በኢትዮጵያ የወሲብ ቪዲዮዎችን የሚያሰራጩ ድረ ገጾችን ለማሳገድ ፊርማ ማሰባሰብ መጀመሩን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ለሚዲያ ተቋማት ተናግረዋል ተብሏል።
በአንድ ግለሰብ ተነሳሽነት የተጀመረዉ እንቅስቃሴው አሁን ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በሆኑ 15 በሚደርሱ ሌሎች አባላትም ድጋፍ ማግኘቱን ብስራት ሬድዮ ዘግቧል።
የማስታወቂያ ባለሙያ በሆነዉ ዓለማየሁ አጥናፍሰገድ በተባለ ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ድረገጾቹን ለማሳገድ፣ እንዲሁም በሕጻናት እና ወጣቶች አእምሮ ላይ የሚያደርሰውን ጫና በማስተማር እና ማኅበረሰብን የማንቃት እንቅስቃሴ አንድ ብሎ መጀመሩ ተነግሯል። በበርካቶች ተቀባይነትን በማግኘት ላይ ያለው ግለሰቡ፤ የሚያስተላልፋቸዉን መልእክቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ፈትሂ ማህዲ ተመልክተው አጋርነታቸውን እንዳሳዩት ገልጿል ነው የተባለው።
ጉዳዩ ከመንግሥት በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ያለው ግለሰቡ፣ ይህን ዓላማ የሚደግፉ አካላት በፊርማ ማሰባሰቡ ላይ እንዲሳተፉ እና ጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዲሰጠው የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያድርጉ ሲል ጥሪ አቅርቧል ተብሏል። የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባሉ ፈትሂ የወሲብ ምስሎቹን በኢትዮጵያ ለማሳገድ ፊርማ ማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን መናገራቸው ተዘግቧል። እንቅስቃሴው እስካሁን ድረስም 15 በሚጠጉ በምክር ቤቱ አባላት ድጋፍ ማግኘቱንም ተነግሯል።
ተመሳሳይ እገዳን እና ሕግን ከደነገጉ አገራት አንዷ ከሆነችው ዩጋንዳ እና ቱርክ፤ በሕጉ ዙሪያ ያስቀመጧቸውን ድንጋጌዎች ለሕዘብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ማስገባታቸውም የምክር ቤቱ አባል መናገራቸው ተጠቅሷል።
በዓለማችን ላይ በርካታ አገራት ክልከላውን በመተግበር ትውልዱን በመጠበቅ ላይ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ ሰሜን ኮሪያ በተለምዶው ቪፒኤን በተሰኘዉ (virtual protected network) አማካኝነትም ዜጎች ድረገጾቹን እንዳይጠቀሙ ካገዱ አገራት ትጠቀሳለች።
ሌላኛዋ የሩቅ ምሥራቅ ቻይና ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ድረገጾቹን ሳንሱር ከሚያደርጉ አገራት ውስጥ ስትሆን፣ የአገሪቷ አደገኛ አጥር በተሰኘ ፕሮጀክት ድረገጾቹ ላይ ቁጥጥር እና ክትትል ታደርጋለች ተብሏል።
በተጨማሪም ኳታር፤ ሶርያ፤ ቱርክሜኒስታን፤ ፓኪስታን፤ ቱርክ፤ ኦማን፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ጎረቤት አገር ኤርትራ ድረገጾቹ ላይ እገዳ እና ቁጥጥር የሚያደርጉ አገራት ናቸው። ቼንጅ ዶት ኦርግ ላይ መሰባሰብ በጀመረዉ ፊርማ እስካሁን ከ400 በላይ ሰዎች ድጋፋቸዉን መግለጻቸው ተመልክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015


