ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲደራጅ ለተወሰነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ተሾሙ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቦርድ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ፍሬህይወት ታምሩ የየኒቨርስቲው የቦርድ ሊቀመንበር አድርጎ መሾሙን ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ደግሞ፤ ከነሐሴ 24/2015 ጀምሮ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ2016 ጀምሮ ራስ ገዝ እንዲሆን በአዋጅ የተፈቀደ ቢሆንም፤ ሙሉ በሙሉ ራስ ገዝ ሆኖ ሥራ የሚጀምረው የሚተዳደርበት መመሪያዎች ከተዘጋጁ በኋላ ከ2017 ጀምሮ እንደሚሆን ሚኒስትሩ መናገራቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ሹመት ማግኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡



