በሰሜኑ ጦርነት ተጽዕኖ ብሔራዊ ባንክ አዳዲስ መመሪያዎች መተግበሩ በባንክ ዘርፉ ላይ ጫና መፍጠሩ ተገለጸ

0
1074

ለኹለት ዓመት የዘለቀው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ባስከተለው ተጽዕኖ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተደጋጋሚ በባንኮች ላይ አዳዲስ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጉ በባንክ ዘርፉ ላይ ጫና መፍጠሩ ተገለጸ።

ብሔራዊ ባንክ በሰሜኑ ጦርነት በተከሰተው ጫና ምክንያት በባንኩ ዘርፍ ላይ ያደረጋቸው አዳዲስ ማሻሻያዎች በባንኮች ሥራ ላይ ጫና መፍጠሩን የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስፋው ዓለሙ ገለጹ። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት ባለፈው ጥቅምት 17/2015 የዳሸን ባንክ 29ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለባለአክሲዮኖች ስለ ባንካቸው አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ባንኮች በበጀት ዓመቱ ካስተናገዷቸው ችግሮች መካከል አንዱ የሆነው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዳሽን ባንክንም የፈተነ ችግር እንደነበር ጠቁመዋል። በጦርነቱ ምክንያት ኢትዮጵያ የምታገኛቸው የውጭ ድጋፎች መቋረጣቸውን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ በባንኮች ላይ አዳዲስ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጉን አንስተዋል። ብሔራዊ ባንክ ተከታታይ መመሪያዎችን በባንኩ ዘርፍ ላይ ተግባራዊ ማድረጉ፣ ዘርፉ በብዙ ጫና ውስጥ እንዲያልፍ ማድረጉንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

በባንኩ ጉባኤ ላይ የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም ያቀረቡት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ ዱላ መኮንን በበኩላቸው፣ ያለፈው በጀት ዓመት በርካታ ተግዳሮቶች የተስተዋሉበት እንደነበር አስታውሰዋል። ኢኮኖሚው በውጭ እና በውስጥ ጫናዎች ውስጥ ማለፉና የሰሜኑ ጦርነት ያስከተለው ጫና ለዘርፉ ተግዳሮት እንደነበር አንስተዋል።

በዚህም የባንክ ዘርፉ የዋጋ ንረትንና የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመከላከል፣ ምርት ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩ አካላትን ለማበረታታትና የመንግሥትን የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ለማሳደግ በተቀረጸ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲዎች ስር ለመሥራት የተገደዱበት ዓመት እንደነበርም አስታውሰዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ባንኮች ከንብረት ዘረፋና ውድመት እስከ ብድር ብልሽት የደረሰ ጉዳት አስተናግደዋል። ባንኮች ካስተናገዷቸው የንብረት ውድመትና ዘረፋ እንዲሁም የብድር ብልሽት ችግሮች በተጨማሪ በትግራይ ክልል ኹለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ፣ በአፋርና በአማራ ክልል ጦርነቱ በተካሄደባቸው ወቅቶችም አገልግሎት መስጠት አልቻሉም።

ምንም እንኳ የባንክ ዘርፉ በጫና ውስጥ ቢያልፍም ዳሽን ባንክ በዓመቱ ያስመዘገበው አፈጻጻም ጥሩ እንደነበር የቦርድ ሰብሳቢው ጠቁመዋል። ባንኩ በዓመቱ ከታክስ በፊት 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንና ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ57 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ተብሏል።

በወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ባንኩ ያሳየው እድገት አመርቂ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የባንኩ አጠቃላይ ከወለድ ነጻ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 5.9 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተነግሯል። የባንኩ አጠቃላይ ሀብትም 117.14 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ24 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተመላክቷል።

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ድርሻም ወደ 14.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ42 በመቶ እድገት አሳይቷል። ባለአክሲዮኖቹ ባለፈው ጉባኤያቸው ተጨማሪ ካፒታል ለማቅረብ መወሰናቸውን ተከትሎ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠንም 6.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here