“ከባለፉት ጊዜያት አሁን ላይ ያለው የክልሉ የጸጥታ ኹኔታ እየተሻሻለ መጥቷል” የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

0
169

ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ ከሰሜን ሸዋ ዞንና ደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ አመራሮች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ 7 ግቦችን የያዘ ውይይት እንደሚካሄድ የገለፁት የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው፤ የመድረኩ ዓላማ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በመልሶ ማደራጀት አዲስ የተደራጀውን የጸጥታና የፖለቲካ መዋቅር በራሱ እንዲቆም ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ የተዋቀረው የፖለቲካና የጸጥታ መዋቅር እስከታችኛው ማህበረሰብ ድረስ አቅም እንዲኖረው ማስቻል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አደረጃጀቱን እስካሁን ከነበረው በተጨማሪ እስከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ መጨረስ ሲሆን፤ በሰላም ጉዳይ የሕዝብ ግንኙነት ሥራን ማጠናከር፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሥራዎችን መስራት፣ በሕዝቡ ውስጥ ያሉ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው አቅጣጫ ማስቀመጥና በማህበረሰቡ የመልማት አቅም ማሳደግ ላይ ውይይት እንደሚካሄድም ነው የገለጹት፡፡ኅብረተሰቡ ውስጥ የደረሰውን ቀውስና ከላይ እስከ ታች እንዲፈርስ ተደርጎ የነበረውን የክልሉን የጸጥታ መዋቅር በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲቆም ለማስቻል የጋራ አቅጣጫ እንደሚሰጥም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አሁን ያለውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት የክልሉ መንግስት የሰላም ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት ኃላፊው፤ አሁን ያለው ግጭት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈታ ባለመሆኑ ከጦርነት ውጭ በሃሳብ ብልጫና በውይይት መፍታት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ጦርነቱ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ልማት የሚያውክ እንጂ ጥያቄ አይመልስም ያሉት ኃላፊው፤ የህብረተሰቡን ምሬት በመገንዘብ ወደ ሰላም አማራጭ መገባት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ያለው የክልሉ የጸጥታ ኹኔታ ከባለፉት ወራቶች የተሻለ መሆኑንና ኹሉም የዞኑ ከተሞችና አብዛኛዎቹ ወረዳዎች ነፃ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፤ በክልሉ አብዛኛዎቹ ቀበሌዎች ላይ ግን ሰላም አለመኖሩን መናገራቸውን ከሰሜን ሸዋ ዞን ኮምዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አብዛኛው ማህበረሰብ የሰላም አማራጭ በመከተል ላይ መሆኑንና ክልሉ በየዘርፉ ያለውን የሕዝቡን የኑሮ ፈተና ለመመለስ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here