የቱርክ አስመጪዎች ብረትና ብረት ነክ እቃዎችን ለኢትዮጵያ ሊያቀርቡ ነው

0
681

የቱርክ ብረት አስመጪዎች ብረትና ብረት ነክ እቃዎችን ለኢትዮጵያ ለማቅረብ መስማማታቸውን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።

አቅርቦቱ የሚከናወነው አሊጋስ፣ ኢዝሚርና እስክንድሪያ ከተሰኙ የቱርክ ወደቦች በመነሳት ብረትና ብረት ነክ እቃዎችን ከሚያቀርቡ ብረት አስመጪዎችና ወኪላቸው አርካስ ጋር በተደረሰ ስምምነት መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለአቅራቢዎች ቀልጣፋ አገልግሎትና በቅናሽ ዋጋ በጂቡቲ ወደብ መዳረሻዎች ለማጓጓዝ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያለው።

ኢትዮጵያ በቂ የብረት ምርት ማቅረብ እስከምትችል ድረስ በቱርክ አገር ብረት ከሚያቀርቡ አስመጪዎች ፍላጎታችንን ያማከለ አቅርቦት እንዲኖር በማጓጓዝ ረገድ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ሲልም ድርጅቱ አክሏል።

በመሆኑም ለቱርክ ብረት አቅራቢዎች የማጓጓዣ ቅናሽና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል የተባለ ሲሆን፣ የብረትና ብረት ነክ እቃዎች የጭነት አገልግሎት በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ተቀዛቅዞ መቆየቱ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ወደ ቱርክ ወደቦች የራሷን መጫኛ መርከቦች በማሰማራት የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማሳደግ እየሠራች መሆኑም ነው የተገለጸው።

ድርጅቱ በመደበኛነት ወደ ቱርክ መጫኛ ወደቦች የራሱን መርከቦች እና ተጨማሪ ቻርተር መርከቦችን አሰማርቶ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማሳደግ እየሠራ እንደሆነም ገልጿል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት 51 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here