የራያ አላማጣ የማንነት ጥያቄ በህገ መንግሥቱ ብቻ አይፈታም ተባለ

0
697

አርብ ሰኔ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የራያ አላማጣ የማንነት ጥያቄ ሕግ መንግሥቱን ብቻ መሰረት በማድረግ ሊፈታ የማይችል መሆኑን የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ ሀይሉ አበራ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የራያ አላማጣ አካባቢዎች ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት በ1984 ሀምሌ ወር ላይ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፤ “ሕገ መንግሥቱ ደግሞ በ1987 የወጣው በመሆኑ ጥያቄያችን በሕገ መንግሥቱ መሰረት ይፈታል የሚለው አስቻይ አይደለም።” ሲሉ ተደምጠዋል።

አክለውም፤ ሕገ መንግሥቱ የክልሎችን ወሰን በግልጽ አያስቀምጥም ያሉ ሲሆን፤ “በወቅቱ ክልሎችን ለማደራጀት የወጣው አዋጅ 7/84 ካስቀመጣቸው አራት መሰረታዊ መርሆዎች አንዱም ሳይረጋገጥ ነው ቦታዎች ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት።” ሲሉ ገልጸዋል።

ክልሎችን ለማደራጀት በወጣው አዋጅ መሰረት የመጀመሪያው መስፈርት የሕዝብ በጎ ፈቃደኝነት ቢሆንም፤ የራያ ሕዝብ በጭራሽ አልተጠየቀም ነው ያሉት። እንዲሁም “ከ1966 በፊት የነበሩ ወረዳዎች ባሉበት ይቀጥላሉ የሚለው ኹለተኛው መስፈርት፣ ከተጠቀሰው ዓመት በፊት በወሎ ክፍለ አገር የነበሩ ወረዳዎችን በግድ ወደ ትግራይ የጠቀለለ ነው ብለዋል።

ሦስተኛው መስፈርት ቋንቋ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፣ ይህም ቢሆን በሕዝቡ ላይ በግድ የተጫነ ነው ካሉ በኋላ፤ “ለአብነትም ብሔራዊ ፈተና ወስደው በሌሎች የትምህርት ዓይነቶች በሙሉ <<A>> የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች፣ በትግርኛ ትምህርት <<F>>ነበር የሚያገኙት።” ሲሉ ገልጸዋል።

አራተኛው የአዋጁ መስፈርት የሕዝብ አሰፋፈርና ስነልቦና የነበረ ቢሆንም፤ ሕዝቡ “ስነልቦናዬ አማራ ነው” እያለ ባለበት ነው ወደ ትግራይ የተካለለው ብለዋል።

ስለሆነም ኹሉም የአዋጁ መስፈርቶች ባለተረጋገጡበት ሁኔታ ነው አካባቢው በኃይል የተወሰደው ያሉ ሲሆን፤ “የሕወሓት መሪዎች ራሳቸው ያወጡትን ሕገመንግሥትም ሊያከብሩት አልቻሉም።” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፤ “በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ላይ “የማንነት ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ለክልል ምክር ቤቱ አቤቱታ ማስገባት አለባቸው” በሚለው መሰረት፤ በ2011 27 ሺሕ 500 የአቤቱታ ድምጽ አሰባስበን ለትግራይ ክልል ምክር ቤት ብናስገባም የተመለሰልን ግድያና ማሳደድ ነው።” ብለዋል።

ከዚያም ለክልል ምክር ቤት የቀረበው ጥያቄ በኹለት ዓመት ውስጥ ምላሽ ካላገኘ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ይሄዳል በሚለው ሕግ መሰረት፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ አስገብተናል ነው ያሉት።

በደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት ላይ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች በሕገ መንግሥቱ መሰረት ምላሽ እስከሚሰጣቸው ድረስ ባሉበት ይቀጥላሉ ነው የሚለው እንጂ በትግራይ ክልል ይቀጥላሉ የሚል የለም ሲሉም ገልጸዋል።

“ይህንም ከአንድ ወር በፊት ባህር ዳር ከተማ ላይ ከ3 ሺሕ በላይ የክልሉ አመራሮች በተገኙበት መድረክ የፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪ ልዑክ አባል የነበሩት ሬድዋን ሁሴን አረጋግጠውልናል” ሲሉ ተናግረዋል።

ስለሆነም የማንነት ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መሰረት ብቻ የማይፈታ በድጋሜ አውስተው፤ “የሚያወጣው እውነታውን መቀበልና የህዝቡን መብት ማክበር ነው” ያሉ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን የሕወሓት ኃይሎች የቡድን መሳሪያ ታጥቀው በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል ሲሉ ከንቲባው አስረድተዋል።

“ሆኖም እኛ ልዩ ኃይሉ ትጥቅ እንዲፈታ ያደረግነው የፌደራሉን መንግሥት እምነን ነው” ካሉ በኋላ፤ “ያፈነገጡ ኃይሎች ዳግም ወደ ቦታው ቢመጡ አማራ ውስጥ ያለውን ኃይል በአንድ ፊሽካ ነው የምንጠራው።” ሲሉ ተደምጠዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here