ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ፋውንዴሽን የፊታችን እሁድ ሰኔ 18/2015 በይፋ ተመስርቶ ሥራ እንደሚጀምር የአርቲስቱ ቤተሰቦችና አደራጅ ኮሚቴው አስታውቋል።
የአርቲስቱ ቤተሰቦችና አደራጅ ኮሚቴው በዛሬው ዕለት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ፋውንዴሽኑ የአርቲስቱን “ሌጋሲ” ለማስቀጠል ታልሞ የሚመሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የፋውንዴሽኑ ምስረታ የምዝገባ ሂደቱ በመጠናቀቁ የፊታችን እሁድ ሰኔ 18/2015 በይፋ ተመስርቶ ሥራ ይጀምራል ብለዋል።
የአርቲስቱ ባለቤት ሊሊ ማርቆስ ቢራና የኮሚቴው አባል ኢፈባስ አብዱልወሀብ እንደተናገሩት፤ ፋውንዴሽኑ በትምህርት፣ በጤና፣ በአርትና በሙዚቃ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ይሆናል።
የክቡር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ ከ60 ዓመታት በላይ በሰራቸው ዘመን ተሻጋሪ ድንቅ ሙዚቃዎቹ የብዙዎችን ቀልብ የገዛና በጥበብ የተሞላ ድንቅ ሰው እንደነበር ይታወቃል። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ ከሆኑ አንጋፋ ድምጻውያን መካከል ዓሊ ቢራ በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑንም በመድረኩ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
አርቲስቱ በዘርፉ ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦ ኹለት የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ሲሆን፤ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የተለያዩ የእውቅና ሽልማቶችን አግኝቷል።
የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ባደረበት ህመም ሳቢያ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል፡፡



