ጦርነቱ እና መዋጮ ያደቀቀው የአማራ ክልል ሕዝብ

0
1137

ኹለት ዓመት ባስቆጠረው የሰሜኑ ጦርነት የሦስቱን ክልሎች ያህል የደቀቀ እንደሌለ ብዙ ማሳያዎች ይቀርባሉ። አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች በተራዘመው ጦርነት ሰፊ የሆነ ማኅበራዊ እና አኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ነው የሚነሳው። ጦርነቱ ለከፋ አስተዳደራዊ ክስረት ሳይዳርጋቸው እንዳልቀረም ይታመናል።

ትግራይ ክልል ውስጥ የባንክ፣ የስልክና የመብራት፣ አገልግሎት አለመኖሩ ይታወቃል። ትምህርት ቤቶች ዝግ ናቸው፣ የጤና ተቋማትም እንደ ወትሮው በሙሉ አቅማቸው ይሠራሉ ተብሎ አይታሰብም።

ክልሉ በኹሉም ረገድ ሰፊ ጉዳት እንዳስተናገደ፣ ወደፊትም ለብዙ ዓመታት የሚቀጥል ችግር እያከማቸ መሆኑን ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ታሪካዊ ክስተቶችን በማውሳት የሚናገሩ አሉ።

አፋር ክልል የደረሰው ሰቆቃም እንዲሁ ጥልቅና ሰፊ መሆኑ ይነገራል። በክልሉ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ እንዲሁም በሰው ሕይወት ጭምር አያሌ ኪሳራዎች እንደደረሱ በተደጋጋሚ ይፋ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መገኛ የሆነው፣ በርካታ በመማር ላይ ያሉ ታዳጊዎችና ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ያሉበት አማራ ክልል በዚህ ጦርነት እያጋጠመው ስላለው የተለየ ድቀት ብዙ የማኅበረሰቡ አካላት የሚያነሱት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ለዚህ መነሻ የሆነው ደግሞ ጦርነቱን በሙሉ ትከሻው የተሸከመ ሆኖ መታየቱ ነው። በሰው ኃይል ረገድ ሚሊሻ፣ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ፣ ወጣት እየተባለ ወደ ግንባር ሲሄድ መቆየቱን በማንሳት አሁንም ቢሆን በየጦር ግንባሩ ይኼው ሁኔታ የቀጠለ ስለመሆኑ በግልጽ ይታወቃል።

በገንዘብ በኩልም ኹለት ዓመት ሙሉ ያለማቋረጥ ከእያንዳንዱ የክልሉ ነዋሪ ለጦሩ ተብሎ ቀለብ ይሰፈራል፣ ገንዘብ ይዋጣል። ቀለብ ሰፈራውና ገንዘብ መዋጮው የአንዴ ጊዜ ብቻ አይደለም። እየደጋገመ ይመጣል። ይህ ደግሞ የክልሉን ሕዝብ እጅግ ያሰለቸ ስለመሆኑም ነው በስፋት የሚነገረው።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኝ አንድ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ (ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸውን የማንጠቅሰው) ‹‹በወረዳው ያሉ ኹሉም ቀበሌዎች ለጦሩ ገንዘብና የእርድ እንስሳት እንዲያዋጡ ግዴታ የተጣለባቸው በመሆኑ፣ እኔ በማስተዳድረው ቀበሌ ውስጥ ይህን እንደማላስፈጽም በግልጽ ተናግሬያለሁ›› ይላሉ።

‹‹የተቃወምኩበት ምክንያትም ነገሩ በጣም ስለተደጋገመና ሕዝቡም ይህን የማድረግ አቅም እንደሌለው ስለምረዳ ነው።›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹የተጣለው መዋጮ ከቀበሌው ሀብት ላይ እንዲፈጸም ወረዳው ያዘዘ ቢሆንም፣ እኔ ግን ለቀበሌው መንገድና ሌሎች አስፈላጊ የተፋሰስ ሥራዎች መሠራት ስላለባቸው ሀብት የለም በማለት ሐሳቤን አቅርቤአለሁ›› ነው ያሉት።

‹‹የቀበሌው ማኅበረሰብ ለረዥም ጊዜ ሲጠይቀው የኖረ የመንገድ ፕሮጀክት ዘንድሮ ተፈጻሚ ካልሆነ ቀጣይም የሚሆንበት መንገድ ጠባብ ነው። በዚያ ላይ እርከንና ሌሎች ሥራዎች ካልተሠሩ አርሶ አደሩ በቀጣይ ለከፋ ችግር ይጋለጣል›› ሲሉም ያስረዳሉ።

ዋና አስተዳዳሪው ‹‹ደሙን አፍስሶ አገር ለሚያቆም ሠራዊት ምንም ቢደረግለት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን ወይ በዚህ ዘዴ የሚጠቀሙ አጭበርባሪ አካላት አሉ፣ ካልሆነም ጉዳዩ የኹሉም የአገሪቱ ሕዝብ ድርሻ መሆን አለበት።›› ባይ ናቸው።

ብዙ ሰው መክፈል የማይችልበት ሁኔታ ላይ መድረሱንና፣ ነገር ግን ግዴታ በመሆኑ ብዙዎች እየተሰቃዩ መሆኑም መታወቅ ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል።

የወረዳው ሕዝብ ከመጀመሪያ ዙር ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ከደጀንነት እስከ ግንባር ድርሻውን እየተወጣ ነው። ለጥምር ጦሩ በአንደኛው ዙር የእርድ በሬዎች፤ በኹለተኛው ዙር ደግሞ በርከት ያለ ኩንታል በሶ፣ ድርቆሽ፣ እንዲሁም በግና ፍየል ወደ ግንባር ልኳል።

ለሦስተኛ ጊዜም ለሠራዊቱ በማለት ከ20 ኩንታል የበለጠ በሶ እና ድርቆሽ፣ 10 ኩንታል ቆሎ፣ በጎችና እና ፍየሎችን ወደ ግንባር ልኳል።

ዞኑም (ምሥራቅ ጎጃም) በዞኑ ከሚገኙ ከተማ አስተዳደርና ወረዳዎች የተሰበሰበውን በዚህ ሳምንት በዋግ ኽምራ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት 376 በጎች እና 145 ፍየሎችን ጨምሮ ምግብ እና ምግብ ነክ ቁሶችን ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

በክልሉ ያሉ ሌሎች ዞኖችም ተመሳሳይ ሥራ እያደረጉ ነው ያሉት፤ በየጊዜው ከሕዝቡ የተሰበሰበውን ድጋፍ ለጥምር ጦሩ ማስረከባቸውን ሲገልጹ ይታያል። ይህ መዋጮ እንደሚቀጥል እንጂ እንዳበቃ አይደለም የሚታወቀው። ይህም ለሕዝቡ ሌላኛው የኢኮኖሚ ድቀት ሆኗል ሲሉ የቀበሌ ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል።

እርሳቸው የቀበሌያቸው ማኅበረሰብ ከዚህ በኋላ መዋጮ መክፈል እንደማይችል በመግለጻቸው በበላይ አመራሮች ጥርስ የተነከሰብኝ ይመስለኛል ብለዋል። ‹‹ሆኖም ግን አመራሮች የበላይ አለቆቻቸውን ለማስደሰት በሚል የሚያደርጉት መስሎ ከተሰማኝና ሕዝቡም በሌለው አቅም እየተበዘበዘ መሆኑን ከተረዳሁ ከመቃወም ወደ ኋላ አልልም።›› ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

ከመንግሥት ሠራተኛውም ከደሞዙ እንደሚቆረጥ አውስተዋል። ጉዳዩ የአንድ ክልል ብቻ ባለመሆኑም ጥምር ጦሩን የሰው ኃይል ከማዋጣት ጀምሮ ለጥምር ጦር የሚሆነውን አስፈላጊ ወጪም በመሸፈን ኹሉም ክልሎች እኩል ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥትም ‹‹ለወቅታዊ ሰላምና ደኅንነት ማስከበሪያ›› የሚል የገቢ ደረሰኝ አዘጋጅቶ ጥሬ ገንዘብ እየሰበሰበ ይገኛል። በዚህ የተነሳም ብዙዎች ከጦርነት የተረፈውን ሕዝብ ሥራ እንዳይሠራ በመከላከያ ሥም ገንዘብ አምጡ በማለት እያሰቃዩት ይገኛሉ በማለት ቅሬታቸውን ሲገልጹ ይስተዋላል።

ለመከላከያና ለልዩ ኃይል አዋጡ የሚለውን ተደጋጋሚ ግዴታ ለመሸሽም በወሳኝ የአምልኮ ቀን ሳይቀር ወደ እምነት ተቋማት አለመሄድን የመረጡ ሰዎች እንዳሉም አዲስ ማለዳ ተገንዝባለች።

ሕዝቡን በዚህ ልክ እንዲማረር ያደረገውም መዋጮ ተደጋጋሚ መሆኑና የማኅበረሰቡ የመክፈል አቅም እየቀነሰ በመሄዱ መሆኑ ከብዙዎች አንደበት ይደመጣል።

የክልሉ መንግሥት ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ በጀቱን ለጦርነት፣ ሕዝቡም ጥሪቱን፣ ጉልበቱን እና ልጆቹን እየገበረ ነው በማለት ጦርነቱ ክልሉን በተለየ ሁኔታ እያደቀቀው እንደሆነ በበርካቶች ይገለጻል። ጦርነቱ አጠቃላይ የአገር እዳ ሆኖ ሳለ ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ፣ ከሲዳማ፣ ከደቡብ፣ ከአዲስ አበባ ወይም ከሌሎች የአማራ ክልል የሚያደርገውን ሩብ ያህል ቀለብ ሲቆረጥ፣ ወታደር ሲዘምት፣ ገንዘብ ሲዋጣ አይታይም በማለትም ቅሬታ የሚያሰሙ አካላት ጥቂት አይደሉም።

‹‹እርግጥ ነው ሶማሌ ክልል አልሸባብን በመዋጋት ትልቅ አገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ኦሮሚያ ክልልም በጉያው ከሚንቀሳቀሰው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ጋር እየተፋለመ ነው። ይህም ቢሆን ግን በአገር ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ የደቀነውንና በቀላሉ መቋጨት ያልተቻለውን አውዳሚ የሰሜኑን ጦርነት አፋር ክልል ብቻውን የሚታገልበት፣ የአማራ ክልልም ብቻውን የሚደቅበት ስሌት ከየት የመጣ ነው?›› የሚል አስተያየትም ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ከሰጡ ሰዎች ተነስቷል።

ሥማቸው እንዲገለጽ ባለመፈለግ ለዚህ ዝግጅት አስተያየታቸውን ከሰጡ ሰዎች መካከል አንድ ወጣት፣ ‹‹የአማራ ክልል በሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግ አገዛ ትልቅ የሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መቀንጨር አጋጥሞታል። አሁንም በጦርነቱና ከዚያ ጋር በተያያዘ መዋጮ ከዚያ የሚብስ እንጂ የማይሻል ድቀት እያስተናገደ መሆኑ መታወቅ አለበት›› ይላል።

‹‹ሕዝቡ ሲኖረው በራሱ ፈቃድ ደስ ብሎት ድጋፍ ሲያደርግ ዐይተነዋል። አሁን ከሆነ ግን እያስገደዱ እየበዘበዙት ነው። በመገናኛ ብዙኀን ሕዝቡ ለወገን ጦር ይህን ያህል ድጋፍ አደረገ እያሉ ሲቀልዱ የሚያንገበግብ ጉዳይ ነው›› ካለ በኋላ፣ ‹‹እስከመቼ ነው ግን የክልሉ ሕዝብ በመዋጮ የሚቸገረው?›› ሲል ይጠይቃል።

‹‹መንግሥትስ መቼም ነጋሪ አያሻኝም ካለ ቆይቷል። ሕዝቡን እንወክላለን የሚሉ አካላት ለምን ዝም ይላሉ? ሕዝቡስ ለምን እንደ አገር በመጣው ዕዳ እኛ የተለየ እየተጎዳንና እየተበዘበዝን ነው በማለት አይሞግትም?›› ስትል አስተያየቷን የሰጠች ሌላ ወጣት እንስትም አለች።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ‹‹በክልሉ በዚህ ወቅት ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋም፣ መንገድ እንዴት ይገነባል? የፈረሰውን መልሶ መገንባት እኮ ፈታኝ ሆኗል። መሆን የነበረበት ግን የፈረሰውን መገንባት ብቻ ሳይሆን በርካታ ተጨማሪ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ፣ የመብራትና የውሃ መሠረተ ልማቶችን መገንባት ነበር። የሥራ ቅጥር የበፊቱን ያህል የለም። ዝውውርና እድገት ከሰማይ የራቁ ናቸው። መሠረተ ልማት ግንባታ ታሪክ የሆነ ይመስላል። የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ እንጂ ተገንብቶ ሲመረቅ ብዙም አይታይም። ቢኖርም ከስንት አንድ ነው።›› ይላሉ።

‹‹ይህ የክልሉ አመራር ክፍተት ነው። ሕወሓትን የመመከት ኃላፊነት ለአንድ ወይም የኹለት ክልል የሚተው አልነበረም። ስለዚህ ጉዳይ ሲነሳ እበሳጫለሁ፤ ማውራት አልፈልግም።›› በማለት ሌላ የክልሉ ነዋሪ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።

ሕዝብ ፈልጎ እና ደስ ብሎት አንዴ ወይም ኹለቴ የታዘዘውን ሊሰጥ ይችላል። በየጊዜው ሲሆን ግን እጦት ይፈጠራል። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀወስ ያመጣል። በደንብ ይታሰብበት የሚሉም ብዙዎች ናቸው።

ድጋፉ የት ነው የሚገባው?

በየጊዜው የተለያየና ብዙ ድጋፍ የሚሰበሰብ ቢሆንም፣ ሠራዊቱ ግን ብዙ ጊዜ ደረቅ ብስኩት በልቶ ነው የሚዋጋው የሚሉ ቅሬታዎች በስፋት ሲስተጋቡ ይታያል።

በግልጽም የሚሰበሰበው ድጋፍ በሌቦች ይዘረፋል በማለት የሚናገሩ አሉ። ለሠራዊቱ መድረስ ያለበት 80 ፍየል ከሕዝብ የተረከበ አካል በማግስቱ 40ዎቹን ፍየሎች የት እንዳደረሳቸው ግራ ገባን እስከሚባል ድረስ ወሬዎች ሲናፈሱ ሰንብቷል።

ያለማቋረጥ ድጋፍ ይደረጋል። በአማራ ክልል ከእያንዳንዱ ሕዝብ ከሚሰበሰበው በተጨማሪ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮችና ከፌዴራል የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ከግል ድርጅቶች ድጋፍ በስፋት ይሰበሰባል።

ይሁን እንጂ በዚህ ሰበብ ብዙዎች ያለአግባብ ከብረዋል፤ ሕዝቡ እየተበዘበዘ ነው። ድጋፉ በትክክል ለጦር ሠራዊቱ አይደርስም። ይህም የሆነው በሚመለከተው አካል ጥብቅ ቁጥጥር ስለማይደረግ ነው የሚለው የሕዝብ ቅሬታ ጦርነቱ ከተጀመረ ሰሞን ጀምሮ እስካሁንም እንደቀጠለ ነው።

በተለየ ሁኔታ ደግሞ ጦርነቱም ድጋፉም አማራ ክልል ላይ የበረታ ነው የሚሉ አካለት ብዙ ናቸው። ይህም የክልሉን ሕዝብ ክፉኛ እየበዘበዘው ይገኛል። አንዱ አካባቢ ስንዴ እየለማ፣ ሌላው አካባቢ በስንቅ ዝግጅት ዓመቱ የሚያልፍበት ሁኔታ መኖር የለበትም። ኹሉም የአገሪቱ ሕዝብ የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ነው የሚሉት፤ እነዚህ አካላት።

የአማራ ክልል ሕዝብ ጦርነቱ ከአጠገቡ እንዲርቅ እና አስተማማኝ ሰላሙን እንዲያገኝ ኹለት ዓመት ሙሉ ቀለብ ሲሰፈር፣ ገንዘብ ሲያዋጣ ከርሟል። ግንባር ተገኝቶም እየተዋጋ ነው።

ይሁን እንጂ የደረሰበት እና እየደረሰበት ያለው ጉዳት እያደረገ ካለው ድጋፍ ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም ነው በማለት፤ የፌዴራልና የክልሉ ባለሥልጣናት በጦርነትና በመዋጮ እየደቀቀ ያለውን የክልሉን ሕዝብ በአፋጣኝ እንዲታደጉ ብዙዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here