ቪዛ በኢትዮጵያ የፊንቴክ ጀማሪዎችን እና ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ የሚያስችለውን ፕሮግራሞች ይፋ አደረገ

0
352

ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ቪዛ በኢትዮጽያ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ (ፊንቴክ) ፈጠራን ለማበረታታት እና በሴቶች የሚመሩ አነስተኛና መካከለኛ ንግዶችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ኹለት አዳዲስ ፕሮግራሞችን ይፋ አድርጓል።

የመካከለኛው እና የምስራቅ አውሮፓ እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ክልል የቪዛ ፕሬዝዳንት አንድሪው ቶሬ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ፤ ቪዛ ለኹለተኛ ጊዜ “ቪዛ በየትኛውም ቦታ (VEI)” የተሰኘውን ተነሳሽነቱን ለማጠናከር በኢትዮጽያ የፊንቴክ ውድድር ለማካሄድ ማሰቡን ተናግረዋል።

በተጨማሪም “ቀጣይ እሷ ናት” የሚለውን የሴቶች ማጎልበቻ እንቅስቃሴ ለመጀመር ዕቅድ መያዙንም ይፋ አድርገዋል። .

“ቪዛ በየትኛውም ቦታ” መጪውን የክፍያ ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚያስችሉ ፈጠራዎችን እንዲያካፍሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፊንቴክ ሥራ ፈጣሪዎችን ለሥራ የሚጋበዙበት ፕሮግራም ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. በ2021 የኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሽያጭ የክፍያ ስርዓት ኦፕሬተር በመሆን፤ የመጀመሪያውን “ቪዛ በየትኛውም ቦታ” ኢትዮጵያ ውድድርን አሪፍፔይ አሸንፏል።

እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ፣ “ቪዛ በየትኛውም ቦታ (VEI)” ከ100 በላይ አገሮች ለተውጣጡ ሥራ ጀማሪዎች ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አንድሪው ተናግረዋል።

እንዲሁም የቪዛ “ቀጣይ እሷ ናት” ፕሮግራም፤ የሴቶች ንብረት የሆኑ አነስተኛ ንግዶችን በገንዘብ፣ በስልጠና እና በአማካሪነት የሚደግፍ አለም አቀፍ ፕሮግራም መሆኑን አስታውቀዋል።

አክለውም፤ እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ቪዛ ከ250 በሚበልጡ የገንዘብ ድጋፎች እና በሴቶች ባለቤትነት ሥር ያሉ የንግድ ተቋማትን በማሰልጠን ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጉን አስረድተዋል።

የቪዛ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ኃላፊ የሆኑት አይዳ ዲያራ በበኩላቸው፤ “የቪዛን አለም አቀፍ ፕሮግራሞች ወደ ኢትዮጵያ በማምጣታችን ኩራት ይሰማናል። በቀጣይነት በዲጂታል ኢኮኖሚ እና በአጠቃላይ የጀማሪዎች ተሳትፎን በማጠናከር ላይ ነን።” ብለዋል።

ቪዛ እ.ኤ.አ ከመጋቢት 2020 ጀምሮ በአዲስ አበባ ውስጥ እንቅስቃሴ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፤ የዲጂታል ንግድ እና የገንዘብ እንቅስቃሴን ለተጠቃሚዎች፣ ነጋዴዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የመንግሥት አጋሮች ልዩ እድሎችን በመፍጠር በፋይናንሺያል ስነ-ምህዳር ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት የአፍሪካን ተስፋፊ ጅምር ማህበረሰብ በሙያ፣ በግንኙነቶች እና በኢንቨስትመንት ፈንድ ለማስቻል የሚረዳውን አዲሱን “የቪዛ አፍሪካ ፊንቴክ አክስሌሬተር” ፕሮግራም መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የ2025 የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን በ2020 የጀመረች ሲሆን፤ በዚህም ዲጂታል እና ፋይናንሺያል አካታች ኢኮኖሚን በመለወጥ እና በማሳደግ በ2025 ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እስከ 39 በመቶ ድርሻ እንድታበረክት ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here