የኢክላምሲያ በሽታ መመርመሪያ ኮንጎ ሬድ ቴስት

0
1065

በእርግዝና ወቅት ስለሚፈጠር የደም ግፊት ወይም ፕሪክላምሲያ እና ኢክላምሲያን በሚመለከትና በሽታውን ለመመርመር በሙከራ ላይ ስለሚገኘው ኮንጎ ሬድ ቴስት አዳዲስ መረጃዎች ብቅ ብለዋል። በመመርመሪያ መሣሪያው ዙሪያም በኢትዮጵያ በቅርቡ የተሰጠ ሥልጠና አለ። ይህን መነሻ በማድረግ ሐይማኖት ግርማይ ተከታዩን ጽሑፍ ልከውልናል።

በእርግዝና ወቅት ስለሚፈጠር የደም ግፊት ወይም ፕሪክላምሲያ እና ኢክላምሲያ [Pre-Eclampsia and Eclampsia] ምንነት፣ ምልክት እና ራስን ከከፋ አደጋ ለመከላከል መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ብሎም ይህን በሽታ ለመመርመር በሙከራ ላይ ስለሚገኘው ኮንጎ ሬድ ቴስት ስለተባለ የሕክምና መሣሪያ እናስነብባችኋለን።

የጽንስ እና የማሕጸን ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ገሊላ ኪዳኔ ጎባ፣ ‹‹በከፍተኛ ደረጃ በዓለም ላይ ጥናት ከሚደርግባቸው በሽታዎች ውስጥ አንዱ ፕሪክላምሲያ ነው›› በማለት የበሽታውን አሳሳቢነት ተናግረዋል። በምክንያትነት ያስቀመጡት፣ በሽታውን በገንዘብ የተሻለ አቅም ያላቸው ሰዎች እንኳን ሊከላከሉት ያልቻሉት መሆኑን ነው። እንዲሁም በሽታው በምን ምክንያት እንደሚከሰት አለመታወቁ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል።

ስለዚህ በሽታውን ቀድሞ መከላከል ካልተቻለ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ቅድመ ምርመራ በማድረግ ሕክምና ለመስጠት ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፤ የሕክምና ባለሙያዋ።

በሽታው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሆነ በአገራችን ለእናቶች ሞት መንስኤ በመሆን ኹለተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል። ይህ በሽታ በእናቶች ላይ የከፋ ጉዳት እንዲያስከትል ምክንያት ከሆኑት ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የምርምራው ሂደት እና ውጤታማነት ላይ ችግር መኖሩ ነው። ዶ/ር ገሊላ እንደሚናገሩት፣ አንዲት ነፍሰጡር እናት ላይ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት መኖሩን በምርመራ ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ወይም መሟላት ያለባቸው ሦስት ነገሮች አሉ።

1)       ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት ይህን ምርመራ እንድታገኝ የራስ ምታት፣ የማቅለሽለሽ፣ ብዥ የማለት እና የመድከም ስሜት ሊኖራት ይገባል። ይህ ደግሞ በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ የተለመዱ ስሜቶች ስለሆኑ፣ አንዲት እናት ይህን ስሜት ለሕክምና ባለሙያው ላትገልጽ የምትችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ዶ/ር ገሊላ ተናግረዋል።

2)      የደም ግፊት መጠን ማንኛውም ጤነኛ ሰው ከሚኖረው 90 በ140 ከፍ ማለቱን ማረጋገጥ ይገባል። የደም ግፊቱ መጠን ቢያንስ በ6 ሰዓት ልዩነት ኹለት ጊዜ መታየት ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለ6 ሰዓት ያህል አንዲትን ነፍሰጡር እንድትጠብቅ ማድረግ ከባድ ይሆናል ብለዋል የሕክምና ባለሙያዋ።

3)      በላብራቶሪ በሚደረግ የሽንት ምርመራ አልቡሚን በተባለ ፕሮቲን እንዲሁም በተለያየ የደም ምርመራ መሠረት የዚህ በሽታ ተጠቂ የሆነች ነፍሰጡር ትለያለች። ነገር ግን ይህን ምርመራ ማግኘት በማይቻልበት አካባቢ የሚኖሩ ነፍሰጡሮች አገልግሎቱን ለማግኘት እንደሚቸገሩ ባለሙያዋ ጠቁመዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ፣ ‹‹ይህ የፕሮቶቲን ምርመራ የራሱ የተወሰኑ ችግሮች አሉት›› ብለዋል። ችግር ብለው ያስቀመጡት አንዳንድ ጊዜ በላብራቶሪ ምርመራ በሽታው እያለ ውጤቱ ግን በተቃራኒው የበሽታውን አለመኖር የሚያሳይበት አጋጣሚ በመኖሩ ነው።

ዶ/ር ገሊላ ጎባ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኤሌኖን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለ20 ዓመታት ያህል ለዚህ በሽታ መመርመሪያ የሚሆን የሕክምና መሣሪያ ሲሠሩ ቆይተዋል። እናም በአሁኑ ወቅት ኮንጎ ሬድ ቴስት የተባለ የሕክምና መሣሪያ ለሙከራ አቅርበዋል። ይህ የሕክምና መሣሪያ የኢክላምሲያ በሽታ ምልክት የሆነውን በሽንት የሚገኘውን ፕሮቲን ለይቶ የሚያሳይ ነው። ከዚህ ቀደም ከነበሩት የመመርመሪያ መሣሪያዎችም በተሻለ መልኩ በቀላሉ በሽታውን ለመለየት ይረዳል።

የክላሚሲያ በሽታ አንዳንድ ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ቆይቶ የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። ብዙዎችን ለሞት የሚዳርገውም ቶሎ ሕክምና ስለማያገኝ ነው። ስለሆነም፣ በሽታው ጉዳት በሚያደርሰው የኢክላምሲያ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ፕሪኢክላምሲያ ተብሎ በሚጠራው ያልከፋ ሁኔታ ላይ ሳለ እንዲታወቅ ይህ መሣሪያ ይረዳል። በቤት ውስጥ የእርግዝና ምርመራ ከሚደረግበት የሕክምና መሣሪያ ጋር ኮንጎ ሬድ ቴስት በመጠን እና በአጠቃቀም የመመሳሰል ነገር እንዳለው ዶ/ር ገሊላ ተናግረዋል።

ስለሆነም፣ መሣሪያው በሕክምና ተቋማት ሙከራ ከተደረገበት በኋላ በግለሰብ ደረጃ በቤት ውስጥ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ የመፍጠር እቅድ መኖሩን ባለሙያዋ አክለዋል።

ኮንጎ ሬድ ቴስት የተባለው የኢክላምሲያ በሽታ መመርመሪያ መሣሪያ በተለያዩ አገራት በሕክምና ተቋማት ውስጥ በሙከራ ላይ ይገኛል። ሕንድ፣ ሜክሲኮ እና ባንግላዲሽ መሣሪያው ከተሠራበት አገረ አሜሪካ በተጨማሪ ሙከራ ተደረጎ ስኬታማ ከሆነባቸው አገራት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢሊኖይ (university of Illinois)፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጽያ የፅንስ እና የማህፀን ሐኪሞች ማኅበር በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ የሕክምና መሣሪያው ሙከራ እንዲደረግበት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። በአፍሪካ ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ዩጋንዳ የዚህ የሕክምና መሣሪያ ሙከራ አካል ተደርጋለች።

‹‹ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲፈጠሩ የተፈጠረው ነገር ይበልጥ ከሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው በኢኮኖሚ በተሻለ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች ወይም የማኅበረሰብ ክፍሎች ነው›› ብለዋል ዶ/ር ገሊላ። ይህ መሣሪያ ግን በአሜሪካ ሲተዋወቅ ጎን ለጎን ይበልጥ ተጎጂዎች በሚገኙባቸው እንደ ሕንድ፣ ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ ባሉ አገራትም እንዲተዋወቅ እየተሠራ ይገኛል፤ እንደ ዶ/ር ገሊላ ገለጻ።

የማስተዋወቅ ወይም መሣሪያውን ሥራ ላይ ለማዋል ለሚደረገው ሙከራ ግብአት የሚሆን ጥናት ለማካሄድ በኢትዮጵያ በሦስት አካባቢዎች ማለትም በአዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሀን እና ጅማ ሥራ ተጀምሯል። የጥናቱ ዋና አካላት የጤና ተቋም፣ የሕክምና ባለሙያ እና እናቶች ናቸው። 45 የመንግሥት እና የግል የሕክምና ተቋማትም ተካታች ይሆናሉ።

በጥናቱ ላይ ከሦስት ሺሕ በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። ከ5 ወር በላይ የሆኑ ነፍሰጡር እናቶች ማለትም የፕሪክላምሲያ ምልክት የሚያሳዩ እንዲሁም ምልክቱን የማያሳዩ ነፍሰጡር እናቶችም ጭምር በጥናቱ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ። ይህም አሁን ካለው የሕክምና መሣሪያ ጋር ለማነጻጸር ስለሚጠቅም ነው፤ እንደ ዶ/ር ገሊላ ገለጻ። እንዲሁም በሽታው ምልክት ሳያሳይ በእናትየው ላይ ሊኖር የሚችልበት እድል ስለሚኖር ለማረጋገጥ ነው።

ጥናቱ ፍቃደኛ ሆነው በተገኙ ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ ብቻ ነው የሚሠራው። በተጨማሪም የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋት ሁኔታ ላይ ያለች ነፍሰ ጡር ሴት የክላምሲያ ምልክት አሳይታ ብትጠረጠር እንኳን ቅድሚያ ሕክምናውን ማግኘት ስለሚገባት ጥናቱ ላይ ተሳታፊ አትሆንም። በአንዲት ነፍሰ ጡር እናት ላይ ይህ ጥናት ሲደረግ ከእርግዝናዋ [ካለችበት የእርግዝና ወራት] ጀምሮ ልጅ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ ያካትታል። ማለትም ጥናቱ የእናቲቱን ሂደት ይከታተላል። ስለሆነም በአጠቃላይ ጥናቱን ወይም መረጃውን አሰባስቦ ለመጨረስ የ6 ወራት ጊዜ ይፈጃል።

ኮንጎ ሬድ ቴስት የሕክምና መሣሪያ ላይ ለሚደረገው ጥናት መረጃ ለሚያሰባስቡ እና ለሚያስተባብሩ የሕክምና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ከተማ ከመስከረም 9 እስከ 11/2015 ለሦስት ቀናት ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በሥልጠናው ላይ የተገኙ በደብረ ብርሀን አየርጤና ጤና ጣቢያ የሚሠሩት ሚድዋይፍ ዋሴ ጉልላት፣ ከገጠራማ አካባቢ ለሚመጡ እናቶች ይህ መሣሪያ ይበልጥ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ይህንንም ያሉት በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የማንቀጥቀጥ እና የመጣል ሁኔታ ሲኖረው ከባእድ አምልኮ ጋር የማያያዝ እና ሕክምና ለማግኘት ፍቃደኛ ያለመሆን ሁኔታ በመኖሩ ነው። ስለሆነም በሽታውን አስቀድሞ በማግኘት እናቶች ለከፋ ጉዳት ሳይዳረጉ ሕክምና እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፤ እንደ ሕክምና ባለሙያው ንግግር።

በተመሳሳይ በሥልጠናው ላይ ያገኘናቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት የማህጸን እና ጽንስ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ደምሰው አመኑ፣ ‹‹በጥናቱ መሠረት የሕክምና መሣሪያው ውጤታማ ከሆነ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት በይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ›› በማለት መሣሪያው ለኢትዮጵያ የሚኖረውን ጥቅም ተናግረዋል። ይህንንም ያሉት የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ተቋማት የሕክምና መሣሪያ እጥረት እንዳለባቸው በመጠቆም ነው።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ በበኩላቸው፣ ይህ ጥናት ውጤታማ ሆኖ በሽታው የዘገየ [የከፋ] ደረጃ ላይ ሳይደርስ የሚገኝ ከሆነ በሽታው የሚያስከትለውን ችግር እንደሚቀርፍ ተናግረዋል። ስለሆነም ጥናቱ ከጠናቀቀ በኋላ ውጤታማነቱ ታይቶ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በዓለም የጤና ድርጅት እንዲሁም በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እውቅና ከተሰጠው በሥራ ላይ የሚውል ይሆናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here