ረቡዕ ነሐሴ 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄሬ ወረዳ የአዋሽ ወንዝ ከልክ በላይ መሙላቱን ተከትሎ፤ 657 አባወራዎች ወይም 3 ሺሕ 156 ሰዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ቡሳ ጎኖፋ መምሪያ አደጋው የደረሰው ነሐሴ 05/2015 ሌሊት ላይ መሆኑን ገልጾ፤ ነዋሪው ከቤቱ ወጥቶ በመሸሹ በሰው ሕይወት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳላደረሰ አስታውቋል፡፡
ነዋሪው ነፍሱን ለማዳን ባደረገው ሽሽት ከቤት ባዶ እጁን በመውጣቱና፤ መኖሪያ ቤቱ በወንዙ መሙላት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ አሁን ላይ ከፍተኛ ለሆነ የምግብ እና መጠለያ ችግር መዳረጉ ተጠቅሷል፡፡
የወረዳው አስተዳደር እና የምዕራብ ሸዋ ዞን ቡሳ ጎኖፋ መምሪያ፤ ተጎጂዎቹን ለመርዳት ጥረት ቢያደርጉም ከችግሩ ስፋት አንጻር በበቂ አለመሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ጎርፉ በ500 ሄክታር መሬት ላይ የለማን ሰብል ሙሉ ለሙሉ ያወደመ ሲሆን፤ በአርሶ አደሮች የወደፊት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀና እና መሬቱን በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
አደጋው ከተከሰተ አምስተኛ ቀኑን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ አስቸኳይ ድጋፍ ለተፈናቃዮቹ ለማድረግ ቸልተኝነት ታይቷልም ነው የተባለው።
በተጨማሪም ሰዎች ከአደጋው ሸሽተው በአንድ ቦታ ተሰብስበው ያሉ በመሆኑ፤ ለተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ ሊጋለጡ ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩም ተጠቁሟል።
ለተጎጂዎቹ ምግብ፣ ልብስ፣ ጊዜያዊ መጠለያ፣ የንጽሕንና መጠበቂያ እና ሉሎች መሠረታዊ ቁሳቁሶች የሚያስፈልግ በመሆኑም ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
የአዋሽ ወንዝ በተለያዩ ጊዜያት ከልክ በላይ በመሙላት በተለይም በአፋር እና መተሐራ አካባቢ ተደጋጋሚ ጉዳትና መፈናቀል እንደሚያስከትል ይታወቃል።



