በሶማሌ ክልል አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል አራት ሰዎችን ገድሎ ራሱን ማጥፋቱ ተገለጸ

0
337

ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ ባሳለፍነው ሰኞ ሰኔ 12/2015 ረፋድ ላይ አንድ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል የሆነ ግለሰብ አራት ንፁሃን ዜጎችን ገድሎ ራሱን ማጥፋቱን የክልሉ ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት አባሉ በቀብሪደሃር ከተማ ቀበሌ 8 እየተባለ በሚታወቀው አካባቢ በሦስት ወንዶች እና በአንዲት ሴት ላይ ተኩስ በመክፈት ሕይወታቸው እንዲያልፍ ካደረገ በኋላ የራሱንም ሕይወት ማጥፋቱን ነው የተገለጸው።

በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ ግለሰቡ በከፈተው ተኩስ የቀበሌውን ሊቀመንበር ጨምሮ አራት ሰዎችን ሕይወት ከማጥፋት ባለፈ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰዎችን አቁስሏል።

የሶማሌ ክልል ጸጥታ ቢሮ ድርጊቱን በማጣራት ላይ መሆኑን ገልጾ፤ ምርመራውን ሲያጠናቅቅ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ይህን ጉዳይ በማስመልከት በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የሶማሌ ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ባወጣው መግለጫ፤ “በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደዚህ አይነት ሕገወጥነት እየተስፋፋ ነው” ካለ በኋላ፤ ለአብነትም ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በጅግጅጋ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ መሰል ጥቃት ንጹሃን ላይ መፈጸሙን አስታውሷል፡፡

በመሆኑም ባለፈው ሰኞ ዕለት በቀብሪደሃር ከተማ በአንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል ምክንያት አንድ የመንግሥት ሹመኛ እና ሦስት የግንባሩ አባላት መገደላቸውን ብሎም ኹለት ሰዎች መቁሰላቸውን ጠቅሶ፤ “የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥታት በመናበብ እንደዚህ አይነት ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ አካላትን አስቸኳይ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here