የመንግሥት ግዢን ከሌብነት የማላቀቅ ጅማሮ

0
1582

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በየዓመቱ የተለያዩ ግዢዎችን የሚፈጽሙ ሲሆን፣ በየደረጃው የሚፈጸሙ የመንግሥት ግዢዎች ከሌብነት የጸዱ አለመሆናቸው በተደጋጋሚ ይነሳል። እነዚህ ግዢዎች ከሚፈጸሙባቸው የግዢ ሥርዓቶች መካከል የጨረታ ግዢ አንዱ ሲሆን፣ የጨረታ ግልጽነትና ከሙስና የጸዳ መሆኑ ላይ በየጊዜው ጥያቄ ሲነሳ ይስተዋላል። የመንግሥት ግዢ በሚገባው ልክ ትኩረት ያገኘ አለመሆኑም ዘርፉን በሚሠሩ አካላት በየጊዜው ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከምትበጅተው ዓመታዊ በጀት ውስጥ እስከ 70 በመቶ የሚደርሰው በጀት ለግዢ የሚወጣ መሆኑን የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል። ምንም እንኳን ዘርፉ ትልቁ የመንግሥት ዓመታዊ በጀት ፈሰስ የሚደረግበት ቢሆንም፣ በየዓመቱ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለግዢ የሚወጣው ገንዘብ ከሙስና የጸዳ እና ከአላስፈላጊ ብክነት የጸዳ ነው ማለት እንደማይቻል የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ ይገልጻሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ የመንግሥት ግዢ ከብልሹ አሠራር የጸዳ ባለመሆኑ፣ እንደ አገር የመንግሥት ግዢ ዓላማ ሙሉ በሙሉ በአግባቡ ተግባራዊ ተደርጓል ማለት አይቻልም። በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የግዢ ዘርፉ ላይ ላሉ ባለሙያዎች መጠቀሚያ ተደርጎ ይወሰዳል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረትና ስለ ዘርፉ ያለው ግንባዜ ከመንግሥት ግዢ ዓላማ ጋር የማይጣጣም ነው ይላሉ።

ታዲያ አሁን ላይ ይህን ችግር ይቀርፋል የተባለለት ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፣ ሥርዓቱ በዘርፉ የሚታየውን ብልሹ አሠራር ከማስቀረት ጀምሮ የመንግሥትን የግዢ ወጪ እስከመቀነስ የሚደርስ ጉልህ ሚና እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። ይህን ሥርዓት ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹የሌቦችን ጉሮሮ አንቆ የሚይዝ ነው›› ሲሉ ይገልጹታል።

ዋና ዳይሬክትሩ ስለ ኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓት ይህን ያሉበት ምክንያት፣ የጨረታ ሽርክናን ወይም ሌብነትን ሊያስቀር የሚችል የመንግሥት የግዢ ሥርዓት መሆኑን በማንሳት ነው።

ኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓትን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2014 በተመረጡ ዘጠኝ ከፍተኛ የመንግሥት ግዢ ፈጻሚ በሆኑ ተቋማት ላይ ተግባራዊ ማድረጓ የሚታወስ ነው። ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነው ይህ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገባቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥርዓቱን በበላይነት የሚመራውን የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣንን ጨምሮ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ እስከ አሁን ስትጠቀም የነበረው የግዢ ሥርዓት በቴክኖሎጂ ያልተደገፈና ከሰው ግንኙነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ በጨረታዎች ላይ ሙስና የመፈጸም እድሉ ሰፊ እንደነበር የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ይገልጻሉ። በቀጥታ በሰዎች አማካይነት የሚሠራ የጨረታ ሥራ ለሙስና ተጋላጭ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው የሚሉት ሃጂ፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ እያደረገችው በሚገኘው የኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓት ከዚህ በፊት በዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ይቀረፋሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ብለዋል።

ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት የግዢ እቅድ ማስጀመር፣ የጨረታ ሂደትን ማስተዳደር፣ አሸናፊዎችን መግለጽ፣ ውል መፈራረምና የውል ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥራዎችን ማከናወን የሚያስችል ነው።

ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት የግዢ ሥርዓት የመንግሥት ግዢ ተቀዳሚ ዓላማና መርህ የሆኑትን ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘትን፣ ከአድሎ የጸዳ አሰራር መፍጠርን፣ ግለጸኝነትን፣ ቁጠባንና ተጠያቂነት የመሳሰሉትን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያግዝ ሥርዓት መሆኑ ታምኖበታል። የመንግሥት ግዢ አጠቃላይ ለኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የመንግሥት በጀት ውስጥ የግዢ ድርሻ እስከ 70 በመቶ ያክሉን ከመሸፈኑ ባሻገር ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) የግዢ ድርሻ እስከ 14 በመቶ እንደሚሸፍን ከመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ የመንግሥት ግዢ ለአገር ውስጥ ምርት 15 በመቶ ድርሻ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች 7.5 በመቶ፣ ለአገር ውስጥ መድኃኒት አቅራቢዎች 25 በመቶ እና ለጥቃቅንና አነስተኛ ሦስት በመቶ እድል ይሰጣል።

በ2014 በጀት ዓመት በዘጠኝ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ በሰባት መሥሪያ ቤቶች ላይ በአግባቡ የተተገበረው ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓቱ፣ በመጀመሪያው የሙከራ ትግበራ በተቋማትና ዘርፉ ላይ ባሉ ባለሙያዎች በኩል ሥርዓቱን ለመፈጸም የቁርጠኝነት ክፍተት ታይቶ እንደነበር የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ይገልጻሉ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ኋላ ከማለታቸው በተጨማሪ፣ የግዢ ባለሙያዎች ሥርዓቱን ያለመፈለግ ዝንባሌዎች ማሳየታቸውን ዳይሬክተሩ ያስታውሳሉ። ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢን ተግባራዊ ለማድረግ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሂደት ሥርዓቱን ከፌዴራል እስከ ክልል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተፈጻሚ ለማድረግ ባለሥልጣኑ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት የግዢ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ከተመረጡ ዘጠኝ መሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ፣ 63 መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥርዓቱ መግባታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በተያዘው በጀት ዓመት እስከ 105 የሚደርሱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥርዓቱ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በ2016 በጀት ዓመት 116 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግዢያቸውን ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት እንዲፈጽሙ እንደሚደረግም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓቱን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ፈተናዎች እንደሚኖሩ ተጠቁሟል።

በመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ስር የሚተዳደረው ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ታደሰ ከበደ በበኩላቸው፣ የመንግሥት ግዢ ከብለሹ አሠራር የጸዳና ግልጽ ከሆነ ከበጀት አጠቃቀም እስከ አጠቀላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው ፋይዳ ጉልህ ነው ይላሉ። በአንጻሩ የመንግሥት ግዢ ግቡን በሚመታበት ሁኔታ በአግባቡ ካልተፈጸመ የሚያስከትለው ኪሳራ ቀላል እንዳልሆነ ያሳስባሉ። ሥርዓቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ የግዢ እቅዳቸውን በኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓቱ ላይ ይፋ እንዲያደርጉ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ይህም ሕዝቡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ምን አቅደው ምን ፈጸሙ የሚለውን መረጃ በግልጽ እንዲያገኝ ያስችላል ተብሏል።

ሥርዓቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ የግዢ እቅዳቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ማስቻሉ፣ ተጫራቾች ለጨረታ ዝግጁ የሆኑ መረጃዎችን በመመልከት ለጨረታ ውድድር ዝግጁ እንዲሆኑ እድል የሚከፍት መሆኑንም ታደሰ ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ከ40 ሺሕ በላይ ተጫራቾች ያሉ ሲሆን፣ እስካሁን ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ሦስት ሺሕ በላይ ተመዝግበዋል ተብሏል።

ይህ ሥርዓት ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም ዐቀፍ የጨረታ ተወዳዳሪዎችን ቁጥር ይጨምራል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን፣ ተጫራቾች በጨረታ ለመሳተፍ ሊያወጡ የሚችሉትን ጊዜና ገንዘብ ያስቀራል። በኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት የግዢ እቅድ የሚያቀርቡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ይሁኑ ተጫራቾች፤ ባለቡት ሆነው አገልግሎቱን በበይነ መረብ አማካኝነት ማግኘት ይቻላሉ። በዚህም ከዚህ ቀደም በጨረታ ሂደት ላይ ይወጣ የነበረውን ወጪ እስከ 50 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል ታደሰ ጠቁመዋል።

ሥርዓቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ በጨረታ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘትና ሂደቶችን ለመከወን አስፈላጊ ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ተሳስሯል ተብሏል። በዚህም ሥርዓቱ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከባንኮች ጋር የተናበበ እንዲሆን በመደረጉ፣ ለተጫራቾች የጨረታ ማስከበሪዎችን እንዲያስይዙ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ላይ በአጭር ጊዜ ሰፊ ተደራሽነት ያገኘው ቴሌ ብር በቅርቡ ወደ ሥርዓቱ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

ሥርዓቱን የሚያለማውን አማካሪ ድርጅት ከመቅጠር ጀምሮ ሥርዓቱ እንዲለማና ለተቋማት ምቹ እንዲሆን ለማስቻል በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፣ በተለይ የሲስተም መፈተሽ ሥራው ለሙከራ ትግበራ ከተመረጡ ተቋማት ባለሙያዎች ጋር ለስድስት ወራት ተከናውኗል ነው የተባለው። በፍተሻ ሥራው የግዢ እቅድ፣ የግዢ እቅድ ማስጀመር፣ ግዢ፣ ጨረታ፣ ሃራጅ፣ ውል፣ ውል መፈራረምና የውል ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓቶችን በተግባር መፈተሽ ተችሏል።

የነበረው የሲስተም ፍተሻ ሥራ በርካታ ልምድ የተገኘበት፣ የሲስተሙ ተጠቃሚዎች በቀላሉ ሥርዓቱን መጠቀም እንዲችሉ ቀላልና ግልጽ እንዲሆን የተደረገበት ሲሆን፣ ሲስተሙ ከበርካታ ተቋማት ሲስተሞች ጋር ቅንጅት ስለሚኖረው መረጃን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበት መሆኑ ታውቋል።

ከኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ጋር ተያያዞ የሚነሱ የደኅንነት ስጋቶችን ለመቀነስ የኹሉም ተቋማት ሰርቨር ማዕከላዊ በሆነ መልኩ በመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን የሚኖር በመሆኑ፣ የአገሪቷን ግዢ በአንድ ቋት ለመያዝ ከማስቻሉም ባሻገር አስተማማኝና ከስጋት ነጻ እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል ተብሎለታል።

ሥርዓቱ የግዢ እቅዶችን፣ መግለጫዎችን፣ የጨረታ ማስታወቂያዎችን ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተጨማሪ የግዢ ተጫራቾችን መጋበዝ፣ የጨረታ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ የሃራጅ ጨረታ ሂደቶችን እና የጨረታ ግምገማዎችን ማካሄድ፣ የጨረታ አሸናፊዎችን ማሳወቅ፣ የውል ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥራዎችን ማከናወን፣ መረጃ እንደ አስፈላጊነቱ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እና መረጃዎችን መተንተን፣ የአቅራቢዎችን ዝርዝር መመዝግብ፣ የጨረታ ሰነዶችን በሽያጭም ሆነ በነጻ እንዲገኙ የሚያስችል ነው።

የኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓቱ ተግባራዊ መሆኑ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ የግዢ ሥርዓቱ ግልጽነትን የተላበሰ እንዲሆን እንደሚያስችል እና ከደንበኞች ጋር ያለውን ቀጥታ ግንኙነት ከመቀነስ ባሻገር ሙስናን መቀነስ እንደሚያስችል ተስፋ ተጥሎበታል።

ኤሌክትሮኒክ የግዢ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ የቻሉ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ ሥርዓቱ የመንግሥት የግዢ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ኤሌክትሮኒክ የግዢ ሰርዓት ከአምስት እስከ 25 በመቶ የመንግሥት ግዢ ወጪን ይቀንሳል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም ሥርዓቱን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ለግዢ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ እንደምትችል ተመላክቷል።

ሥርዓቱ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ሰፊ ተደራሽነትን ለመፍጠር፣ አስተዳደራዊ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ ለግዢ አፈጻጸም የሚፈጀውን ጊዜ ለማሳጠር፣ የጨረታ ተወዳደሪዎችን ለማብዛት፣ ፍትሐዊነትን ለመፍጠርና አጠቀላይ የግዢ ሥርዓቱን ለማዘመን የማይተካ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here