ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም የፖለቲካና የጸጥታ ኹኔታ ላይ የሚመክር የግምገማ መድረክ በባህር ዳር መካሄድ ጀምሯል፡፡
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ፤ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና ዘላቂ ሰላም መገንባት የክልሉ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
“በግጭት ምክንያት የወደሙ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን እና የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል” ያሉም ሲሆን፤ ከመልካም አስተዳደር አኳያ በተለይ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲቀረፉ ማድረግ ከአመራሩ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የሚሳተፉበት የግምገማ መድረክ ባህር ዳርን ጨምሮ በጎንደር፣በደሴና በደብረ ብርሃን እንደሚካሄድ ርዕሰ መስተዳደሩ መጠቆማቸውን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዛሬ በተጀመረው የግምገማ መድረክ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡



