። ለሥራ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እንኳ ወደሚሄዱበት ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ በተቻለ መጠን በተሽከርካሪ ሳይሆን በአየር ላይ እንዲያደርጉ ተገደዋል። ‹አትሂዱ› የሚባልባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው፣ ‹አትለፉባቸው› የሚባሉ መንገዶች ጥቂት አይደሉም። ከከተማ ወጣ ብሎ የታመመ ዘመድን መጠየቅ፣ የሞተን መቅበር ‹ነበር› እየሆነ መጥቷል።

ነጋዴው ‹ገንዘብ በሰዎች ኪስ ውስጥ ፈስሷልና እፈስ› የተባለ ይመስል፤ በሕግና ደንብ ሳይሆን በአመሉ ልክ ይሸጣል። ‹በመጥፎ ኹኔታዎች ውስጥ ጥሩ እድሎች ይኖራሉ!› ይሉት የአነቃቂ ነን ባዮች ንግግርን ነጋዴው በሚገባ እየተጠቀመበት ነው። የሕግ አምላኩ አይሰማም ብሎ እጥፍ ትርፍ በማጋበስ ላይ ተጠምዷል። ስስትና ራስ ወዳድነት በሕግ አጥር ውስጥ ሊገደቡ አልቻሉም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሞት አዲሱ ልምዳችን ሆኖ፣ ‹እገሌ የሚባል ሰው ተገደለ›ን አልፈን ‹መቶ በላይ ሰዎች ተገደሉ› ማለት ላይ ደርሰናል። ተስፋን በሚገዳደር መጠን ሰውነት እጅግ ረክሶ የንጹሐን ሞት የዜና አውታሮች ቁርስና ምሳ ሆኗል። በቅርቡ እንኳን በወለጋ ዳግም የብዙዎች ሕይወት በጭካኔ መነጠቁን ሰምተናል። ከዚህም በላይ የመንግሥት ያለህ የሚያስብል ከወዴት ይመጣል?

አሸባሪዎች፣ አጥፊዎችና የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ አካላት እንዲህ ባሉ የግፍ ሥራዎች ውስጥ እየተሳተፉ እንደሆነ መንግሥት በተለያየ አጋጣሚ ለማሳወቅ ሞክሯል። ምንም እንኳ የሰዎችን ሕመም በተረዳ መጠን እልቂቶችና ሞቶች በተፈጸሙ ሰዓት መንግሥት ከነመፈጠሩም ያለና የነበረ ባይመስልም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የውጪ ኃይሎች ሴራ በኢትዮጵያ ላይ ማጥላቱን ሲናገሩ ይደመጣል።

ሕዝብ በሕግ አምላክ ሲል፣ የሕግ አምላክ እንዲደርስለት ይጠብቃል። አንድን ሀብት ጠብቅ የተባለ አደራ የተሰጠው ሰው ያንን ሀብት መጠበቅ ባይችል እና በሌባ ቢዘረፍ፣ አደራ ሰጪው ዘራፊውን ሳይሆን የሚጠይቀው አደራ ተቀባዩን ነው። እንደዛም ሁሉ መንግሥት ባለበት አገር የንጹሐን ሞት ከገዳዮች ይልቅ ንጹሐን ዜጎቹን መጠበቅ ያልቻለውን መንግሥት ተጠያቂና ተከሳሽ ማድረጉ የማያጠራጥር ነው።

አዲስ ማለዳ መንግሥት አለሁ ይበል ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች። ሕግና ስርዓት እንዲከበር ስትል ትጠይቃለች። ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ ወይም በተሰጣቸው ሥም ሳይለዩ እኩል እንዲዳኙ፣ በሚናገሩት ቋንቋ የተነሳ ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ጥበቃ እንዲደረግላቸውም ታሳስባለች። ምንም በማያውቁት የመኖር መብታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ እየተነጠቁ ስላሉ ሕጻናትም ትለምናለች።

ብዙዎች ዛሬ ላይ እንዴት ነው የምንኖረው፣ አገር መፍረሷ ነው እያሉ ዛሬን እያሰቡ ይገኛሉ። ከዛም በላይ ግን የሚያሳስበው ነገ ነው። ዛሬ በብሔር ተለይተው ስለሚገደሉ፣ በር ስለሚዘጋባቸው፣ እንግልት ስለሚገጥማቸው ሰዎች ስናነሳ፤ ነገንም አብረን እያነሳን መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

የቀደመው ስርዓት የዘራው ዘረኝነት ነው ዛሬ በአደባባይ እየታየ ያለው፣ ቀድሞ የተተከለ ጠባብነትና ጨለምተኝነት ነው ዛሬ በገሃድ የተገለጠው ወዘተ ሲባል ይደመጣል። እንደዛው ሁሉ፤ ዛሬ እየታጨደ ብቻ ሳይሆን ሌላም አዲስ መርዛማ ዘር እየተዘራ እንደሆነ መንግሥትም ሕዝብም ሊያስተውሉ ይገባል። ሕይወቱ ካለፈው ይልቅ ጠባሳውን እና ቂሙን ይዞ የሚሻገር ትውልድ ከዚህኛው ትውልድ ደጃፍ ላይ ተራውን እየጠበቀ ይገኛል።

ብዙዎች በተፈናቀሉባቸው፣ በሞቱባቸውና ቤት ንብረታቸውን ባጡባቸው አካባቢዎች ሕጻናት እና አዳጊ ልጆች ይገኛሉ። እነዚህ ‹እገሌ ወላጆቻችሁን እንዲህ አድርጎባችኋል፣ እነ እገሌ እንዲህ ዓይነት ጭቆና በቤተሰባችሁ ላይ ፈጽመዋል!› ተብለው መሰበክ አይኖርባቸውም። ወይም የሐሰት ትርክት፣ ውሸትና መሰል ጉዳይ አጀንዳቸው አይሆንም። እነዚህ ከትምህርታቸው፣ ከወላጅና ቤተሰባቸው፣ ከለመዱት ነገር ሁሉ የተለዩ፣ በሕይወት የተረፉ ልጆች የሆነውን እና እየሆነ ያለውን በንጹሕ ልብና አእምሯቸው ላይ እያተሙ ነው።

እርግጥ ነው! መንግሥት በሰሜኑ ያለውን ጦርነት ጨምሮ፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ፣ ዓለም ዐቀፍ ተጽእኖዎችና በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች ሁሉ ውሳኔ፣ ምላሽና ሥራውን የሚጠብቁ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህም በድምሩ ቀላል ጫና እንደማይኖራቸው እሙን ነው። ሆኖም የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ነውና፣ የመንግሥትና የባለሥልጣናቱ ዝምታ እየሆነ ያለውን ወደ አለመሆን አይቀይረውምና፤ መንግሥት ከሕግ አምላክ የሚጠበቀውን እንዲያደርግና አለሁ እንዲል አዲስ ማለዳ በአጽንዖት ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here