ሰኞ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ አርሶ አደሮች ወቅታዊ የገበያ መረጃ እንዲደርሳቸው የሚያደርግ የስልክ መተግበሪያ በማበልጸግ ተደራሽ ማድረጉን አስታውቋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ መተግበሪያ፤ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በወቅቱ ገበያ ሸጠው መጠቀም እንዲችሉ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
አርሶ አደሩ በብዙ ልፋት ያመረተውን ምርት ቀጥታ ለገበያ ማቅረብ ሲገባው ደላሎች በሚፈጥሩት የገበያ ሰንሰለት ብልሽት ምክንያት ምርቱን በሚፈልገው ዋጋ መሸጥ አለመቻሉ ተጠቁሟል።
ችግሩን ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው ከ2015 መግቢያ አንስቶ ለሙከራ በተመረጡ የደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የስልክ መተግበሪያ አበልጽጎ ወቅታዊ የገበያ መረጃ በእጅ ስልካቸው መልዕክት እንዲደርስ እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
መተግበሪያው ለ1 ሺሕ 300 አርሶ አደሮች በሳምንት አራት ቀን ወቅታዊ የገበያ መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረጉ ምርታቸውን በወቅቱ ገበያ ሸጠው መጠቀም መቻላቸው ተገልጿል።
ቀጣይ ተደራሽነቱን በማስፋት ለበርካታ የምስራቅ አማራ አርሶ አደሮች ወቅታዊ የገበያ መረጃ እንዲደርሳቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን፤ መተግበሪያ ለአርሶ አደሩ ከንግድ ተቋማት ዕለታዊ ዋጋ በመላክ በምርቱ ተደራድሮ እንዲሸጥ ማስቻሉም ተመላክቷል።



