ብዙዎቻችን ወደ ሕክምና ማእከላት የምንሄደው ሕመም ሲሰማን ወይም አንዳች የጤና እክል ሲገጥመን ነው። ይህም መሆኑ አንዳንድ ሕመሞች በጊዜ ሳይደረስባቸው ይቀራል። ከዛም በላይ በቶሎ መሻሻል እንዳይኖር ሊያደርግና ከፍተኛ ወጪንም ሊያስወጣ ይችላል።
ይህን ለመከላከል እንዲቻል የጤና ባለሞያዎች የሚመክሩት ዓመታዊ የሆነ የጤና ምርመራ ማድረግን ነው። ይህም ከስር ከስር ሰዎች የጤናቸውን ሁኔታ እንዲከታተሉና በቶሎ እርምጃ መውሰድ ያለባቸው ሲሆን እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል።
ዌልነስ ቼክአፕ የተሰኘ ድረ ገጽ ይህን በተመለከተ ባወጣው ዘገባ፣ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከጤና ባለሞያዎች ጋር የሚገናኙት የጤና እክል ሲገጥማቸው እንደሆነ በመጥቀስ ይጀምራል። ‹አንዳንድ ሰዎች ወደ ሐኪም ዘንድ የሚሄዱት ሕመም ሲሰማቸው ወይም አዲስ ነገር በአካላቸው ላይ ሲያዩ ነው። ካልሆነም አንድ የተወሰነ ሕክምናን ሲፈልጉ ነው።›› ይላል። በአንጻሩ ደግሞ በገጠማቸው የጤና እክል የተነሳ መደበኛ የሕክምና ክትትል ያላቸው ሰዎች እንዳሉም ይጠቅሳል።
በድንገተኛ ሕመም የተነሳ ወደ ሕክምና ከሚሄዱ ሰዎች ጎን ለጎን፣ የታዘዘላቸውንና የወሰዱትን መድኃኒት በተመለከተ ክትትል ለማድረግ፣ የሕጻናት ሕክምና፣ የነፍሰጡር ክትትልና የመሳሰሉ መደበኛ የጤና ክትትሎች እንዳሉ ያስረዳል። ከእነዚህና መሰል ከሆኑት ውጪ ግን፣ መደበኛ የጤና ምርመራ በየዓመቱ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የሚስማሙ እንዳሉ ሁሉ፣ በኹለትና በሦስት ዓመት ማድረግም በቂ ነው ብለው የሚያምኑ ስለመኖራቸውም ዘገባው ያነሳል።
ዓመታዊ የጤና ምርመራ ምንድን ነው?
መደበኛ የጤና ምርመራ በምን ያህል ጊዜ ልዩነት መካሄድ አለበት ወይም ቢካሄድ ጥሩ ነው የሚለው ላይ የጤና ባለሞያዎች በተለያየ ጊዜ የተለያየ አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል። ኸልዝ ቼክአፕ የተባለ ጤናን የተመለከቱ መረጃዎችን የሚያቀርብ አውታር በገጹ እንዳስነበበው፣ በትንሹ በዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ የጤና ምርመራ ማድረግ ይመከራል። ይህም ብዙዎች የሚስማሙበት ስለመሆኑ ያመላክታል።
በአንጻሩ ደግሞ ‹‹የለም! ዓመታዊ የሕክምና ክትትል በሁሉም እድሜ ውስጥ ላሉ ሰዎች ላያስፈልግ ይችላል። ስለዚህ በእድሜ መሠረት ሊሆን ይገባል።›› የሚል ዕይታ መኖሩንም ይጠቅሳል። በዚህም መሠረት ሕጻናት ልጆችና ወጣቶች ከአዋቂዎች አንጻር የጤና ምርመራ የሚያደርጉበት ጊዜ የተለየ እንዲሆን ይጠበቃል ይላል። ከዛ ከፍ ያሉ ወጣትነት ላይ ከደረሱት ጀምሮ ደግሞ በኹለት ዓመት እንዲሁም ዓመታዊ የጤና ምርመራ ቢያደርጉ ይመረጣል።
በፈቃደኝነት በተደራጁ የጤና ባለሞያዎች የተመሠረተው የጤና ግንዛቤን በማስፋፋት ላይ ያተኮረው ‹የጤና ወግ› የተሰኘ ድርጅት፣ በገጹ ላይ ይህን በሚመለከት አንድ ጽሑፍ አስነብቧል። በዚህም ላይ ስለ ዓመታዊ የጤና ምርመራ ምንነት ሲያስረዳ እንዲህ ይለል፤
‹‹ዓመታዊ የጤና ምርመራ በተለያየ የእድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች የሚደረግ እና ለአንድ በሽታ የመጋለጥ እድላቸውን ቀድሞ ለማወቅ የሚያስችል የምርመራ ዘዴ ነው። እድሜ እና ጾታን መሠረት አድርገው በየዓመቱ እና ከዛም በላይ ሊደረጉ የሚገቡ የምርመራ ዓይነቶች አሉ። እነዚህን ምርመራዎች መረዳት እና መቼ መጠየቅ እንደሚገባ ማወቅ ጤናማ ሆኖ ለመቆየት ያግዛል።››
ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ ለምን ይጠቅማል?› የሚለው ጥያቄ አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው። የጤና ወግ ላይ ባለው ሐተታ መሠረት፣ ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ እንደ ካንሰር እና አንዳንድ በቅድመ ጥንቃቄ ልንከላከላቸው የምንችላቸውን ሕመሞች ለመቆጣጠር ያግዛል።
ኸልዝ ቼክአፕ የተሰኘው ገጽም ባሰፈረው ጽሑፍ ይህን ነጥብ ያነሳል። ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ እንደ ቅድመ መከላከል ይቆጠራል ይላል። በዚህም ተከታታይነት ያለው ምርመራ ስለሚደረግ፣ ብሎም የቤተሰብ የጤና ታሪክ፣ የግል የአኗኗር ሁኔታና የመሰለው ስለሚነሳ፣ ከጤና ጋር በተገናኘ ያሉ ስጋቶች አብረው ሊነሱ ይችላሉ። ከዚህና ከሚደረጉ ምርመራዎች በመነሳትም የጤና ባለሞያዎች በቀላሉ ሊደርሱ ይችላሉ የሚባሉ የጤና እክሎችን ቀድመው መከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
ከዛም ባለፈ አንድ ሰው ተላላፊ ላልሆኑ (በዘር ሊተላለፉ ለሚችሉ) በሽታዎች ያለውን የተጋላጭት ስጋት ለመለየት ያስችላል። ይህም ምልክቶች በብዛትና በስፋት ሳይታዩ አስቀድሞ በሽታው በቶሎ እንዲለይ እና ሕክምና በቶሎ እንዲሰጥ ያስችላል። ይህም በሽታው ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ጉዳት በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ የሚያግዝ ነው።
ከዚሁ ሳይርቅ፤ የተገኘ ወይም ምልክት የታየበት በሽታ ላይ ፈጣንና ተከታታይ የሆነ የጤና ክብካቤ እርምጃና የሕክምና መፍትሔ ለመስጠት ይጠቅማል። በቶሎ መደበኛ ሕክምና ጀምሮ ወደ ቀደመ ጤንነት ለመመለስም በእጅጉ ይረዳል።
‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ› እንዲሉ፤ ወቅትን ጠብቆ የጤና ምርመራ ማድረግ የግል ለውጥን ለመከታተልና ጤናማ የሆነ የአኗኗር መንገድን ለመከተል ትልቅ ሚና አለው። ለምሳሌ ጤናማ አመጋገብን በተመለከተ ከጤና ባለሞያ ተገቢውን ምክር ለማግኘት ብሎም ቀድሞ በማንኛውም አጋጣሚ የተደረገ ምርመራንና የምርመራ ውጤት ያለበትን ሁኔታ ለመከታተል ያግዛል። መድኃኒት እየወሰደ ያለ ወይም ቀደም ብሎ መድኃኒት የወሰደ ሰውም ጤናው ያለበትን ደረጃና ለውጡን ለመከታተል ያስችለዋል።
ከዚህም ሁሉ በላይ ደግሞ ስጋትን ይቀንሳል። ራሴን፣ ወገቤን፣ ጎኔን ወዘተ ያመኛል የሚልና መሰል የተለያዩ ምልክቶችን የሚያይ ሰው፣ የሕመሙ ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል በመገመት ከመጨነቅ፤ ጥርጣሬዎችን ለማጥፋት እንዲህ ያለው የጤና ምርመራ ክትትል ትክክለኛውን የጤናውን ሁኔታ እንዲረዳ ያስችለዋል።
እድሜና ዓመታዊ ምርመራዎች
በምን እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን ዓይነት የጤና ምርመራ ያድርጉ፣ ሐኪምስ ምን ዓይነት ምርመራዎችን ሊያዝ ይችላል የሚለውን በተመለከተ፣ የጤና ወግ ዘርዘር አድርጎ ጠቃሚ ምክሮችን አስፍሯል። ይህንንም እንደሚከተለው እንመልከት።
እድሜዋ/ው ከ18 እስከ 39 ዓመት መካከል የሚገኝ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት፣ በሥራ እና ቤተሰብን በማስተዳደር የተጠመዱ ናቸው ይላል፤ የጤና ወግ ዘገባ። በዚህም የተነሳ ዓመታዊ የጤና ምርመራዎችን ብዙ ጊዜ ሳያደረጉ ያልፋሉ።
በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች ከሚታዘዙት የምርመራ ዓይነቶች መካከል ክብደት እና ቁመት፣ የደም ግፊት ልኬት፣ የዐይን ምርመራ፣ የጆሮ ምርመራ፣ አጠቃላይ የደም ሕዋሶች ምርመራ፣ መሠረታዊ ወይም የተሟላ የሜታቦሊክ ፓነል (የኩላሊት አሠራር፣ የጉበት አሠራር፣ የተለያዩ የደም ውስጥ ንጥረ ነገሮች ምርመራ)፣ የኮሌስትሮል ፍተሻ፣ የታይሮይድ ሆርሞን ምርመራ፣ የስኳር በሽታ ምርመራ፣ በደም ንክኪና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች፣ የሽንት ምርመራ፣ የልብ ምርመራ እንዲሁም የሆድ አልትራሳውንድ ይገኙበታል።
ከዚህ በተጓዳኝ ለሴቶች የሚመከሩ ተጨማሪ ምርመራዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ተጠቃሽ ነው። እነዚህም በተለይ ከ21 ዓመት በላይ ላሉ ሴቶች ቢያንስ በየሦስት ዓመት የሚያደርጉት ምርመራ እንዲሆን ነው የጤና ባለሞያዎች የሚመክሩት።
እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የሚታዘዘው ደግሞ ከቀደሙት በተወሰነ መጠን የተለየ ነው። ምክንያቱ ደግሞ በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል። ስለዚህ ነው የጤና ባለሞያዎች በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ዓመታዊ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚመክሩት።
ለዚህም ጠቃሚ መረጃ ይሰጣሉ የተባሉ ምርመራዎች መካከል፤ ክብደት እና ቁመት፣ የደም ግፊት ልኬት፣ የዐይን ምርመራ፣ የጆሮ ምርመራ፣ አጠቃላይ የደም ሕዋሶች ምርመራ፣ መሠረታዊ ወይም የተሟላ የሜታቦሊክ ፓነል (የኩላሊት አሰራር፣ የጉበት አሰራር ምርመራዎች፣ የተለያዩ የደም ውስጥ ንጥረ ነገሮች ምርመራ)፣ የኮሌስትሮል ፍተሻ፣ የታይሮይድ ሆርሞን ምርመራ፣ የስኳር በሽታ ምርመራ፣ በጾታዊ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ምርመራ፣ የሽንት ምርመራ፣ የልብ ምርመራ እና የሆድ አልትራሳውንድ ተጠቃሽ ናቸው።
በተጨማሪም ከ50 ዓመት እድሜ በኋላ ለሚገኙ ኮሎኖስኮፒ የተሰኘ ምርመራ እንዲደረግ የጤና ባለሞያዎች ይመክራሉ። ይህም ምንም እንኳ እድሜያቸው ከ50 በታች ለሆነም በሕክምና ታሪክ ላይ በመመሥረት ሊያስፈልግ ቢችልም፤ በዓመታዊ ምርመራ ውስጥ ግን ሊካተትና በጤና ባለሞያዎች ሊታዘዝ የሚችል ምርመራ እንደሆነ ነው የጤና ወግ ዘገባ የሚያመላክተው።
በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ተጨማሪ ምርመራዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ማሞግራም፣ የኦስቲዮፖሮሲስ ምርመራ (Bone mineral density testing) ይጠቀሳሉ። እድሜያቸው 65 እና ከዛ በላይ ለሆኑ ሴቶችም የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ አለ። በተጓዳኝ ለወንዶችም ሊታዘዙ ከሚችሉ ተጨማሪ ምርመራዎች ውስጥ የፕሮስቴትና የፕሮስቴት ካንሰር ምርመራ የሚዘነጋ አይደለም።
በዚህ መሠረትና ሐኪሞች እንደሚሰጡት ትዕዛዝ ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ በብዙ መልኩ ጠቃሚ መሆኑ አያጠራጥርም። አዳጊ በሆነችና ብዙ በድህነት ውስጥ ያለ ሕዝብ በሚገኝባት አገርም፣ እንዲህ ያለው ቅድመ ምርመራ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ብዙዎች ያነሳሉ።
ይህንን እና መሰል ዓመታዊ የጤና ምርመራ ለማድረግ የገንዘብ አቅም አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ነው። በኋላ ሕመም ሰውነት ላይ ሲሠለጥን ለመታከምና ለመዳን ከሚያስፈልገው ወጪ አንጻር ግን አነስተኛ ነው። ስለዚህም ለቅድመ ጥንቃቄ የሚያግዝ በመሆኑ በቅናሽ ዋጋ ምርመራ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የጤና ጣቢያዎችና የሕክምና ማእከላት በተቻለ አቅም አገልግሎቱን ለማግኘት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ የሕክምና ባለሞያዎች ይመክራሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



