ከፋይናንስ ተቋማት በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ለሚገኝ ብድር ወጥ እና ኹሉን ዐቀፍ የኤሌክትሮኒክ የምዝገባ ሥርዓት መዘርጋቱ ተገለጸ።
ሥርዓቱ ‹‹በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሠረት የዋስትና መብት አዋጅ ቁጥር 1147/2019››ን ተፈጻሚ ለማድረግ ነው የተባለ ሲሆን፣ በዋናነት የፋይናንስ ዘርፉን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ሥማቸውን እንዲገለጽ ያልፈለጉ በብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አዲስ ሥርዓት መሆኑ በተገለጸው በዚህ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ፣ የፋይናንስ ተቋማት ለሰጡት ብድር ዋስትና ብለው በያዙት ንብረት፣ ማንኛውም አካል ያለመዝጋቢው እውቅና ሊገበያይ ቢሞክር በራሱ ላይ ኪሳራ እየፈጸመ መሆኑን ማወቅ አለበት ነው ያሉት ኃላፊው።
ምክንያቱም አስቀድሞ ለብድር ዋስትና የተመዘገበውን ንብረት ሌላ ሰው ቢገዛው፣ አበዳሪው ንብረቱን አድኖ የመውሰድ መብት አለው ብለዋል።
ይህ የሚሆነው ግን ተንቀሳቃሽ ንብረቱ በዚህ ሥርዓት ከተመዘገበ ነው ያሉት ኃላፊው፣ አበዳሪው የፋይናንስ ተቋም ንብረቱ ይያዝልኝ ብሎ ቢጠይቅ፣ ብሔራዊ ባንክ ተበዳሪው የወሰደውን ብድር መመለስ ባለመቻሉ ያስያዘው ንብረት እንዲያዝ ብሎ ለፖሊስ ደብዳቤ የሚጽፍ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም በአዋጅ የተቀመጠው ሕግ የሚለው ማንኛውም አበዳሪ ተንቀሳቃሽ ንብረት መያዣ አድርጎ ብድር ከሰጠ፣ ሕጉ በሦስተኛ ወግን ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ስለሚል፣ በዚያ ንብረት ላይ እገዳ ተደርጓል ማለት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ምዝገባ ካልተከናወነ ግን ሕጉ በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ጠቁመው፣ የምዝገባ ሥርዓቱ ይህን ንብረት አስመዝግቤ ከዚህኛው አበዳሪ ይህን ያህል መጠን ገንዘብ ተበድሬያለሁ የሚለውና የተበዳሪው ማንነት የሚመዘገብበት ኤሌክትሮኒክ መዝገብ (collateral registration system) ነው ብለዋል።
ለዚሁ አገልግሎት የሚውለው ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት በኩል እንደተገዛና ሥራ እንደጀመረ አንስተው፣ ወደፊት ስለዚሁ የምዝገባ ሥርዓት አገር ዐቀፍ እወጃ ይደረጋል ሲሉ ተደምጠዋል።
የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ወረደቃል ገብረክርስቶስ በበኩላቸው፣ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓቱ የሚከናወንበት ሰርቨር በ1 ሚሊዮን 460 ሺሕ ዶላር ከውጪ አገር ተገዝቶ የገባ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ሰርቨሩ የሶፍትዌር እና የሃርድዌር ግዢ እንዲሁም የተከላ ሥራ (installation) ነው ያለው ያሉት ኃላፊው፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚሠራ ትልቅ መሣሪያ ነው ብለውታል።
ስለሆነም ከብድር ጋር ተያይዞ፣ ተበዳሪዎች በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከየትኛው የፋይናንስ ተቋም ብድር እንደወሰዱና ስለብድሩ ሁኔታ ወጥ የሆነ የመረጃ ቋት ሊኖር ስለሚገባ ብሎም ብሔራዊ ባንክ ይህን ለመቆጣጠር በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን በመኖሩ፣ የኤሌክትሮኒክ መመዝገቢያ መሣሪያውን በኃላፊነት ወስዶ እንደሚያስተዳድረው ጠቁመዋል።
ለዋስትና በተያዘ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በተወዳዳሪ ባለመብቶች የሚነሳ የቀዳሚነት መብትን ለመወሰን የሚያስችል አንድ ወጥና ኹሉን ዐቀፍ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ እንዲሁም ዋስትናው የተጠበቀ ዘመናዊ የብድር ሥርዓት እንዲኖር እና ግለሰቦችና ተቋማት ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በማስያዝ ሥራ ላይ የሚውል አዲስ ካፒታል ማግኘት እንዲችሉ በሚል በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት ‹‹በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሠረት የዋስትና መብት አዋጅ›› መዘጋጀቱ ይታወቃል።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



