የቤት ግብር ተመን ማሻሻያው በአተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ገለጹ

0
820

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከማሻሻያው በፊት የነበረው የክፍያ መጠን እዚህ ግባ የማይባል እንደነበር ገልጿል

አርብ ሰኔ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የቤት ግብር ተመን ማሻሻያው በአተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት ገልጸዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ይህን የገለጹት፤ አዲስ ቻምበር የቤት ግብር ማሻሻያ ላይ የግንዛቤ ማሰጨበጫ መድረክ በሚል ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩም የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አደም ኑሪ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ባቀረቡት ገለጻ፤ በአገልግሎት ላይ ያለው አዋጅ በ1968 የወጣውና አዋጅ ቁጥር 80 በመባል የሚታወቀው፣ የከተማ ቦታ ኪራይና የቤት ግብር በመባል የሚታወቀው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ከተማዋ ቀድሞ ያልነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ቪላ ቤቶችና ሪል ስቴቶች ጋር በተያየዘ አዋጁ በክፍያው ላይ ወቅታዊ በማድረግ ረገድ ክፍተት ያለበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

“ይህም ከከተማዋ እድገትና አሁን ካለንበነት የመሰረተልማት ፍላጎትና እድገት ደረጃ ጋር አብሮ የሚራመድ ግብር መሰብሰብ አልተቻለም፡፡” ያሉት አደም፤ በዚህም ምክንያት በከተማዋ ማህበረ-ኢኮኖሚ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ላይ ውስንነት እንዲኖር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

አክለውም፤ በቀደሞው አዋጅ “የጣሪያና የግድግዳ ግብር ከሚከፍሉ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል 96 በመቶ የሚሆኑት ከአምስት መቶ ብር በታች ይከፍሉ ነበር፡፡” ያሉ ሲሆን፤ “ይህም ገንዘብ ለልማት ሊውል ቀርቶ የመሰብሰቢያንም ወጭ የሚሸፍን አልነበረም፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት መሰንበት ሽንቁጤ ግብር ለከተሞች እድገት የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሆኖም በግብር ዙሪያ የሚወጡ አዋጆችና ደንቦች ከመውጣታቸው በፊትም ሆነ ከወጡ በኃላ የሚመለከታቸውን አካላት ሲያሳተፉ እንደማይታይ በመግለጽ፤ ከዚህ አንፃር ክፍተት እንዳለ አንሰተዋል፡፡በመሆኑም ንግድ ምክር ቤታቸው የግንዛቤ ማሰጨበጫ መድረኮችን በማመቻቸት መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ቀርበው እንዲመክሩ መድረክ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ይህም በግብር ጉዳዮች ላይ መተማመን እንዲኖር እና ችግሮችም ካሉ ለመቅረፍ መንግሥት የሚጠበቅበትን ገቢ እንዲሰበሰብ እንደሚያስችል አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ኃላፊ አስማማው ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ “የቤት ግብር አከፋፋል ላይ እሴትን ያገናዘበ ወቅታዊ ተደረገ እንጂ አዲስ አዋጅ አልወጣም፡፡” ብለዋል፡፡

በከተማዋ ከ285 ሺሕ በላይ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከተማዋ የምትሰበሰበው ግብር ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር አነሰተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ናይሮቢ ከአጠቃላይ ግብር ውስጥ የቤት ግብር 20 በመቶ ሲሆን ፣ የዛምቢያዋ ዋና ከተማ ሉሳካ 74 በመቶ እንደሚሰበሰቡም ለማሳያነት አቅርበዋል፡፡ ይሁንና አዲስ አበባ ከተማ የምትሰበሰበው ከ1 በመቶ በታች 0 .08 መሆኑን አንስተዋል፡፡

 

የአዲስ ቻምበር የግልግል ተቋም ዳይሬክተር ዮሀንስ ወ/ገብርኤል ባቀረቡት የሕግ ምልከታ፤ “በአዋጅ የወጣ የግብር ማሻሻያ የሚሻሻለው በአዋጅ ነው፡፡” ሲሉ ሞግተዋል፡፡ “አዲስ ደንብም ሲወጣ በደንብ ይተካል” ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢንቨስትመንት አማካሪው ያሬድ ሀይለ መስቀል በበኩላቸው፤ “ይህ የቤት ግብር ተመን ማሻሻያ ወቅቱን ያላገናዘበ እና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡” ሲሉ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ አንጻር ሞግተዋል፡፡በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው፤ “ግብር መክፍሉን እንደግፋለን ነገር ግን አሁን ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ታሳቢ ያደረገ አይደለም፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በተጨማሪም “የመከፍል አቅም የሌላቸው ዜጎች መክፍል አይችሉም እና እነርሱስ እንዴት ይታያሉ?” የሚሉ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡

ህብረተሰቡ ላይ ተደራራቢ ችግር እንዳለ እንረዳለን ያሉት አስማማው፤ ሆኖም የቤት ግብር ትመናው በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመክፍል አቅም የሌላቸው ባለቤቶች መክፍል እንደማይችሉ ከተረጋገጠ ለአንድ ዓመት ከከፍያ ነፃ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡

የአምልኮ ቦታዎች፣ ኢምባሲዎች፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የቤት ግብር ማሻሻያው የማይመለከታቸው መሆናቸውን የንብረት ግብር ማስተባባሪያ ፅህፈት ቤቱ ማስታወቁንከአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here