በሳዑዲ ለ12 ዓመታት በሆስፒታል አልጋ ላይ ያሳለፈው ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ ተሸኘ

0
153

ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በሳዑዲ አረቢያ ከአስራ ኹለት ዓመታት በፊት “ማን እንዳደረሰው ባልታወቀ” የመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰበት ካሱ አሊ እድሪስ የተባለ ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ መሸኘቱን፤ በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

ካሱ በደረሰበት አደጋ በወቅቱ ኮማ ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን፤ በአገሪቱ የመከላከያ ሆስፒታል ( ሃሪሰል ወጠኒ ሆስፒታል) ተወስዶ ሲታከም መቆየቱ ተነግሯል።

ግለሰቡ ሕጋዊ ዶክመንት ያልነበረው በመሆኑ ቤተሰቡን ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ እንደነበር የገለጸው ኤምባሲው፤ ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር በተደረገ የማፈላለግ ሂደት ቤተሰቡን አደጋው በደረሰ በ11 ዓመቱ ማግኘት መቻሉን ገልጿል።

በዚህም ቤተሰቦቹ በተለይም እናቱ “ወደ አገር ቤት በምንም አይነት ሁናቴ ይምጣልኝ” ብለው በጠየቁት መሰረት ወደ አገር ቤት እንዲገባ ኤምባሲው ከደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመነጋገር ቀጥታ እንዲቀበለው ከስምምነት ተደርሶ በዛሬዉ ዕለት ወደ አገር ቤት መሸኘቱ ተገልጿል።

በዚህም መሰረት ካሱ ኢትዮጵያ የደረሰ ሲሆን፣ የደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታልም ቃል በገባው መሰረት እንደተቀበለው ኤምባሲው አስታውቋል።

ሃሪሰል ወጠኒ ሆስፒታል ተካሚውን ዛሬ ወደ አገር እስከተሳፈረበት ቀን ድረስ፤ በግምት ስምንት ሚሊዮን የሳውዲ ሪያል (2.13′ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር) የሚሆን ወጪ አውጥቶ እንዳሳከመው ተነግሯል።

ይህ እንዲሳካ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የካሱን ሙሉ የአልጋ ትኬት፣ የኹለት የጤና ባለሙያዎችን ትኬት ወጪ የቻለ ሲሆን፤ ኤምባሲውም ካሱን ወደ ኢትዮጵያ ይዘውት ለሚሄዱ ለኹለት የሌላ አገር ዜጋ የጤና ባለሙያዎች ነፃ ቪዛ በመስጠት ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here