ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሕንድ የተጓዘ የሕንድ ዜግነት ያለው ግለሰብ ሙምባይ ኤርፖርት ሲደርስ በተደረገ ፍተሸ 16 ኪሎግራም ወርቅ እንደተያዘበት ኤ ኤን አይ ዘግቧል።
ባሳለፍነው ሐሙስ ሙምባይ ዓለም ዐቀፍ ኤርፖርት እንደደረሰ በተካሄደ ፍተሻ ግለሰቡ ከኢትዮጵያ ካጓጓዘው 16 ኪሎ ወርቅ ጋር መያዙ ታውቋል። የግለሰቡ ማንነትም ሆነ የተነሳበትን ፍተሻ እንዴት እንዳለፈ ባይነገርም በመዳረሻው ላይ መያዙ ተነግሯል።
ወደ ሕንድ በተደጋጋሚ ወርቅ ደብቀው ለማስገባት የሚሞክሩ እንደሚያዙ የተነገረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ከሙምባይ አውሮፕላን ማረፊያ ብቻ አራት ሰዎች ወርቅ ደብቀው ሊያስገቡ ሲሉ ተይዘዋል። ኹለቱ ከዱባይ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሱዳን ወደ ሕንድ ለማስገባት ሲሞክሩ የተያዙ ናቸው ተብሏል። ወርቁን ደብቀው ለማስተላለፍ ሰውነታቸው ውስጥ እንደቀበቶ በሚሽከረከር መያዣ ቀበቶ አልያም በልብሳቸው ውስጥ እንደሚደብቁ ተነግሯል።
ወርቁንም ሲያስተላልፉ በዱቄት መልክ አልያም የተፈጥሮ መልኩን እንደያዘ በተለያየ ቅርጽ በማድረግ እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል። ከኢትዮጵያ 16 ኪሎ ግራም ወርቅ ይዞ የወጣው ሕንዳዊ የትኛውን አየር መንገድ እንደተጠቀመ በዜናው አልተጠቀሰም።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015


