የሀብት መጠናቸውን ደብቀዋል የተባሉ የ17 ሀብት አስመዝጋቢ ባለሥልጣናትን ጉዳይ ለተጨማሪ ምርመራ ለፍትሕ ሚኒስትር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ማስተላለፉን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
ለተጨማሪ ምርመራ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተላልፈው የተሰጡ ባለሥልጣናት፣ ኮሚሽኑ ባደረገው የሀብት አስመዝጋቢዎች የሀብት ማረጋገጥ ሥራ ካስመዘገቡት ሀብት መጠን ውጪ ሀብት ተደብቆ የተገኘባቸው ናቸው ተብሏል። ባለሥልጣኖቹ ያስመዘገቡት የሀብት መጠን እና ከምዝገባ በደበቁት የሀብት መጠን መካከል ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት የታየባቸው ናቸውም ተብሏል።
ባለሥልጣኖቹ ኮሚሽኑ ባገኘው መረጃ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎባቸው ክስ እንዲመሠረትባቸው መረጃቸው ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መላኩን አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ምንጮቿ ሰምታለች። ሀብት አስመዝጋቢዎች በውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ያሉ የመንግሥት አመራሮች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ የማጣረት ሥራውን ሠርቶ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስተላልፏል።
ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተላልፈው የተሰጡ ባለሥልጣናት የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ያስመዘገቡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሰነድ ሲመረምር ከፍተኛ ሳይመዘገብ የቀረ ሀብት በማግኘቱ ሲሆን፣ ከሀብት ምዝገባ የደበቁት ሀብት ቤት፣ መኪና እና መሬት (ቦታ) እንዲሁም የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚገኝበት ተመላክቷል።
ኮሚሽኑ ባደረገው የሀብት ምዝገባ ትክክለኝነት ማረጋገጫ ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ባላቸው የመንግሥት ተቋማት ላይ ባካሄደው የማረጋገጥ ሥራ፣ ከፍተኛ ሀብት የደበቁ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸው አስተላልፏል። ኮሚሽኑ የሚያስተላልፋቸውን ባለሥልጣናት ጉዳይ የወንጀል ምርመራው የሚካሄደው በፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ውስጥ በሚገኘው የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክተር ጀነራል ነው።
በሌላ በኩል፣ ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ ክስ እንዲመሠረትባቸው ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያስተላለፋቸው፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት የደበቁ 23 የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የወንጀል ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከፍትሕ ሚኒስቴር ምንጮቿ ሰምታለች።
ከሚሽኑ የተደበቁ ሀብቶችን ለመለየት የገቢ ምንጭና ተቀማጭ ገንዘብ ለማረጋገጥ ከመንግሥት እና የግል ባንኮችን መረጃ የተጠቀመ ሲሆን፣ የተደበቁ የመኪና፣ የቤትና የመሬት መረጃዎችን ደግሞ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ማረጋገጡ ተመላክቷል።
ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት የደበቁ አካላት ላይ ምርመራ እንዲደረግ እና በተገኘው የምርመራ ውጤት ክስ ተመሥርቶባቸው በሕግ እንዲጠየቁ ያደረገው ጥረት፣ በመንግሥት ውሳኔ እንዲቋረጡ በመደረጉ እና የመመርመርና ክስ የመመሥረት ሥልጣን ያላቸው ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የኮሚሽኑ ሥራ ላይ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 የፌዴራል እና የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናትን ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጉዳያቸው እንዲጣራና ክስ እንዲመሠረትባቸው አስተላልፎ በመንግሥት ውሳኔ ምርመራው መቋረጡ የሚታወስ ነው።
ኮሚሽኑ የመዘገበውን ሀብት ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ በአዋጅ ቁጥር 668/2002 አንቀጽ 11 መሠረት በተሿሚ፣ በተመራጭ ወይም በመንግሥት ሠራተኛ በተሞላ መረጃ ያልተሟላ፣ ትክክል ያልሆነ ወይም የሐሰት መረጃ የያዘ መሆኑን ለመጠርጠር ኮሚሽኑ በቂ ምክንያት ሲኖረው ወይም ሀብቱ በትክክል አልተመዘገበም የሚል ጥቆማ ሲቀርብ ወይም በተፈጸመ ወንጀል ምክንያት ምርመራ ሲጀመር የምዝገባውን ትክክለኛነት በማጣራት በተገኘው ውጤት ላይ እርምጃ የማስወሰድ ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015


