የተማሪዎች ምረቃ ከዩኒቨርሲቲ መውጫና ከ12ኛ ክፍል ፈተና ጋር ሳይጋጭ እንደሚከናወን ተገለጸ

0
334

በ208 የትምህርት ፕሮግራሞች የመውጫ ፈተና ተዘጋጅቷል

ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ከዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና እና ከ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጋር ሳይጋጭ እንደሚከናወን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በ208 የትምህርት ፕሮግራሞች የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ፣ ከመውጫና ከ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጋር በማይጋጭ መልኩ እንዲከናወን የሚረዳ ዕቅድ ተዘጋጅቷል።

ዶክተር ኤባ እንዳመለከቱት፤ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2015 ድረስ የሚሰጥ ሲሆን፤ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ደግሞ ከሐምሌ 17 ቀን 2015 ጀምሮ ባሉት ቀናት ይሰጣል።

ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎቻቸውን የምረቃ መርሃግብር ከመውጫ ፈተና በኋላ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎቹ ምርጫ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሲጠናቀቅ ማካሄድ እንደሚችሉ መገለጹን ጠቁመዋል። በዘንድሮው ዓመት 180 ሺሕ የሚጠጉ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና እንደሚወስዱ አስታውቀው፤ ለ208 የመመረቂያ ፕሮግራሞች የሚውሉ የፈተና ዓይነቶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የመውጫ ፈተና የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ሆኖ ይቀጥላል ያሉት ዶክተር ኤባ፤ በመሆኑም በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ተፈትነው 50 በመቶና በላይ ያመጡ ተማሪዎች እንደሚያልፉ አስረድተዋል፡፡ የመውጫ ፈተናው ሙሉ በሙሉ በኦንላይን የሚሰጥ በመሆኑ የተማሪዎች ሥም ዝርዝር ተልኮ ወደ ዳታ ማዕከል መግባቱን አመላክተዋል።

ለተማሪዎች ለፈተና የሚሆን ልዩ የመታወቂያ ቁጥር ይሰጣቸዋል ያሉት ዶክተር ኤባ፤ በተሰጣቸው ቁጥር መሠረት በኦንላይን መፈተን እንዲችሉ የሚረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በማዕከል ደረጃ የተዘጋጀውን የፈተና ሥርዓት ለመሞከር እንደ አገር ሞዴል ፈተና እንደሚሰጥ አስታውቀው፤ በዚህም ጉድለቶች ካሉ ለማስተካከልና ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

ለፈተናው መሳካት ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተደራጀ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። ለመውጫ ፈተናው የሚውሉ ኮምፒዩተሮች፣ የኢንተርኔት አገልግሎትና ጄኔሬተሮች ዝግጅት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here