ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር አድርገው ሾመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ ሹመቱን የሰጡት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ ሆኖ እንዲቋቋም በ1294/23 የራስ ገዝ አዋጅ በረቀቀው መሰረትና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ/28/2015 ባካሄደው 23ኛው መደበኛ ስብሰባ የዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማጽደቁን ተከትሎ ነው፡፡
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን በላቀ መልኩ እንዲፈጽሙ እንዲሁም የሰው ሀብትና የፋይናንስ አስተዳደር ነጻነትን በማረጋገጥ በአገሪቱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የላቀ አስተዋጾ እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ ከተሾሙት ቻንስለር በተጨማሪም አዲስ የቦርድ አመራሮች የተሰየሙለት ሲሆን፤ ቦርዱም ዩኒቨርሲቲውን በሃላፊነት ሊመሩ የሚችሉ ፕሬዚዳንት እና ም/ፕሬዚዳንቶችን በቀጣይነት እንደሚሾም ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።



