የማረሚያ ቤቶች አዋጅ ላይ የተጠራው ውይይት በቂ ሰው ባለመገኘቱ ተሰረዘ

0
629

በፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመወያየት የሕግ፣ ፍትኅና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚቴ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ያዘጋጀው የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማነስ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላለፈ።

ለውይይቱ ከ15 ተቋማት በላይ በደብዳቤ መጋበዛቸውንና በሚዲያም መጠራታቸውን ያስታወሰው ቋሚ ኮሚቴው፣ በመድረኩ የተገኙት ብዛት እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ለተፈጠረው መስተጓጎል የተገኙትን ተቋማት ይቅርታ በመጠየቅ ስብሰባው እንዲበተን አድርጓል።

ጥቅምት 25 ቀን 2012 የቋሚ ኮሚቴው አዲስ ሰብሳቢ እንዲሆኑ የተመደቡት ተመስገን ባይሳ (ዶ/ር) የተሻለ ሕግ እንዲወጣ ‘’ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ያልተወያየበት ሕግ ነው’’ የሚባለውን አስተያየት ለማስቀረት ሲባል ስብሰባው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን በመግለፅ ስብሰባው እንዲበተን አድርገዋል።

ማረሚያ ቤቶች የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን እንዲያቋቁሙ የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ ላይ ምክር ቤቱ በ1ኛ መደበኛ ስብሰባው መስከረም 29 ቀን 2012 ለፓርላማው ያቀረበው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ፣ የማረሚያ ቤት አስተዳደርን ወደ ኮሚሽን እንዲያድግና ተጨማሪ ዘጠኝ ሥልጣኖች እንዲኖሩት የሚጠይቅ ነው።
ረቂቁ ከዚህ ቀደም በፖሊስ ጣቢዎች ስር ሲተዳደሩ የቆዩትን ማረፊያ ቤቶችንም በማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ስር ሆነው እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሲሆን አንድ ማረሚያ ቤት ማረሚያ እንዲባል ለሕዝብ በግልጽ የሚታወቅ መሆን እንዳለበት ረቂቁ ደንግጓል።

ለዚህም እንደ ምክንያት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቀረት እና ማረሚያ ቤቶችን ለሕዝብ ግልፅ እንዲሆኑ ለማድረግ ይረዳል በሚል እንደሆነ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የማብራሪያ ኖት ያስረዳል።

በረቂቁ ላይ ዝርዝር ውይይቶች ተደርጎበት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብለት አዋጅ ቁጥር 3/2012 ሆኖ ለሕግ፣ ፍትኅና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here