የዓለም ጤና ድርጅት ባሳለፍነው ወር ባወጣው ዘገባ፣ ጭንቀት እና ድባቴ የዓለምን ኢኮኖሚ ወደ አንድ ትሪሊዮን ገደማ ዶላር እያስወጣ መሆኑን አስታውቋል። ድርጅቱ ከዓለም ዐቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ጋር በመተባበር ይፋ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በዓመት 12 ቢሊዮን የሚገመቱ የሥራ ቀናትም በአልቦ ይባክናሉ።
እንደሚታወቀው የአእምሮ ጤና እክል መኖር ሰዎች በተሰማሩበት የትኛውም መስክ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። በአንጻሩ ግን አገራትም ይህን በተመለከተ ብሔራዊ የሆኑ አካሄዶችና እቅዶች የሏቸውም። በዓለም ላይ 35 በመቶ የሚሆኑት አገራት ብቻ ናቸው ከሥራ ሁኔታ ጋር የተገናኘ የአእምሮ ጤና ዙሪያ ብሔራዊ ፕሮግራም ያላቸው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በአእምሮ ጤና ዘርፍ ላይ ድንጋጤና መነቃቃትን ፈጥሯል። ከወረርሽኙ በኋላ ነው በዓለም ላይ የነበረው የድባቴና ጭንቀት መጠን ላይ የ25 በመቶ ጭማሪ የታየው። ይህም በርካታ አገራትና መንግሥታት ለአእምሮ ጤና እና ለሚያስከትለው ጉዳት ምንም ዝግጁነት የነበራቸው እንዳልሆኑ አሳይቷቸዋል።
በጉዳዩ ላይ የመንግሥት ትኩረት አናሳ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል። በተጓዳኝ የማኅበረሰብ መረዳት ብዙ ክፍተት ያለበት ነው።
የሥነልቦና (Psychology) ባለሞያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሔኖክ ኃይሉ የአእምሮ ጤና እክል ሲባል ብዙዎች ‹እብድ› የሚለው ነገር ወደ ሐሳባቸው እንደሚመጣ ይጠቅሳሉ። ይህም የአእምሮ ችግር እውቅና የሚያገኘው ጎልቶ ሲወጣና ሲታይ እንደሆነ አመላካች መሆኑን አንስተዋል። ምልክታቸው ጎልቶ የማይታይ የአእምሮ ሕመሞች እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጣቸው፣ ነገር ግን በአእምሮ ሕመም ከፍተኛውን መጠን የያዙት እነዚሁ ምልክት የማያሳዩት እንደሆነ ጠቁመዋል።
እንዴት ደኅና ሆንን?
በኢትዮጵያ ለአእምሮ ጤና የጎላ ምልክት ካላሳየ በቀር ትኩረት አያገኝም። ከባድ ሐዘን፣ አስጨናቂ የሕይወት ገጠመኝና ፍርሀት የመሳሰሉት ብዙዎችን ያጋጥማል። በአንጻሩ ደግሞ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ሲሆን፣ ካለው የሕዝብ ብዛት አንጻር በቂ የአእምሮ ጤናም ሆነ የሥነ ልቦና ባለሞያዎች የሉም። ታድያ የአብዛኛው ሰው ሥነልቦናዊ ደኅንነት እንዴት ተጠበቀ? ሰዎች እንዴት ነው በብዙ ችግር መካከልም ደኅና ሆነው መቆየት የቻሉት?
ሔኖክ ኃይሉ ‹‹በማወቅም ባለማወቅም የምንሠራቸው ነገሮች ጠብቀውን ነው።›› ይላሉ። ይህንኑ ጥያቄ ያነሱት የሥነልቦና ሕክምና ባለሞያው፣ ‹‹የአእምሮ ሐኪሞች በቁጥር መቶ አካባቢ አሉ። የሥነልቦና ሕክምና የሚሰጡም ከዛ አይበልጡም። በዚህ ቁጥር ብዙ ችግር ሳያጋጥም መቆየት እንዴት ተቻለ ስንል፤ ብዙ የጠበቁን ነገሮች አሉ።›› ሲሉ አክለዋል።
ነገሩን በምሳሌ ሲያስረዱ በሰዎች ላይ የሚደርስን ከባድ ሐዘን አነሱ። በኢትዮጵያዊያን ባህል መሠረት ሀዘን የገጠመበት ቤት በግልም ሆነ ሰብሰብ ብሎ ሄዶ ማጽናናት የተለመደ ነው። በዛም ሀዘን የገጠማቸውና የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች፤ ካጡት ሰው ጋር ስለነበራቸው ጠቅላላ ሁኔታ እንዲያወሩ ይደረጋል።
ለቅሶ ቤት የተለመዱ የሚመስሉ የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህ ጥያቄዎችም ሀዘንተኞች እንዲተነፍሱ ያደርጋልና ያግዛቸዋል። እነዚህም በልምድ ነገር ግን ጥቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ ባለማወቅ የሚደረጉ ድርጊቶች መሆናቸውን የሥነልቦና ባለሞያው ያወሳሉ።
እናም እንደ ማኅበረሰብ የአእምሮ እና የሥነልቦና ደኅንነትን ለመጠበቅና ደኅና ሆኖ ለመቆየት ያስቻሉ እንዲህ ያሉ ልምዶችና እሴቶችን ልብ ማለትና ማስቀጠል እንደሚገባ ሔኖክ መክረዋል። ከዚህ ባሻገር የአእምሮ ጤና ላይ ችግር ሲከሰት በዘርፉ ባለሞያዎ የሆኑትን የማማከር ልምድም ወሳኝና ትልቅ ነገር ነው ብለዋል።
ደኅና መሆን ይቻላል!
የአእምሮ ጤና በተለያየ መንገድ መጠበቅ ሳይቻል ሲቀር ወይም ከልጅነት ጀምሮ በተፈጠረ ችግር የተነሳ የበረታ የአእምሮ ጤና ሕመም ሲኖር፣ ሰዎች መዳን የሚቻል አይመስላቸውም። ይህም የሆነው የሰው አንጎል/አእምሮ ከሆነ ሂደት በኋላ አይለወጥም የሚል እምነት ስለነበር ነው።
ይህን ጉዳይ ያነሱት የሥነ አእምሮ ሐኪም ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ ናቸው። ይህ የሰው አንጎል ወይም አእምሮ ከሆነ ጊዜ በኋላ አይለወጥም የሚል እምነት ከየት መጣ የሚለው ላይ የተለያዩ ነጥቦችን አስቀምጠዋል።
አንደኛ ያሉት አንጎል ላይ ጥቃት ወይም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ድነው ሲሻሻሉ በብዛት አለማየትን ነው። ሌላውና ኹለተኛው ደግሞ እንደሌሎች የሰውነት ክፍሎች የሰውን አእምሮ ከፍቶ መመርመር አይቻልምና ነው።
‹‹ስለዚህ ስለአንጎል የምናውቀው ነገር ምንጩ ኹለት ነው። ወይ ከእንስሳት አልያም ከሕጻናት የአእምሮ እድገት ዝንባሌ በመነሳት ነው። አንጎል ይለወጣል አይለወጥም የሚለው መነሻው እሱ ነው።›› አሉ።
ሦስተኛው የአእምሮ ለውጥ ከሆነ ሂደት በኋላ ይቆማል የሚል እምነት የመነጨው ደግሞ አእምሮን የተረዳንበት መንገድ ከማሽን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው ብለዋል። ‹‹የሰው አእምሮ እንደኮምፕዩተር ነው እንላለን።›› አሉ።
እናም በእነዚህ ምክንያቶች አንጎል አይለወጥም የሚል እሳቤ መዳበሩን ነው ዶክተር ዳዊት ያስረዱት። ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ ዕይታ እየተቀየረ ስለመሆኑ የተለያዩ ማሳያዎች መኖራቸውን አንስተዋል። ይልቁንም አንጎል ለምሳሌ አንድን ነገር በመደጋገም/ደጋግሞ በማድረግ በውስጡ በሚመነጭ ኬሚካል የሚፈጠረው ስሜት አእምሮን መለወጥ ወይም ወደ በጎ ማምጣት ይችላል የሚል እምነት ተፈጥሯል ብለዋል።
‹‹ይህ ግን አዲስ እውቀት አይደለም። የሰው ልጅ በተፈጥሮ ቋሚ አይደለም፤ ወደ ልዕልና ይደርሳል።›› ያሉት ዶክተር ዳዊት፣ ይህ ለውጥ እንዴት ከአእምሮ ጤና ጋር የተያያዘ እንደሚሆን አስረድተዋል።
አንደኛ ያነሱት ከእድገት ጋር የሚያያዝ ነው። ሰዎች በግልም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ እድገት እያሳዩ በሄዱ ቁጥር፣ አዲስ ነገር መፈለጋቸው አብሮ እያደገ የሚቀጥል ነው። እናም ሰዎች ሁሌም ፍለጋ ላይ ይቆያሉ። ይህ በፍለጋ መቆየት በአንድ በኩል የአእምሮ ጤና ላይ እክል ሊፈጥር ይችላል።
በተጓዳኝ ሰዎች ራሳቸው በፈጠሩት ነገር ሁሉ መልሰው እየተፈጠሩ መሆኑን ያነሳሉ። ልክ ባህልን ሰዎች እንደሚሠሩትና፣ ያ ባህል መልሶ ሰዎችን እንደሚሠራ ማለት ነው። በድንገት ታድያ የባህል ለውጥ ሲፈጠር በማኅበረሰብም ውስጥ ሆነ በግለሰብ ሕይወት ውስጥ መናጋት ይፈጠራል። ይህም ሁሉ አለመረጋጋት እና ጭንቀትን በመፍጠር አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን፣ እንደ ዶክተር ደዊት ገለጻ ‹የፈጠርነው ነገር መልሶ እኛን እየጠለፈን ነው።›
ሌላው ቴክኖሎጂ ነው። ብዙ ሰዓት አንድን ነገር በማድረግ ባሳለፍን ቁጥር፤ አንጎል እየተለወጠ የመሄዱ ማሳያም ይኸው ነው። ሰዎች እርስ በእርስ ወይም ከሰው ጋር ከመነጋገር ይልቅ ከሞባይል እና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር የሚያጠፉት ጊዜ ይበዛል። ይህም በብዙ መልክ ለውጦችን ያስከትላል።
እነዚህ ለውጦች ታድያ አሉታዊ ይምሰሉ እንጂ በበጎም መጠቀም እንደሚቻል ዶክተር ዳዊት ጠቅሰዋል። ሁሌም የሰዎች አእምሮ ላይ ለውጥ ያለ በመሆኑ፣ ያንን የመለወጥ ተፈጥሮ ለተሻለ ነገር የመጠቀም አቅም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ለምሳሌ ሲያነሱ ትምህርት ቤቶችን ጠቅሰዋል። ትምህርት ቤቶች ሰውን የመለወጥ አቅም መጠቀሚያ ማእከላት መሆናቸውን ያስረዳሉ።
እናም ‹አእምሮ ከዚህ በኋላ አይለወጥም› ማለት ተገቢ እንዳልሆነና መለወጥ እንደሚችል በማወቅ በማሰብና በማስተዋል በራስ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ መክረዋል።
‹‹የምለወጥ መሆኔን ካወቅሁ አስቤ መለወጥ እችላለሁ። እናም አስቦ መለወጥ ይቻላል። ሐሳብና ስሜትን መንካት ባይቻል እንኳ የሰውን ጠባይ መንካት ይቻላል። እናም ለመለወጥ ድግግሞሽ አንዱ መንገድ ነው።›› ሲሉም አክለዋል።
‹ሌላው መንገድ›
ቃልኪዳን ኃይሉ ወጣት የሥነልቦና ማማከር ምሩቅና ባለሞያ ናት። በሮትራክት ክለብ የሙያና አመራር ልማት ዳይሬክተር (professional and leadership development Director) በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።
ባሳለፍነው መስከረም መጨረሻ ላይ በምታገለግልበት ክበብ ‹ሌላው መንገድ› የተሰኘ የቡድን የምክክር ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ የሠልጣኖች ምርቃት እንዲሁም የዓለም ዐቀፍ የአእምሮ ጤና ቀንን ምክንያት ባደረገ መድረክ ላይ ነበር ያገኘናት።
የሮትራክት ክበባት ጓደኝነትና ቤተሰባዊነትን ማጠናከር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት እና በየሙያ ዘርፍ እድገት ማሳየት የሚሉ ምሰሶዎች ያሏቸው መሆኑን አንስታለች። እርሷም በመሪነት ስትሰየም፣ የነበረውን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ትኩረቷ ያረፈበትን የአእምሮ ጤና ጉዳይ በማንሳት ‹ሌላ መንገድ› የተሰኘውን ፕሮጀክት አስተዋውቃለች።
ሌላው መንገድ የቡድን ምክክር (ግሩፕ ካውንስሊንግ) የተሰጠበት/የሚሰጥበት አውድ ሲሆን ለስምንት ሳምንታት የዘለቀ ነው። የሮትራክት ክበብ አባላት ሌሎችን ለመርዳት ወደኋላ ባይሉም የራሳቸው የአእምሮ ጤና ላይ ብዙም እንደማይሠሩ የጠቀሰችው ቃልኪዳን፣ ፕሮጀክቱም ይህን ለመለወጥ በማለም የተካሄደ እንደነበር አውስታለች።
በዛም አባላቱ በሕይወታቸው ያሉ ጭንቀትን የሚፈጥርባቸው ክስተቶች፣ በልጅነት የገጠሟቸውንና እያደጉ ሲመጡ አሉታዊ ጠባያት ወይም ስሜቶች የፈጠሩባቸውን ሁኔታዎች በሚመለከት ሲወያዩ ቆይተዋል።
ያንን መነሻ ችግር ካወቁ በኋላም ጠባያቸውን ወደተሻለው ለመቀየር የሚያስችሉ ልምምዶችን አድርገዋል። ከዛም በተጨማሪ በድሎኛል ለሚሉት ሰው፣ ለራሳቸውም ቢሆን ይቅርታ እንዲያደርጉ ተደርጓል። ከእነዚህ ሂደቶች በኋላ ነው ‹ከሕመም ተመረቁ› ተብለው ለምርቃት የበቁት። አዲስ ማለዳም ለዚህ ጽሑፍ ግብዓት የሆኗትን ሐሳቦች ከዚሁ የምርቃት መድረክ ላይ ነው የቃረመችው።
‹ሌላው መንገድ› ወደፊትም የአሁኑ ተመራቂዎች ያሉበትን ሁኔታ የሚከታተልበት ቀጠሮ እንዳለም ቃልኪዳን አመላክታለች።
ከዚህ በተጓዳኝ ወጣቶች አሁን ያሉባቸውን ከአእምሮ ጤና ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ቃልኪዳን አንስታለች። በተለይም እንደቀልድ ጣል የሚደረጉ ‹ብሞትስ! ሰልችቶኛል! ደብሮኛል! አምላክ ጨከነብኝ!› የሚሉና መሰል ንግግሮችን እንደቀልድ ማለፍ እንደማይገባ ጠቁማለች። ሐሳብ ድርጊትን ይወልዳልና እንዲያ የሚሉ ሰዎች ራስን ስለማጥፋት ማሰብ የጀመሩ ናቸው ብላለች።
ከዛም በተጓዳኝ ሰዎችንም ሆነ ራስን ከመፈረጅ እንቆጠብ በማለት መክራለች። ‹ድብርት ውስጥ ነኝ› ብሎ ራስን ከድባቴ ጋር እንደሚኖሩ ማሰብ፣ ‹ተወዳጅና ተፈላጊ አይደለሁም!› ብሎ ራስን መፈረጅም ትክክል እንዳልሆነም ነው ያነሳችው። ሌሎችንም ከመፈረጅ እንደዛው እንቆጠብ ስትልም ሐሳቧን አካፍላለች። ከዛ ባለፈ እርስ በእርስ መመካከርና በግል ደስ የሚሰኙበት ተግባር ላይ መሳተፍ የአእምሮ ጤናን ለመጠበቅ ያግዛልና ያንን መለማመድ እንደሚገባ አሳስባለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



