ለኢንተርፕራይዞች 200 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የብድር በጀት ተፈቀደ

0
992

ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተጨማሪ 200 ሚሊዮን ዶላር የብድር በጀት መያዙን የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በጀቱ የተገኘው ከዓለም ባንክ በብድር ሲሆን፣ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ ለመደገፍ ከተያዘው መስከረም ወር ጀምሮ ለሦስት ዓመት ተግባራዊ ይሆናልም ነው የተባለው።

ብድሩ የሚቀርበው በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ሆኖ፣ የተፈቀደውን ብድር በሊዝ ፋይናንስ እና በሥራ ማስኬጃ ብድር ለመስጠት የቢሮ ሥራዎች ብቻ እንደሚቀሩ ተገልጿል። አሁን የተፈቀደው ብድር ከዚህ ቀደም ለኢንተርፕራይዞች ሲደረግ የነበረውን ድጋፍ ለማስቀጠል እና ከአሁን በፊት ብድር ያላገኙትን እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።

የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ወረደቃል ገብረክርስቶስ፣ ብድሩ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አልፎ በሌሎች ባንኮች አማካኝነት ለኢንተርፕራይዞች እንደሚሰጥ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ባንኩ እንደ ንግድ ፈቃድ፣ የመሥሪያ ቦታ/የኪራይ ውል፣ ቅድመ ማስያዣ እና የመሳሰሉ መስፈርቶችን በማውጣት ብድሩን የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል። አክለውም ብድሩ ባልተጋነነ የወለድ ምጣኔ እንደሚቀርብ ጠቁመው፣ ወለዱ በባንኮች የወለደ ምጣኔ አሠራር ይወሰናል ነው ያሉት።

‹‹ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ይደገፋሉ፣ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞችም ከባንኮች የፋይናንስ ድጋፍ ያገኛሉ።›› ያሉት ኃላፊው፣ ፕሮጀክቱ የተነደፈው መሀል ላይ ያሉትን እና የብድር እንዲሁም የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ችግር ያለባቸውን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለማገዝ ነው ብለዋል።

ስለሆነም ብድሩን በአምራችነት ዘርፍ የተሰማሩና በአነስተኛና መካከለኛ ምድብ ውስጥ የሚገኙ በአገሪቱ የሚገኙ ኹሉም ኢንተርፕራይዞች እንደሚያገኙ ነው ያስረዱት።

ኢንተርፕራይዞች በሰበሰቡት ፕሮፎርማ አዋጭነታቸው ተጠንቶ መሣሪያ በኪራይ የሚወስዱ ሲሆን፣ በኋላም የመሣሪያውን የባለቤትነት ደብተር እንደሚያገኙ ተመላክቷል።

በአምስት ዓመታት ውስጥ በተሠሩ ሥራዎች ከ3 ሺሕ 300 በላይ ለሆኑ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከ240 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎ ማሽን በሊዝ እንዲሁም የሥራ ማስኬጃ ብድር በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካኝነት እንዲያገኙ ተደርጓል ሲሉ የፕሮጀክቱ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አክለዋል።

እንዲሁም በፕሮጀክቱ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ከ1 ሺሕ 200 ለሚልቁ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልዩ ልዩ የአቅም ማሳደጊያ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን አክለዋል።

በተጨማሪም 33 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ከአገር ውጪ በተዘጋጁ ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ከውጪ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ መደረግ መቻሉም ተጠቅሷል።

የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመት በፊት ሥራ ሲጀምር ከሰባት ሺሕ የማይበልጡ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ በሚደረግላቸው ድጋፍ ቁጥራቸው ከ21 ሺሕ በላይ ደርሷል ነው የተባለው።

ይህ የፋይናንስ ፕሮጀክትም ከልማት ባንክ ጋር በመተሳሰር የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ እና የንግድ ልማት አገልግሎት ችግር ለመፍታት ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት የትግበራ በጀት መፈቀዱ የዘርፉን የፋይናንስ ፍላጎት ለመፍታትና ለመደገፍ እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here