የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች የስድስት ወር አበል አልተከፈለንም ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል።
ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ በኮርፖሬሽኑ ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ክፍል አማካኝነት ከታህሳስ 23/2014 ጀምሮ የካምፕ ማሻሻያ አበል እንደሚከፈላቸው በደብዳቤ ተገልጾላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ አበል የሚታሰብበት ሥራ ታስቦ አልተከፈላቸውም።
አዲስ ማለዳ የተመለከተችው ደብዳቤ ‹‹ከዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ጽሕፈት ቤት በ5/6/2014 በተጻፈልን የውስጥ መጻጻፊያ ፕሮጅክቶችን ውጤታማ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ ላሉ ሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች የካምፕ ማሻሻያ አበል እንዲከፈላቸው በስትራቴጅክ ማኔጅመንት መወሰኑን በመግለጽ ከታህሳስ 23/2014 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ መግለጹ ይታወቃል። በመሆኑም ከላይ በተገለጸው መሠረት እንዲፈጸም እናሳስባለን።›› ይላል።
ሠራተኞቹ የካምፕ ማሻሻያ አበሉን ማግኘት የጀመሩት ከሐምሌ ወር ጀምሮ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከጥር እስከ ሰኔ ወር 2014 ያለው ግን አልተሰጠም ብለዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዳሉት፤ ለአንድ ሠራተኛ በቀን 100 ብር እንዲሚከፈል በኅብረት ሥራ ማኅበሩ ጸድቆ ነበር። እያንዳንዳቸውም የአበል ተጠቃሚ ሠራተኞች በወር ሦስት ሺሕ ብር አጠቃላይ በስድስት ወር ውስጥ 18 ሺሕ ብር አበል አልተከፈላቸውም።
የሠራተኞቹን ቁጥር ተቋሙ ሲጠየቅ ግን እንደማያውቅ ነው ምላሽ የሰጠው። ሠራተኞቹ ለተቋሙ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ዋና ኃላፊዎቹ ‹‹አልተፈቀደም›› የሚል ምላሽ እንደሚሰጧቸው አንስተው፤ የሠራተኞች ማኅበሩ ግን ይከፍላሉ ሲላቸው እንደቆየ አብራርተዋል።
በኮርፖሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ጥንፉ ሙጬ በስትራቴጂክ ማኔጅመንት የተወሰነው የካምፕ ማሻሻያ አበል በኅብረት ሥራ ማኅበሩ ባለመጽደቁ ነው ክፍያ ያልተፈጸመው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሥራ አስኪያጁ በተያያዘም ‹‹በጉዳዩ ዙሪያ ኅብረት ሥራ ማኅበሩ ውይይት አላደረገም፤ ስትራቴጂክ ማኔጅመንቱ ብቻ በቅን ልቦና ነው የወሰነው። የአበሉ መጠንም አልገለጸም›› ብለዋል።
በታህሳስ ወር 2014 በስትራቴጂኪ ማኔጅመንቱ በኩል እንዲከፈል የተወሰነው አበል እንደገና በኅብረት ሥራ ማኅበሩ ውይይት ተደርጎበት ከሐምሌ ወር 2014 ጀምሮ ለ2 ሺሕ 300 ገደማ የኮርፖሬሽኑ ቋሚ ሠራተኞች አበል መስጠት እንደተጀመረ ነው ያስረዱት።
ከሐምሌ ወር ጀምሮ ለቋሚ ሠራተኞች እየተከፈለ ያለውን አበል በተመለከተም ሥራ አስኪያጁ ደረጃ በደረጃ ገልጸዋል። በዚህም በአዲስ አበባ ዙሪያ (በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት) ለሚገኙ ሠራተኞች ከደረጃ አንድ እስከ ስድስት በቀን 90 ብር፤ ከደረጃ ሰባት እስከ ዘጠኝ በቀን 100 ብር እንዲሁም ከደረጃ 10 እስከ 13 ያሉ ሠራተኞች በቀን 110 ብር አበል ከደመወዝ ጋር እየተከፈላቸው ነው ተብሏል።
እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጪ (በሌሎች የክልል ከተሞች) ላሉ ሠራተኞች ደግሞ የምግብ ማሻሻያ የአበል ከደረጃ 1 እስከ 6 በቀን 160፤ ከደረጃ 7 እስከ 9 በቀን 170 ብር እንዲሁም ከደረጃ 10 እስከ 13 ለሚገኙ ሠራተኞች በቀን 180 ብር ከደመወዝ ጋር አብሮ እየተከፈለ ነው።
ከአዲስ አበባ ውጪ ላሉ 1 ሺሕ 927 ሠራተኞች ከ10 ሚሊዮን 190 ሺሕ ብር በላይ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ለሚገኙ ቀሪ ሠራተኞች ከአንድ ሚሊዮን 318 ብር በላይ መከፈሉን ጥንፉ አክለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



