አርብ ሰኔ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በምዕራብ ጎጃም ዞን በሰሜን ሜጫ ወረዳ ብራቃት ዙሪያ ቀበሌ ብራቃት ንዑስ ከተማ የሰው ማገት ወንጀል የፈጸሙት ግለሰቦች በ11 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸው የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
ነገሩ የሚጀምረው ሰኔ 11/2015 ከቀኑ 9፡30 አካባቢ በምዕራብ ጎጃም ዞን በሰሜን ሜጫ ወረዳ ብራቃት ዙሪያ ቀበሌ ብራቃት ንዑስ ከተማ የግል ተበዳይ የሆነው መ/ር ሀብታሙ እማኛው ከወንድሙ ጋር ሻይ ቡና ብለው ተሰነባብተው ወደ ቤቱ በመሄድ ላይ እያለ ተከሳሽ የሆነው አቡሽ ቻሌ የተባለው ግለሰብ ባለባጃጁን ሀብታሙ እማኛውን እስከሚሄድበት ድረስ እንዲሸኘው ይለምነዋል፡፡
ባጃጁን አቁሞ ተከሳሽ የሆነውን አቡሽ ቻሌን አሳፍሮ ይዞት እየሄደ እያለ 2ኛው ተከሳሽ ሱራፌል አድማሱ የተባለው ግለሰብ ጓደኛዬ ነው ያዝልኝ ይለዋል።
ትንሽ እንደተጓዙም ተከሳሽ ሱራፌል አድማሱ ደብቆት ይዞት የነበረውን ታጣፊ ክላሽ በማቀባበል በአሽከርካሪው ጀርባ ላይ በመደቀን በማስፈራራት ባጃጁን ከሰሜን ሜጫ ወረዳ ወደይልማና ዴንሳ ወረዳ ፅዮን ቀበሌ ልዩ ቦታው ኩል ወንዝ አካባቢ ሲደርስ ተጎጂው ባጃጁን አቁሞ ለማምለጥ ጥረት ቢያደርግም አልሳካ ይለዋል፡፡
ከፅዮን አዴት ዙሪያ ቀበሌ ሸገዝ ወንዝ ከቀኑ 11።00 ሰዓት አካባቢ ጫካ ውስጥ በማስገባት በማንበርከክ “800 ሺሕ ብር ካላመጣህ እንገልሃለን” በማለት ያስፈራሩታል እሱም ይህን ያህል ገንዘብ እንደሌለው ይነግራቸዋል፡፡
የወንድሙን ስልክ በማውጣት ስልክ በመደወል 800 ሺሕ ብር እንዲያመጣለትና ገንዘቡ በወቅቱ ካልደረሰ ግን እንደሚገሉት ይነግረዋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ የባጃጇን አቋቋምና የሰዎቹ ሁኔታው ስላላማራቸው ለይልማና ዴንሳ ወረዳ ፖሊስ ያዩትን ጥቆማ ይሰጣሉ፡፡
የይልማና ዴንሳ ወረዳ ፖሊስም በደረሰው ጥቆማ መሰረት ከቦታው ሲደርሱ አጋቾች በያዘው የጦር መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ ቢከፍትም፤ በአካባቢው ማህበረሰብ ጥረትና በፖሊስ ከበባ ተጎጅው ምንም ጉዳት ሳይደርስበት አጋቾቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉ ተገልጿል።
ፖሊስም የምርመራ መዝገብ በማደራጀት በተፋጠነ መዝገቡ እንዲታይላቸው በማድረግና መዝገቡን ለይልማና ዴንሳ ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት በመላክ ክስ እንዲመሰረትበት ይደረጋል፡፡
የይልማና ዴንሳ ወረዳ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኃላ ግለሰቦች ጥፋተኛ ናችሁ ተከራከሩ ተብሎ ቢፈቀድላቸው የፖሊስና የአቃቢ ሕግ ማስረጃ መቃወም ባለመቻላቸው ሰኔ 14/2015 በዋለው ችሎት በእያንዳንዳቸው በ11 ዓመት እስራት መቀጣታቸውን የይልማና ዴንሳ ወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ኢ/ር አዲሱ ብርሀኑ ገልጸዋል።



